የመዋቅር ጥያቄና ውዝግቡ

0
2341

በኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫ የክልል፤ የዞን እንዲሁም የወረዳ እንሁን ጥያዎች ሲነሱ ይስተዋላል። በአማራ ክልል፤ በቤንሻንጉል ክልል፤ በደቡብ ክልል፤ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ወቅቶች የመዋቅር ይገባኛል ጥያቄዎች ይነሳሉ።

ታዲያ በየጊዜው የሚነሱት የክልል እንሁን ጥያቄዎች በአንዳንዶቹ በኩል ትክክል ናቸው የሚል አስተያየት ሲነሳ፤ በሌላ ጎን ደግሞ የለም! ከሕገ መንግሥቱ ጀምሮ ስህተት ነው የሚል ሙግት ይደመጣል። ይህም ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አከራካሪ ጉዳይ ሆኗል።

የመዋቅር ጥያቄ የአንዱ ምላሽ ማግኘት፤ የሌላኛው መዘግየት እንዲሁም መታገድ፣ ጥያቄ በሚያቀርቡት አካላት ቅሬታን እያሳደረ ይገኛል። በኢትዮጵያ በየአቅጣጫው የሚገኙና የመዋቅር ጥያቄ የሚያቀርቡ አካላት ቅሬታ የሚያነሱት የአንዱ ጥያቄ ተመልሶ የሌላኛው ምላሽ አለመሰጠት እኩልነት የተናጠበው ተግባር ስለሆነ ነው ባይ ናቸው።

ከዚህ በፊት የተነሱ የተወሰኑት የክልልም ሆነ የዞን እንሁን ጥያቄያቸው የይሁንታ ምላሽ የተሰጣቸው ሲሆን፤ አንዳንዶች ደግሞ ጥያቄያቸውን በመሰንዘር ላይ ይገኛሉ፡: የክልልነት ይገባኛል ጥያቄው በተለይም በደቡባዊ የኢትዮጵያ ክፍል አሁንም እንደቀጠለ ነው።

ይሁን እንጂ፣ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችና ተግባራዊነታቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው እያመዘነ መሆኑን የዘርፉ ምሁራንም የየበኩላቸውን አስተያየት እየሰጡ ነው።

በተለያዩ ወቅቶች የተነሱትና በመሰንዘር ላይ ያሉ “ክልል፤ ዞን፤ ልዩ ወረዳ” እንሁን የሚሉ ጥያቄዎች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የሚያመዝን ይመስላል የሚሉት የፖለቲካ ተንታኝ ሱራፌል አያሌው ናቸው። እንደ ምሁሩ ገለጻ ከሆነ፤ የመዋቅር ጥያቄው ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚልቀው ለማስተዳደር እንዲመች በክልል መዋቀሩ ተመራጭ ሆኖ ሳለ፤ መዋቅሩን በሚመሩት አካላት የወገንተኝነት አሰራር ሚዛን ስለሚደፋ አገርን ከማሰብ ይልቅ ብሔር ተኮር የመሆን እድል እየሰፋ ስለመጣ ነው።

ሱራፌል ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ከሆነ፤ ይህ ጥያቄ አንዳንዴ በተለይም በክልል መካከል ለዘረኝነት ብሎም ለጎጠኝነት መስፋፋት መንስኤ ሳይሆን እንዳልቀረ ነው። ኢትዮጵያ ባለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንገብጋቢውና እልባት ለማምጣት የሚበጀው፣ የመዋቅር ጥያቄ ከማንሳት ይልቅ ብሔርን ተኮር አድርጎ እየተስፋፋ ያለው የእርስ በእርስ ጦርነት መነሻው መከፋፈል መሆኑን መገንዘብ ነው ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ።

