መነሻ ገጽዜናትንታኔወለጋን ማን ይታደገው?

ወለጋን ማን ይታደገው?

ኢትዮጵያን እያስተዳደረ ያለው መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ ቦታዎች ንጽሐን ላይ ጭፍጨፋ እና ግድያ የፈፀሙ ታጣቂ ኃይሎችን በአግባቡ ተቆጣጥሮ ተጠያቂ ማድረግ እንዲሁም የፀጥታ መዋቅሩን መፈተሽ ባለመቻሉ፤ ችግሩ ይበልጡኑ ተንሰራፍቶ ይገኛል።

በዋነኛነት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ እና ምዕራብ ወለጋ ዞን በተለያዩ አቅጣጫዎች ማንነትን መሠረት ባደረገ መልኩ የሚፈጸሙ ጅምላ ግድያዎችና አሰቃቂ ጭፍጨፉዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩና እየተስፋፉ ነው።

አንድ የቤተሰብ አስተዳዳሪ የቤቱን እና የቤተሰቡን ደኅንነት ማረጋገጥ ካልቻለ አስተማማኝ ሁኔታ ላይ አለ ለማለት እንደማያስደፍር ሁሉ፣ የኦሮሚያ ክልልም በወለጋ ዞኖች ያለው የፀጥታ ሁኔታ ከአቅሙ በላይ ከሆነ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ችግሩን መቅረፍ ይጠበቅበታል።

ይህ ካልሆነ ግን የኦሮሚያ ክልል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የአመራር ቀውስ እንዳለበት አመላካች መሆኑን ሲናገሩ የሚደመጡ እንዳሉ ሁሉ፣ በወለጋ የችግሩ ገፈት ቀማሽ የሆኑ ሰዎችም ይህንኑ ለአዲስ ማለዳ አረጋግጠዋል።

ብዙ ጊዜ ለንጽጽር የሚቀርበው የሶማሌ ክልል ነው። ክልሉ በቀድሞ አመራሮቹ ዘመን ከፍተኛ ግጭች እና መፈናቀል የታየበት ወቅት ቢኖርም፣ በአሁን ሰዓት ክልሉ ጠንካራ አመራር በማግኘቱ እና ኅብረተሰቡን በማቀናጀት የፀጥታ አካሉን እና የፖለቲካ መዋቅሩን አስተሳስሮ ማስተዳደር በመቻሉ የክልሉን ሰላም ማረጋገጥ መቻሉ ይነገራል።

ማን ይጠየቅ?

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ የሚኖሩ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፣ የክልሉ ልዩ ኃይል ሰዎችን ከጥቃት ከመታደግ ይልቅ ለኦነግ ሸኔ ቡድን ተባባሪ ኃይል እንደሆነ ነው።

በተጨማሪ ቀን ላይ በቡድኑ፤ ሌሊት ደግሞ በልዩ ኃይሉ ጭምር ለጥቃት እንደሚጋለጡ እና ችግሮች በሚከሰቱባቸው ወቅት ለልዩ ኃይሉ የመከላከያ የደንብ ልብስ በማልበስ የመከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው እንዳቀና የሚነገርባቸው ወቅት እንዳለም ያስረዳሉ።

በተጨማሪ፣ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በክልሉ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ለመቆጣጠር እየተሠራ ነው ከማለት ወጥቶ፣ ከአቅሙ በላይ መሆኑን በማረጋገጥ ኃላፊነቱን ሙሉ ለሙሉ ለፌዴራል መንግሥት ማስተላለፍ ባለመቻሉ ችግሩ መቅረፍ አልተቻለም የሚሉ አሉ።

በፌዴራል መንግሥትም ከተሰጠው ትኩረት አናሳነት እና ቸልተኝነት ጋር ተያይዞ፣ በወለጋ ዞኖች በተለያዩ አካባቢዎች ማንነትን መሠረት በማድረግ የሚፈፀሙ ጥቃቶች አቤት ባይ ማጣታቸውን ሲናገሩ የሚሰሙ የፖለቲካ ፓርቲዎችም አሉ።

