ዕረቡ ሐምሌ 6 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል ተከስቶ ለኹለት ዓመታት ያህል የዘለቀውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተቋቋመው አብይ ኮሚቴ ትናንት ሐምሌ 5 ቀን 2014 የመጀመሪያ ስብሰባውን አካሂዷል።
አብይ ኮሚቴው በስብሰባው፤ በአፍሪካ ህብረት መሪነት ለሚካሄደው የሰላም ውይይት የራሱን የአሰራርና ሥነምግባር አካሄድ ተወያይቶ መወሰኑን የኮሚቴው አባልና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪ ሚኒስትር የሆኑት፤ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስታውቀዋል።
ኮሚቴው በንዑሳን ኮሚቴዎች በመደራጃትም ኃላፊነት ተከፋፍሎ ሥራውን መጀመሩንም ነው አምባሳደር ሬድዋን የገለፁት፡፡
መንግስት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ያለውን ችግር ለመፍታት፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰብሳቢነት የሚመሩትና በአጠቃላይ ሰባት አባላት ያሉት የሰላም አማራጭ ዐቢይ ኮሚቴ ሰኔ 20 ቀን 2014 ማቋቋሙ ይታወሳል።