የመዋቅር መበራከትና ተከታይ ፈተናዎቹ
ከዚህ በፊት ጥያቄያቸው የተመለሰላቸው ቦታዎች ከጅምሩ እስከ ይሁንታው ድረስ በርካታ ውዝግቦች እንዳሳለፉ ይነገራል። በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ ይስተናገዳሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩ የክልልነት ይገባኛል ጥያቄዎች ደም መፋሰስንና ህልፈተ ሕይወትን እንዲሁም የንብረት ውድመትንም አስከትለዋል።

ክልሎች በአዲስ መልኩ ከተዋቀሩ በኋላም ነዋሪዎች በርካታ ችግሮች ሲጋረጡባቸው ይስተዋላል። ለአብነትም አዲሱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ ነዋሪዎች፣ ክልሉ በቅርቡ የተመሠረተ መሆኑን ተከትሎ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ተንሰራፍተውባቸዋል።

በክልሉ በተጠቃለሉት ዞኖች ስር የሚገኙ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ፤ ለውሃ መሠረተ ልማት፤ ለትምህርት መሣሪያ እጥረት፤ ለምግብ እና ለሌሎች በርካታ ችግሮች ተጋላጭ ሆነዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ሌሎች በአማራ፤ በቤንሻጉል ጉምዝ ክልል እንዲሁም በኦሮሚያ ክልል በተደረጉ የዞን መዋቅሮች ቀላል የማይባሉ ውጣ ውረዶች በነዋሪዎች ላይ ተረማምደዋል።

በተለያዩ ወቅቶችና ቦታዎች ክልል፣ ዞን እንዲሁም ወረዳ መሆን ይገባናል የሚሉ አካላት ላይ እስከ ሞት ድረስ ጉዳት ተስተናግዷል። በጉዳዩ ዙሪያ የሚነሱ ጥያቄዎችንም ባለድርሻ አካላት የይሁንታ አጸፋቸውን መንፈጋቸው እንዲሁም ከብዙ ተደጋጋሚ ጥያቄ በኋላም ለአንዳንድ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠታቸው ይታወቃል።

ይሁንና የአንዱ ጥያቄ የይሁንታ ምላሽ ማግኘት፣ “እኛ በምን እናንሳለን” በሚል መፈክር የሌላኛውን የመዋቅር ይገባኛል ጥያቄ ይበልጥ ሲያበረታታ ተስተውሏል። ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ለዘመናት የተደጋገመ ጥያቄ ሲቀርብበት የነበረው የሲዳማ የክልል እንሁን ጥያቄ ይሁንታ ከተቸረው በኋላ የጉራጌ ሕዝብ የክልል እንሁን ፍላጎት ንሯል።

የጉራጌ ሕዝብ የክልል እንሁን ጩኸት ሲዳማ ክልል መሆኗ ከተፈቀደላት ጉራጌ ጥያቄው የማይስተናገድበት ምክንያት አይኖርም የሚል ነው። የጉራጌ ሕዝብ የክልል እንሁን ጥያቄ ውጤት እንዲያመጣና ክልል ለመሆን እንደማያንስ ከሚያስረዱበት መካከል፣ ከዚህ በፊት የክልልነት ጥያቄያቸው ይሁንታ ካገኙት የሚያንስ አለመሆኑን የወረዳውን ብዛት በመጥቀስ ነው።

ለአብነትም ‹የጉራጌ ሕዝብ የክልል ጥያቄና ጩኸት› በሚል በተሰየመው የነዋሪዎች ድምጽ ማራመጃ ቡድን፣ “ሀረር ክልል ሆኖ የተዋቀረው በዘጠኝ ወረዳዎች ሲሆን፤ ጉራጌ በአዲስ አወቃቀር 16 የሚጠጉ ወረዳዎች እያሉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ለምን አይሰጥም። ጉራጌ ክልልነት ይገባዋል ደግሞም ትግላችን ይቀጥላል።” የሚል ሐሳብ ይገኛል።

በሌላ በኩል፣ በክልልነት ከተዋቀረ ስምንት ወራትን ያስቆጠረው አዲሱ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ያሉ ነዋሪዎች ሕይወታቸውን ከማጣት ጀምሮ የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ፈተና እንደሆነባቸው ይናገራሉ።