ከዚህ አንፃር የፌዴራል መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 395/95 በአንድ ክልል ውስጥ ግጭት በሚያጋጥምበት ወቅት በክልሉ መንግሥት ጠያቂነት የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ችግሩን በዘላቂነት ማረጋገጥ ቢኖርበትም፣ ይህን ተግብሯል ለማለት እንደማያስደፍር ሲያነሱ የሚደመጡም አልጠፉም።

ከዚህ አኳያ ከክልሉ መንግሥት በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥትም ተጠያቂ የሚሆንበት እድል እንዳለም ይጠቆማል።

የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጌትነት ወርቁ፣ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ በተለያዩ አቅጣጫዎች በተደጋጋሚ በንጽሐን ዜጎች ላይ የሚፈፀመውን ማንነት ተኮር ግድያ እና ጥቃቶችን በማስቆም ሰላምን በዘላቂነት ማስፈን ከክልሉ ባለፈ የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት መሆኑ ለማንም የሚታወቅ ነው ይላሉ።

ነገር ግን፣ አብዛኛው የክልሉ ባለሥልጣናት የሸኔ ቡድን መኖርን በመፈለጋቸው እና በፌዴራል መንግሥት በኩል በታየው ቸልተኝነት ምክንያት ችግሩ እንዳልተቀረፈ እንዲሁም በቡድኑ የሚፈፀሙ ጥቃቶች እንዳልቆሙ ጠቁመዋል።

በአካባቢው እየተካሄደ ያለው ጥቃት ማንነት ላይ ያነጣጠረ ነው ከማለት በተጨማሪ የዘር ማጥፋት እየተካሄደ ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ በሰፈረው ሕግ መሠረት የዘር ማጥፋት ተብለው ከተቀመጡት ውስጥ ዐስሩንም መስፈርቶች እና አራቱንም ምክንያቶች አሟልቶ እንዳገኙት አስረድተዋል።

- ይከተሉን -Social Media

በኮተቤ ሜትሮፓሊታን ዩኒቨርሲቲ መምህር እና የፖለቲካ ምሁር አሰፋ አዳነ (ረ/ኘ) እንደገለጹት፣ በአንድ አገር አምባገነንም ሆነ በሕዝብ ተመርጦ እንዲሁም በመፈንቅለ መንግሥት አገርን ለማስተዳደር ሥልጣን የሚይዝ መንግሥት የመጀመሪያ ሥራው ዜጎች ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሰው ሥራ እንዲሠሩ ማስቻል እና ሰላምን ማረጋገጥ ነው።

ይህ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ አሁን ላይ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ባለፉት አራት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮችን መቅረፍ እንዳልቻለ እና በኦሮሚያ ክልልም በወለጋ ዞኖች የሚፈጠሩ ግድያዎችን እንዲሁም ጥቃቶችንም መፍታት አልቻለም ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ለልማት ሥራዎች ከሚሰጣቸው ትኩረቶች ጎን ለጎን በሚያሳየው ቸልተኝነት እና ከቀድሞ ኢሕአዴግ በተሻለ ሕግ መተግበር ባለመቻሉ እንደሆነ ተናግረዋል። እናም ችግሩን በዘለቄታ ለመቅረፍ ከታሰበ ከላይ የተጠቀሱ ችግሮችን ማስተካከል እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ምሁሩ አክለውም፣ በወለጋ ዞኖች በተለያዩ ቦታዎች ንጽሐን ዜጎች ላይ የሚፈፀሙ ግድያ እና ጥቃቶች ከሸኔ ቡድን ጎን ለጎን የክልሉ ልዩ ኃይል ተባባሪነት እንዳለበት የአካባቢው ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ሲያነሱ አድምጫለሁ ባይ ናቸው።

በተጨማሪም፣ በአካባቢው ጥቃቱን ታጣቂ ኃይል ብቻ እየፈፀመ ይገኛል በሚለው እንደማይስማሙ እና በአካባቢው ያለው የፀጥታ ኃይልም ቡድኑን ለመቆጣጠር እንዳልቻለ ብቻ ማሳያ ሳይሆን፣ እንዳይችል ስለተገደደ በመደረጉ የሚፈጠር ችግር ነው ብለዋል።

አያይዘውም፣ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የልዩ ኃይል አባላትን በማቀናጀት በአካባቢው ከማሰማራት በተጨማሪ፣ የአካባቢው ነዋሪዎችም ራሳቸውን በራሳቸው እንዲከላከሉ በማድረግ ረገድ መንግሥት ፍላጎት አለው ለማለት እቸገራለሁ ባይ ናቸው።

ከዚህ በፊት ትጥቅ ያላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች፣ በመንግሥት አካላት በኩል ትጥቃቸውን እንዲፈቱ የተገደዱበት ሂደት መኖሩ እና ቡድኑም ይህን ተከትሎ ጥቃቶችን ለመፈፀም ምቹ እድል ተፈጥሮለታል ይላሉ።

ፓርቲዎቹ በመግለጫቸው ምን አሉ?

- ይከተሉን -Social Media

እናት፣ መኢአድ እና ኢሕአፓ ፓርቲዎች በሰጡት የጋራ መግለጫ፣ በኦሮሚያ ክልል እንዳሻው የሚፈነጨውና በሥምም በግብርም የተለያየ ካባ የሚደረብለት ታጣቂ ቡድን፣ ለሥልጣን ሚዛን ማስጠበቂያነት እየዋለ ነው ብለዋል።

በተጓዳኝ በታሪክ በሚጠቀሱ የዘር ፍጅቶች መገናኛ ብዙኀን ያላቸው አስተዋጽኦ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ደግፈው ይቆማሉ ወይም ዐይተው እንዳላዩ፣ ሰምተው እንዳልሰሙ ያልፉታል ብለዋል፤ ፓርቲዎቹ።

‹‹እየተጨፈጨፈ ያለውን ማኅበረሰብ ጨምሮ በሚሰበሰብ ግብር የሚተዳደሩ የመንግሥትና አፍቃሬ መንግሥት ሚዲያዎች በተራ ጉዳይ ጊዜያቸውን የሚያጠፉትን ያህል ለሰው ነፍስ ግድ የማይሰጣቸው ሆነው ዐይተው እንዳላዩ አልፈዋል። አለፍ ሲልም፣ ለሌሎች ስለጉዳዩ አብዝተው ለሚጮኹ አካላት የተቃርኖ ዘገባና ማስተባበያ ዝግጅቶችን በመሥራት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍርድ አያመልጡም።›› በማለት ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል፣ በቂ ባይሆንም የአቅማቸውን ያህል የሚጮኹትን እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፣ የሕይወት ዋጋ ጭምር የሚከፍሉ ቁርጠኛ የጸጥታ ኃይሎች የሚመሰገኑትን ያህል የማጣራት፣ የማውገዝ፣ ዘላቂ የመፍትሔ አቅጣጫ የማስቀመጥ ሕገመንግሥታዊ መሠረትና ሥልጣን ያላቸው እንደራሴዎችና ምክር ቤት ያሉ ተቋማት ሆን ብለው ዝምታን በመምረጣቸው በአገሪቱ እየሆነ ላለው የዘር ፍጅት የታሪክና ፍትሕ ባለዕዳ ናቸው ይላሉ።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በበኩሉ፣ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች በአማራ ተወላጆች ላይ በደረሰው የዘር ማጥፋት ወንጀል ላይ ኹለቱም ምክር ቤቶች ተባባሪ ናቸው ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።