ከተፈተኑባቸው ጉዳዮች መካከልም በተማሪዎች በኩል የሚስተዋለው የትምህርት ግብዓት አለመሟላት ተጠቃሽ ነው። በክልሉ የሚገኙ ተማሪዎች ሊፈታ ያልቻለ የመጽሐፍ እጥረት እንዳለባቸው በተደጋጋሚ ይናገራሉ። በተለይም የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ከዚህ ቀደም “ምን አንብበን እንፈተን። ምንም መጽሐፍ የለንም” ሲሉ ተናግረው ነበር።

መምህራን በበኩላቸው፣ ደመወዝ ስላልተከፈላቸው ላለማስተማር መደምደማቸውን ተከትሎ ተማሪዎች የትምህርት ገበታቸውን ለመከታተል ያልቻሉበት አጋጣሚ ተስተውሏል። አዲስ በተዋቀሩ ክልሎችና ዞኖች በዜጎች ላይ ተጋርጦ የሚስተዋለው የውሃ ችግርም ሌላኛው አቤቱታ ነው።
በቅርቡ የተዋቀረው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ነዋሪዎች የውሃ ችግር ሰለባ መሆናቸውንም፣ 12 ዓመታት የዘገየው የቦንጋ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ጨምሮ በሌሎች ከተሞች ያለው የንጹሕ ውሃ አቅርቦት ችግር እንዲፈታ ክልሉ በግንቦት ወር 2014 ለፌዴራል መንግሥት ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።

የክልልነት ይሁንታ ጠቃሚ ነውን?
በየወቅቱ የክልል፤ ዞን እንዲሁም የወረዳ እንሁን የሚሉ የመዋቅር ጥያቄዎች ይነሳሉ። ይሁን እንጂ የውሳኔው ውጤት ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ።

ከጥቅሙ ጉዳቱ አመዝኗል የሚሉት የመዋቅር ጥያቄውን ገዢው መደብ ለወንበር ማግኛ እየተጠቀመበት መሆኑን በማንሳት ነው። ገዢው መደብ ወንበር ላይ ተቀመጠ እንጂ፣ ችግር የመፍታት እድል አልፈጠረም የሚሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ተመራማሪ ውሂበእግዜር ፈረደ (ዶ/ር) ናቸው።

የፌዴራሊዝም ስርዓትን ሰበብ በማድርግ ሥልጣን ላይ ለመውጣት የሚቃትቱ ምሁራንና የፖለቲካ አራማጆች ‘‘ማንነትህ ተነክቷል ተነስ‘‘ በማለት ሕዝቡን እያነሳሱ እንደ ትልቅ መሣሪያ ከመጠቀማቸው በዘለለ፤ በመዋቅር ደረጃ ሚዛን የደፋ ለውጥ አልታየም ነው ያሉት።

ገዢው መደብ ሕዝቡን በዚህ፣ “ማንነትህ ተገፍቷል ተነስ” በሚል ኩትኮታ የራሱን ወንበር ከማመቻቸት የተሻገረ የፌዴራሊዝም ትክክለኛ ሂደትን የሚጠቀም የለም ነው ያሉት ውሂበእግዜር።

‹‹አሁን አሁን እንደሚስተዋለው ከሆነ፤ ክልል መሆን ለሕዝብ ጠቃሚ ሳይሆን ጎጂ የመሆን አዝማሚያው የበረታ ይመስላል። የክልል እንሁን ጥያቄ የሚያነሳው ሁሉ ወንበር ፈላጊና ሕዝብ መጣጭ ነው።›› የሚሉት ውሂበእግዜር፤ በኢትዮጵያ የሚስተዋለው የመዋቅር ጥያቄ ለገዢው እንጂ ለሕዝቡ ምንም ጠቃሚ አለመሆኑን ተናግረዋል። በመሆኑም ጥቅም ሊኖረው የሚችለው ገዥው መደብ ለሥልጣን መዥጎድጎዱን ቸል ሲል ነው ሲሉ አሳስበዋል።