ፖርቲው ባወጣው መግለጫ፣ በአማራ ክልል ተወላጆች ላይ የተቀናጀ፣ ተከታታይና ሥልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል ሲፈፀም፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥቃቱን በግልፅ አለማውገዛቸው የጥቃቱ ተባባሪ ናቸው ብዬ እንዳምን አድርጎኛል ብሏል።

ኹለቱ ምክር ቤቶች በክልሉ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጥቃት በግልፅ አለማውገዛቸው በአማራ ሕዝብ ላይ ያላቸውን ንቀት በግልፅ ያሳያል ነው ያለው።

የድርጅቱ ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በመግለጫው ላይ እንዳሉት፣ በአማራ ንጽሐን ላይ የሚደርሰውን ጥቃት መንግሥት ካላስቆመ ኢትዮጵያ ወደ እርስ በእርስ ግጭት ልትገባ እንደምትችል አሳስበዋል።

- ይከተሉን -Social Media

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን፣ በክልሉ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ወለጋና አካባቢው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር እንዲሆን ሲል የመፍትሔ ሐሳቡንም አቅርቧል።

በተጨማሪም፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ሀዘን እንዲታወጅ የጠየቀው አብን፣ ከዚህ ባለፈ ግጭቱን ያቀጣጠሉት የኦነግ፣ የኦፌኮና የክልሉ አመራሮች በሕግ እንዲጠየቁ ሲልም አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እንዲሁ መንግሥት ማንነትን መሠረት አድርገው የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለማስቆም ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ዜጎችን ከአሰቃቂ ጭፍጨፋ የመጠበቅ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ አሳስቧል። እንዲሁም መፍትሔ ይሆናሉ ሲል ምክረ ሐሳቦች አቅርቧል።

‹‹ሆኖም መንግሥት ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ማሳሰቢያዎችንም ሆነ ምክረ ሐሳቦቻችንን ለመቀበል ምንም ዓይነት ፍላጎት አላሳየም። የሕግ የበላይነትን የማስከበር ኃላፊነቱም ከእለት እለት ጥያቄ ውስጥ እየገባ መምጣቱ በብርቱ አስግቶናል።›› ብሏል።

ፓርቲው ከኹለት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ፣ በቄለም ወለጋ አካባቢ በንጹሐን ዜጎች ላይ የተለመደ ተመሳሳይ አሰቃቂ ጭፍጨፋ መፈጸሙ እጅግ አሳዝኖናል ብሏል። መንግሥት ታጣቂ ኃይሎች ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ተከትሎ እየሸሹ የነበሩት ታጣቂዎች የፈጸሙት እንደሆነ መግለጹንም አስታውሷል።

ፓርቲው መንግሥት እንዲህ ዓይነት እርምጃዎች ሲወሰዱ ታጣቂ ኃይሎች በሽሽት ላይ ምን ዓይነት ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ፣ የሕወሓት ወራሪ ኃይል ከአማራና ከአፋር ክልል ሲወጣ ከፈጸመው እኩይ ድርጊት በመማር ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ሲገባው ሆነ ብሎ (በተባባሪነት)/በቸልተኝነት/በአቅም ማነስ/በተለያዩ ምክንያቶች፣ እንዲሁም የእኩይ ኃይሉ  ተባባሪዎች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ በመሰግሰጋቸው እና የዜጎችን ነፍስ ለመታደግ የሚያስችሉ ተግባራትን በቁርጠኝነት ባለመተግበሩ ተጠያቂ ያደርገዋል ብሏል።

ወለጋን ማን ይታደግ?

የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጌትነት ወርቁ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ በሰጡት አስተያየት፤ እየተፈጸመ ያለውን ማንነት ተኮር ጥቃት በአጭር ጊዜ በዘላቂነት መቅረፍ ካልተቻለ የመገናኛ ብዙኀን፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሲቪክ ተቋማት ሀቁን በማሳወቅ እንዲሠሩ እና ይህም አንዱ መፍትሔ እንደሚሆን ገልፀዋል።

ዋና ጸሐፊው አክለውም፣ አብዛኛው የክልሉ ባለሥልጣናት የሸኔ ቡድን መኖርን እንደሚፈልጉት ተረድቶ የፌዴራል መንግሥት ፍቃደኛ ከሆነ እንዲሁም ከወደደ አመራሮችን መቀየር እንዳለበት እና ተጨማሪ መፍትሄ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የልዩ ኃይሎች አወቃቀሮች የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይልን የሚያክል በብዛትም ሆነ በትጥቅ የሚበልጠው የለም ያሉ ሲሆን፣ ቡድኑ በአካባቢው የሚያደርሰውን ጥቃት ግን መግታት እንዳልቻለ አመልክተዋል።

ከተለያዩ ክልሎች በተውጣጡ ልዩ ኃይል አባላት የአካባቢውን ሰላም ለማስፈን መሥራት ይቻላል ብለው በሚናገሩ ሰዎች ሐሳብ እንደማይስማሙ ግን ዋና ጸሐፊው አስቀምጠዋል።

‹‹ይህ የፖለቲካ ማድመቂያ ከመሆን ባለፈ ስለማይፈይድ፤ በአካባቢው ሰላም ለማስፈን መሥራቱ ጥሩ የሚሆነው የመከላከያ ኃይል ብቻውን ማሳተፉ ነው›› ይላሉ።

እስከ አሁን ባለው የመከላከያ ኃይል በድጋፍ መልክ ወደ አካባቢው በማቅናቱ  ከክልሉ ልዩ ኃይል ጋር በጥምረት አጥፊ ቡድኑን ለመቆጣጠር ወደ ፍልሚያ የሚገቡበት እድል ያለ ቢሆንም፣ ከክልሉ ባለሥልጣናት እና ከጎን ከሚሰለፉ ኃይሎች ሾልከው በሚወጡ መረጃዎች ሳቢያ ሠራዊቱ የሚጠቃበት ሁኔታ እንዳለም ገልፀዋል።

ለዚህ ደግሞ አካባቢውን በመከላከያ ኃይል ስር ብቻ እንዲሆን ማድረግ እና ከዚህ ኃይል በላይ የሚሆንበት እድል ከኖረ እስከ ዓለም ዐቀፍ ድረስ ድጋፍ መጠየቅ ያስፈልጋል ብለዋል።

ዋና ጸሐፊው አያይዘው የአካባቢው ነዋሪ ራሱን በራሱ ለመከላከል ትጥቅ በሚታጠቅበት ወቅት ትጥቅ እንዲፈቱ የሚገደዱበት ሁኔታ እንዳለ ጠቅሰዋል። ነገር ግን ይህን ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁመው፤ መንግሥት ከዚህ ሂደት በመውጣት የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲከላከሉ ከማሠልጠን በተጨማሪ በማስታጠቅ እና በመደገፍ ኃላፊነቱን ቢወጣ የተሻለ ነው ብለዋል።

በዚህም መንገድ ቡድኑን ከመግታት ጎን ለጎን አመርቂ ውጤት ሊመጣ የሚችልበት ሂደት ሰፊ እንደሆነ ዋና ፀሐፊው ጠቁመዋል።

መምህር እና የፖለቲካ ምሁሩ አሰፋ አዳነም፤ መንግሥት በቀጣይ ከዚህ ሂደት በመውጣት፣ ከመከላከያ ኃይሉ ጎን ለጎን የአካባቢው ነዋሪዎችን በማሠልጠን እና ትጥቅ በማስታጠቅ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲከላከሉ በማድረግ ረገድ መሥራት አለበት በሚለው የመፍትሔ ሐሳብ ይስማማሉ።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍ እና የልማት ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ታመነ አባተ በበኩላቸው፣ በኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች ለሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች እልባት በማስቀመጥ ሰላምን ማረጋገጥ ከክልሉ መንግሥት በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነት ነው ይላሉ።

ምክንያቱም መንግሥት በሥልጣን ላይ እንዲቆይ በአገራዊ ምርጫ በሕዝብ ሲመረጥ፣ በኢትዮጵያ በሚፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች፣ በአገር አንድነት ላይ ችግር የሚፈጥሩ አካላት ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ሰላምን ለማረጋገጥ ነው። በመሆኑም መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቶ ችግሩን መቅረፍ ነው ያለበት ሲሉ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ማኅበረሰቡን በማደራጀት ወይም በማዘጋጀት ራሱን በራሱ እንዲከላከል የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበትም ዋና ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል።

ሻለቃ ታመነ፤ የክልሉ ልዩ ኃይል ከቡድኑ ጋር ግንኙነት አለው የሚሉ ጥያቄዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ የክልሉ መንግሥት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ያሉ ችግሮችን ማውጣት እንዳለበት እና የፌዴራል መንግሥትም የአመራር ለውጦችን በማድረግ ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተጨማሪም የክልሉ መንግሥት ከአቅሙ በላይ ከሆነ ለፌዴራል መንግሥት ማሳወቅ እንዳለበት እና በዚህ ወቅት ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ልዩ ኃይሎች በማቀናጀት የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ቢሠራ ይመከራል ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

በወለጋ አካባቢ ለሚንቀሳቀሰው የሸኔ ቡድን የመከላከያ ኃይል አቅም አልቻለም ተብለው በሚነሱ ሐሳቦች እርሳቸውም አይስማሙም። ይህን ሐሳብ ጠቅሰውም፣ የተቀናጀ የመከላከያ ኃይል አካባቢውን እንዲያስስ ከማድረግ ባሻገር የአካባቢው ነዋሪ ራሱን እንዲከላከል በመደገፍ ረገድ መንግሥት በአትኩሮት ቢሠራ ቡድኑን መቆጣጠር እና ሰላምን ማረጋገጥ እንደሚቻል አስረድተዋል።

ኢዜማ በመግለጫው፤ መንግሥት በተለይም በወለጋ አካባቢ በዚህ ደረጃ ለምን የጸጥታ ችግሮችን መቆጣጠር እንደተሳነው ለሕዝብ በግልጽ የማሳወቅ ግዴታ ያለበት መሆኑን ያስታውሳል። ከዛ በተጨማሪ፣ ዘላቂ መፍትሔዎችን ለማምጣት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር መሥራት እንዳለበት ማስገንዘቡን አስረድቷል።

ይህ መፍትሄ የጊዜ ገደብ ወጥቶለት አካባቢውን ከመሰል ጥቃቶች በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንደሚያወጣ በይፋ በመግለጽ፣ መንግሥት ለዜጎች ደኅንነት መጠበቅ ምን ያህል ቁርጠኛ እንደሆነ እና መንግሥታዊ የማስፈጸም አቅም እንዳለው ሊያሳይ ይገባልም ብሏል።

‹‹ይህን ማድረግ የማይችልና ዛሬም አድበስባሽ ሆኖ መቀጠል ካሰበ አካባቢውን የመቆጣጠር አቅምም ሆነ ፍላጎት እንደሌለው ያሳብቅበታል። ከመንግሥት የደኅንነት ክፍተቶች  ባሻገር  በአካባቢው የሚኖሩ ዜጎች ከአብራካቸው የወጡ፣ አብረዋቸው ለረዥም ጊዜ የኖሩ እና በጋብቻ፣ በባህል፣ በእምነት፣ የተጋመዱ ወንድምና እህት ዜጎችን የመኖር መብት ለማስከበር አብረው በመቆም፤ ከዚህ ዓይነቱ ዘግናኝ ጭፍጨፋ በመከላከል ሰብዓዊ እና ኢትዮጵያዊ እሴቶችን እንዲያስቀጥሉ ፓርቲው ጠይቋል።