ሲዳማ በክልልነት ከተዋቀረ ወዲህ በመሠረተ ልማት፤ በሕዝብ አስተዳደር እና በሌሎች በርካታ ነገሮች ለውጥ ዐሳይቷል ሲባል ይደመጣል። ይሁን እንጂ፣ እንደ ፖለቲካ ተንታኞቹ ገለጻ ከሆነ፤ ሲዳማ ክልል በሚባልበት ደረጃ ላይ አይገኝም።

የክልልነት ይሁንታን ካገኙት መካከል ሲዳማ ክልልን ብዙዎች ተጠናክሯል፤ ለምቷል እንደሚሉት አይደለም የሚሉት ውሂበእግዜር፤ በምልከታቸው ግን ሲዳማ ክልል እንደተዳከመ እንጂ ለምታ እንዳላዩ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

የፖለቲካ ተንታኙ ኢዛና ዘመንፈስ፣ ፌዴራሊዝምና አንቀጽ 39 በሚል ጽሑፋቸው ጉዳዩን አንስተዋል። በዛም ላይ ሲጠቅሱ፤ ምንም እንኳን አንቀጽ 39 በዋነኛነት የሚያትተው፤ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ካለፈው ታሪካቸው የወረሱትን አሉታዊ የእርስ በርስ ግንኙነቶች ደረጃ በደረጃ እያረሙ አገራዊ ወንድማማችነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን መገንባት እንዲችሉ ለማድረግ ያለመ ግብ እንዳለው ቢሆንም፤ አብዛኞቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን ለየራሳቸው ጠባብ ፍላጎት መሳካት በሚያመች መልኩ ሊተረጉሙት ሲሞክሩ ይስተዋላሉ ሲሉ አስቀምጠዋል።

ለአሁኗ ኢትዮጵያ የሚሻለው…?
ኢትዮጵያ በተለይም ከዓመታት ወዲህ ዜጎቿ እርስ በእርስ ባላንጣ የሆኑበት ደረጃ ላይ ደርሳለች። “ድር ቢያብር አንበሳ ያሥር” እንዲሉ በቀደሙት ጊዜያት ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ቆመው ሌሎች የውጭ ጠላቶችን ሲመክቱ እንጂ፣ አሁን እንደሚስተዋለው አድዋን እየዘመሩ ወገን በወገን ላይ የተነሳበት አሳፋሪ ተግባር እንዳላስተናገዱ ታሪክ ይዘክራል።

ውሂበእግዜር በበኩላቸው፣ ፌዴራሊዝም ስርዓት ከመምጣቱ በፊት ኢትዮጵያ በታሪኳ የአሁኑን ዓይነት የእርስ በርስ ጦርነት ታይቶባት አይታወቅም ብለዋል።

በኢትዮጵያ እርስ በርስ መገዳዳል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረ ክስተት ነው የሚሉት ውሂበእግዜር፤ ይህም የመነጨው “የእኛ” የሚል የተገነጠለ አስተሳሰብ ከመጣ ወዲህ ነው።

በመሆኑም፣ በአንድ ሕዝብ መካከል ክፍፍል መፍጠሩ አሁን ላይ ላለችው ኢትዮጵያ የሚመች እንዳልሆነ ነው ውሂበእግዜር ያስገነዘቡት። ለአብነትም ለኢትዮጵያዊነት ማእከል ይሆናል ተብሎ የነበረው ደቡብ ክልልም እየተቆራረጠ መሆኑን የጠቀሱት ውሂበእግዜር፤ በዚህ ደግሞ የሚገኘው ትርፍ እርስ በርስ መገዳደል፤ መከፋፈልና ጎሳ መለየት ነው ይላሉ።

ኢትዮጵያን አሁን ካለችበት ችግር ለማውጣት በዚህ ወቅት የመዋቅር ጥያቄ አንገብጋቢ ሊሆን እንደማይገባም ተጠቅሷል። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ለተነሱ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ምላሽ መሰጠቱን ተከትለው ብዙ ጥያቄ የሚያቀርቡና በማቅረብ ላይ ያሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች አሉ።

ይሁን እንጂ፣ ኢትዮጵያን አሁን የሚጠቅማት በአራቱም አቅጣጫ የመዋቅር ጥያቄ ማንሳት ሳይሆን፤ በአንድነት ሆኖ በማበር የውጭ ጠላቶችን መመከት ነው። ካልሆነ ግን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚም ክልል እየበዛ በሄደ ቁጥር ተከትሎ ለሚመጣው የበጀት ፍላጎት መሟላት መልስ መስጠት እንደሚያዳግት ነው የተነሳው።

ሁሉም በየተራ የመዋቅር ጥያቄ ሲያነሳ፣ የአንድ አገር ሕዝብ ከውጭ እንደመጣ እንደባዳ እንዲተያይ በር ይከፍታል ሲሉም ስጋታቸውን ገልጸዋል። በመሆኑም፣ የመዋቅር መብዛት በጋራ ተሁኖ የሚፈጠረውን ጠንካራ የኢኮኖሚ ለውጥና የማኅበራዊ ትስስር እንዲሁም ጠንካራ የፖለቲካ አደረጃጀት ቢያደናቅፍ እንጂ ምኞትን እውን ሊያደርግ አይችልም ሲሉ ውሂበእግዜር ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

ሕጉና የመዋቅር ጥያቄ
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 መሠረት ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰንና እስከ መገንጠል ያለው መብቱ በማናቸውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ መሆኑ፤ ቋንቋውን የማሳደግና ባህሉንና ታሪኩን የመግለጽ፤ የማዳበር፤ የማስፋፋትና የመንከባከብ ሙሉ መብት እንዳለው የሕግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የመዋቅር ጥያቄ የሚያነሱ የማኅበረሰብ ክፍሎችም በመጀመሪያ ደረጃ ጥያቄአቸውን የሚያነሱት ሕገ መንግሥቱን ትራስ በማድረግ ነው። በየወቅቱ ለሚነሱት የክልል፣ ዞን ብሎም ልዩ ወረዳ የመሆን ጥያቄዎች ሕጉ ፈቃደኝነት እንዳለው የሕግ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

የመዋቅር ጥያቄ ራስን ከማስተዳደር፤ የራስን ጉዳይ በራስ ከመወሰን ጋር የተያያዘ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው የሚሉት በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ተመስገን ሲሳይ (ፕ/ር) ናቸው።

የፌዴራል መንግሥት፤ ክልሎች እንዴት ይዋቀራሉ እንዲሁም አከላለሉ ምን መምሰል አለበት የሚሉትን ነጥቦች ሕገ መንግሥቱ በተወሰነ መልኩም ቢሆን አስቀምጦታል ያሉት የሕግ መምህሩ፤ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን መብቱ ያለምንም ገደብ የተቀመጠ መሆኑ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ተደንግጓል ብለዋል።

የራስን እድል በራስ መወሰንን በተመለከተ አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ ኹለት፣ ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ቋንቋውን የማሳደግ፤ ባህሉን የመግለጽ እንዲሁም ታሪኩን የመንከባከብ መብት እንዳለው ያስቀምጣል ይላሉ ተመስገን።

ይሁን እንጂ ሕጉ በትክክል ተፈጻሚነት የማያገኝበት ሁኔታ እንዳለም ተመላክቷል። እንደ ባለሙያው ገለጻ ከሆነ፤ ምንም እንኳ አንቀጽ 39 የጉዳዩን አግባብነት ቢደነግገውም፤ የመዋቅር ጥያቄው ምላሽ ሳይቸረው ለዓመታት መቆየትና ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ አካል አለመኖር በሰላማዊና ሕጋዊ ኹነት የሚፈታውን ጉዳይ መልኩን እንዲቀይር ምክንያት ሆኖታል።

በማኅበረሰቡ በኩል የሚነሱት የክልልነት ይገባኛል ጥያቄዎች በአንድ በኩል ተገቢነታቸውን የሚነቅፉ አካላት አሉ። ወዲህ ሕጉን ተንተርሰው ጥያቄያቸውን የሚያቀርቡ አካላት ደግሞ ትክክል ስለመሆናቸው አጥብቀው ይሞግታሉ።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረቻቸው የሕግ ምሁራን በበኩላቸው፣ ከሕጉ አንጻር በማኅበረሰቡ የሚነሳው ጥያቄ ትክክል መስሎ ቢታይም ሕገ መንግሥቱ ግን በአንቀጽ 39 ላይ የደነገገው ሕግ፤ ማስተዋል የጎደለውና እንከን የተሞላበት የብሔር ፌዴራሊዝምን የሚያበረታታ መሆኑን ይናገራሉ።

የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በባህሪውና በይዘቱ፣ ሊወጣውና ሊመልሰው የማይችል ጥያቄ የተሸከመና ያስተናገደ ይመስለኛል ይላሉ የሕግ መምህሩ ተመስገን። የመዋቅር ጥያቄያቸው ምላሽ ሳይቸረው ውሎ ሲያድር ቅሬታ የሚሰማቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ በሌላ ጎን ደግሞ ምላሽ አግኝቶም አስተዳደራዊ ፈተና የሚጋረጥበት ሁኔታ እንዳልጠፋ ይነገራል።

የመዋቅር ጥያቄ አቅርበው ምላሽ ተሰጥቷቸው በቅርቡ ክልል የሆኑ የሲዳማና አዲሱ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች፣ ከመሠረተ ልማት ጀምሮ በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው በተደጋጋሚ መናገራቸው አይካድም።

የሕግ መምህሩ እንዳሉት ከሆነ፤ የመዋቅር ጥያቄዎች እየተለጠጡ እና እየተሳቡ ሲመጡ የአስተዳዳር ጉዳዮች ምላሽ ሊሰጥበት ከማይቻልበት ደረጃ ሊያደርሱ እንደሚችሉ ይገመታል።

መንግሥት አንዳንድ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚያነሱትን የመዋቅር ጥያቄ ምላሽ ሰጥቶ ሌላኛውን ማዘግየቱ፣ በርካቶችን የእኩልነት መብታቸው እንዳልተከበረላቸው ዓይነት ስሜት ሲፈጥርባቸው ይስተዋላል።

የሕግ መምህሩ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ጉራማይሌ ነገሮችን እናያላን ብለዋል። ‹‹በተለይም የክልል፤ የዞን እንዲሁም የልዩ ወረዳ እንሁን ጥያቄ በተለያዩ ቦታዎች ይነሳሉ። መንግሥት ፖለቲካው የከበደ ሲመስለው ለአንዱ ፈቅዶ ለአንዱ ደግሞ የሚከለክልበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰው፤ አንዱን ከልክሎ ለሌላው የሚፈቅድ የሕግ ማዕቀፍ ደግሞ የለም ባይ ናቸው።

ምንም እንኳ መንግሥት ለጉዳዩ ምላሽ ካስቀመጠው የሕግ ድንጋጌ አንጻር፣ ለመዋቅር ጥያቄ የሚሰጠው መልስ በተለይም ራስን ከማስተዳደር፤ ከእኩልነት ደረጃ ሲመዘን ክፍተት ይስተዋልበታል ብለዋል።

የአስተዳደር ጉዳይ ጊዜ ወስዶ በጉዳዩ ላይ ማሰብንና ከፍተኛ በጀትን የሚጠይቅ ነው ያሉት ተመስገን፤ ሕገ መንግሥቱ ላይ ቅድመ ሁኔታን ያላገናዘቡ እንከኖች ይስተዋሉበታል ሲሉ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here