እንዲሁም በማኅበረሰብ መካከል የተፈጠረ ጥላቻ እንዳልሆነና ደም የጠማቸው ግፈኞች  እኩይ ተግባር መሆኑን በተግባር እንዲያሳዩ አበክሮም ጠይቋል። ፓርቲው በተጨማሪ የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ መዋቅር በኃይል እጥረት ምክንያት ሰላም ማስፈን በማይችልባቸው ቦታዎች ላይ ማኅበረሰቡ ራሱን ለመከላከል የሚያስችለውን አደረጃጀት እና ትጥቅ እንዲኖረው እንዲደረግ ብሏል።

አዲስ ማለዳ ከሕግ ባለሙያው ጥጋቡ ደሳለኝ ጋር ቆይታ አድርጋለች። እርሳቸው በበኩላቸው በወለጋ የተለያዩ ዞኖች ያለውን ሰላም የማስፈን ግዴታ የመንግሥት እንደመሆኑ መጠን፣ በአካባቢው ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ ካስፈለገ የፌዴራል መንግሥት የፀጥታ መዋቅሩን እና የክልሉን አስተዳዳራዊ መዋቅሮች መፈተሽ አለበት ብለዋል።

ለዚህም የክልሉ መንግሥት ለሸኔ ቡድን መረጃ በመስጠት እና አንዳንድ አካላትን ሁሉ በመደበቅ ተባባሪ ነው ሲባል ይሰማል ይላሉ። የሕግ ባለሙያው አክለውም፣ የክልሉ ልዩ ኃይል ዜጎችን ከጥቃት የሚታደግ ባለመሆኑ ከሌሎች ክልሎች ብቻ በተውጣጡ ልዩ ኃይሎች እና በመከላከያ ሠራዊት ዜጎችን ለመታደግ እንዲሁም አካባቢውን ከስጋት ቀጠናነት ለማውጣት የፌዴራል መንግሥት ሊሠራ ይገባል ይላሉ።

የክልሉን መንግሥት መዋቅር ከማሻሻል በተጨማሪ፣ በወለጋ ዞኖች የሚገኙ አካባቢዎች በፌዴራል መንግሥት ስር እንዲተዳደሩ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የሕግ ባለሙያው ጠጋቡ ተናግረዋል። አክለውም፣ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በአጠቃላይ ኃይልን የመጠቀም ብቸኛ መብት የተሰጠው ለመንግሥት ብቻ መሆኑን አመልክተዋል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲከላከሉ መረጃ በማሳወቅ እና ሐሳባቸውን በማካፈል ረገድ መንግሥት ቢሠራ የሚደገፍ ነው ብለዋል። በአንጻሩ ከማስታጠቅ አኳያ ግን የፀጥታ መደፍረሱን አይለውጠውም ባይ ናቸው።

ነዋሪዎችን የማስታጠቅ ሂደት ቢኖር እንኳ፣ ኅብረተሰቡን እያጠቃ ያለው ኃይል ራሱን የቻለ የውትድርና ሥልጠና የወሰደ እና በቂ ትጥቅ የታጠቀ እንደመሆኑ መጠን የፀጥታ መደፍረሱን ሊያከረው ይችላል ይላሉ።

በዋናነት ግን በክልሉ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እየሆኑ ያሉ ዜጎችን ደኅንነት የሚፈታ የክልል መዋቅርን ማሻሻል ዋናው የመንግሥት ሥራ እንዲሆን የሕግ ባለሙያው ጠይቀዋል። አያይዘውም፣ የጥፈት ቡድኑን በወቅቱ በመግታት የአካባቢውን ሰላም ማረጋገጥ ካልተቻለ፣ ወደ ሌሎች ቦታዎች የሚሸጋገርበት ሂደት በመኖሩ፤ ከዚህም ሳይሻገር ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ እንዲዘረጋለት አሳስበዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች