የትጥቅ ፖለቲካ እና የኢትዮጵያ ፈተና

1
1901

ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ መጣ የተባለውን ለውጥ መጠሪያውን እንዲያገኝ ምክንያት ተደርገው ከተያዙ ነጥቦች ውስጥ አንደኛው፤ ከአገር ውጪ የነበሩና ‹መንግሥትን በትጥቅ ትግል ነው መጣል የምንችለው› ብለው የሚታገሉትን ‹ኑ› ብሎ ማስገባቱ ነበር። እነዚህም አካላት ሲገቡ ኢትዮጵያ ከአንጻራዊ ሰላም የተሻለ ሰላም ታገኛለች ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፤ በአንጻሩ አሁንም ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ይልቅ ምርጫቸውን የትጥቅ ትግል አድርገው የቀጠሉ ኃይሎች ጥቂት አይደሉም። ይህም ኢትዮጵያን አሁን ላይ በአያሌው እያስከፈላት ይገኛል። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን ጉዳይ መነሻ በማድረግና ባለሞያዎችን በማነጋገር ተከታዩን የሐተታ ዘ ማለዳ አሰናድቷል።

ኢትዮጵያ ከመንግሥት ጋር ቅራኔ ውስጥ በገቡ የታጠቁ ኃይሎችና አሸባሪዎች በእጅጉ እየተፈተነች መሆኑን የሚያመላክቱ የጸጥታ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ ቀጥለዋል። ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ይልቅ የትጥቅ ትግልን ምርጫቸው ያደረጉ የታጠቁ ኃይሎችም ተበራክተው፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ መምጣታቸውን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ በአራቱም ማዕዘን ሰላሟን እንድታጣና ዜጎቿ በጦርነትና በታጣቂዎች ጥቃት በግፍ የሚገደሉበትና የሚፈናቀሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል።

በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት ራሱን “የለውጥ መንግሥት” ብሎ ከሚጠራው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ጋር ቅራኔ ውስጥ የገቡ አካላት፣ መንግሥት በአሸባሪነት የፈረጃቸውን ጨምሮ በየአካባቢው የታጠቁ ኃይሎች ተፈጥረዋል። በዚህም በየአካባቢው የሰላማዊ ዜጎች ሞትና መፈናቀል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሄዶ ንጹሐን ዜጎች በጅምላ የሚገደሉበት ሁኔታ በኢትዮጵያ የተለመደ እየሆነ መጥቷል።

ንጹሐን ዜጎች በየአካባቢው በታጠቁ ኃይሎች ሲገደሉ፣ የታጠቁ ኃይሎች የሚንቀሳቀሱበትን አካባቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሲያሰፉ፣ በመንግሥት ተቋማትና ጸጥታ ኃይሎች ላይ አርምጃ ሲወስዱ፣ ሰዎችን ሲያግቱና እንዳሻቸው ሲዘርፉና ግብር ሲሰበስቡ ከድርጊታቸው የሚያስቆማቸው አካል በመጥፋቱ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትን ጨምሮ “መንግሥት የታጠቁ ኃይሎችን ጥቃት ማስቆም አልቻለም” የሚሉ ቅሬታ በመንግሥት ላይ በተደጋጋሚ ይቀርባል።

መንግሥት በአሸባሪነት ከፈረጃቸው በትግራይ ክልል ከሚንቀሳቀሰው ከሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና በኦሮሚያ ክልልና አጎራባች ክልሎች ከሚንቀሳቀሰው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ ከሚጠራውና በመንግሥት “ሸኔ” ተብሎ ከሚጠራው በተጨማሪ፤ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል፣ በጋምቤላ ክልል፣ በአፋር ክልልና በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች አሉ።

ባለፉት አራት ዓመታት ታጣቂ ኃይሎች ከፍተኛ ችግር ከፈጠሩባቸው አካባቢዎች ኦሮሚያ ክልልና ቤኒሻንጉል ጉምዝ በቀዳሚነት የሚጠቀሱ ቢሆንም፣ በሌሎች አካባቢዎችም አልፎ አልፎም ቢሆን የጸጥታ ችግር ሲፈጥሩ ይስተዋላል። በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች አንዳንዶቹ የረዥም ጊዜ ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ፣ መቀመጫቸውን ኤርትራ አድርገው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ስርዓትን ለመጣል የትጥቅ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ናቸው።

የታጠቁ ኃይሎች ውልደትና እድገት
ኢትዮጵያ በታሪኳ ፍላጎታቸውን በትጥቅ ትግል ወይም በኃይል እናሳካለን ብለው የነፍጥ ፖለቲካ የሚከተሉ ኃይሎች አያጧትም። በንጉሣዊያን ዘመን ከነበረው የአስተዳደርና የግዛት ጥያቄ እስከ አሁኑ ማለትም፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ተፈጥሯል እስከተባለለት 21ኛው ክፍለ ዘመን የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የአስተዳደር ጥያቄ አለን የሚሉ የታጠቁ ቡድኖችና አሸባሪ የሚባሉ ኃይሎች በኢትዮጵያ ምድር በየአካባቢው ተፈጥረዋል።

ኢትዮጵያ በዘውዳዊው የአስተዳደር ስርዓት ካስተናገደችው የነፍጥ ፖለቲካ ተላቃ ወደ ሰላማዊና ዴምክራሲያዊ የፖለቲካ ስርዓት ለመሸጋገር የምታደርገው ጥረት አሁንም በአሸባሪዎችና በታጣቁ ኃይሎች እየተፈተነ ነው። ታሪክ እንደሚያወሳው በንጉሣዊያን ዘመን የግዛት አስተዳደርን ለማስፋፋትና ለማስጠበቅ፣ የአንድ አካባቢ ግዛት አስተዳዳሪ ከሌላ አካባቢ የግዛት አስተዳደር ወይም የግዛት አስተዳዳሪን በሚቀናቀኑ ኃይሎች መካከል የትጥቅ ትግል የተለመደ መሆኑን ነው።

አሁን ላይ ያ ዘመን አልፎ ዓለም ዴሞክራሲን እየተለማመደች የፖለቲካ አሰላለፉ ወደ ሰላማዊ ፉክክር የተሸጋገረ ቢሆንም፣ ዴሞክራሲን በወጉ ተለማምደዋል የተባሉ አገራት ሳይቀሩ የነፍጥ ፖለቲካን በመረጡ አሸባሪዎችና ታጣቂ ኃይሎች ይፈተናሉ። የአፍሪካ አገራት ደግሞ በእጅጉ በአሸባሪዎችና የትጥቅ ትግል በመረጡ ኃይሎች ይፈተናሉ።

ኢትዮጵያም በአሸባሪዎችና የነፍጥ ፖለቲካ ምርጫቸው ባደረጉ የታጠቁ ኃይሎች ከሚፈተኑ የአፍሪካ አገራት መካከል አንዷ ነች። ኢትዮጵያ ከዘውዳዊው ስርዓት ማብቃት በኋላ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን እየተላመደች ቢመስልም፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንከተላለን ከሚሉት መንግሥታት ጋር ቅራኔ ውስጥ የገቡ አካላት ወደ ኋላ እየጎተቷት ይገኛሉ።

ከጥንት ከጠዋቱ አባዜ ያልተላቀቀው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለፉት 30 ዓመታት ዴሞክራሲዊ መንግሥት ነኝ በሚለው፣ በቀድሞው ኢሕአዴግ በአሁኑ ብልጽግና ስርዓት እና ከስርዓቱ ጋር ቅራኔ ውስጥ በገቡ የታጠቁ ኃይሎች ፍትጊያ እየዋዠቀ ነው። ኢትዮጵያን ከኹለት ዐስርት ዓመታት በላይ ከገዛው ከኢሕአዴግ ስርዓት ቅራኔ ውስጥ የገቡ፣ መቀመጫቸውን በጎረቤት አገራት በተለይም ኤርትራ አድርገው ከስርዓቱ ጋር ተፋጠው ከ20 ዓመት በላይ የቆዩ ከሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ይልቅ የትጥቅ ትግል መርጠው የቆዩ ኃይሎች ነበሩ።

በወቅቱ ኢትዮጵያን በማስተዳደር ላይ የነበረው ኢሕአዴግ ከኤርትራ ጋር የነበረው ግንኙነት በጎሪጥ የሚተያዩ ባላንጣዎች እንጂ፣ ከዓመታት በፊት አንድ አገር የነበሩና በታሪክ አጋጣሚ ኹለት አገር የሆኑ የአንድ አገር ክፋይ ጎረቤታሞች አይመስሉም ነበር። ከኢሕአዴግ ጋር ቅራኔ ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ኃይሎች የኢትዮጵያንና የኤርትራን የጎሪጥ መተያየትን እንደ አጋጣሚ ተጠቅመው ኤርትራን መሸሸጊያቸው አድርገው በወቅቱ የነበረው የኢሕአዴግ ስርዓትን ለመጣል በመረጡት የትጥቅ ትግል ውስጥ ቆይተዋል።

በኢሕአዴግ ላይ የበረታውን ሕዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ በ2010 ወደ ሥልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በወቅቱ በውጭ አገር የሚገኙ፣ የስርዓቱ ተፎካካሪ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎችና በኤርትራ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩትም ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ መቀመጫቸውን በተለያዩ የውጭ አገራት አድርገው የትጥቅ ትግልና ሰላማዊ ትግል ሲያደርጉ የነበሩ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።

በኢሕአዴግ ስርዓት ተቋውሞ ያላቸውና ስርዓቱን በትጥቅ ትግል ለመቀየር ዓላማቸው አድርገው በኤርትራ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች፣ በስርዓቱ ላይ የሚነሳው ተቃውሞ ቀስ በቀስ ሕዝባዊ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ ኢሕአዴግ ከወደቀ በኋላ ሰላማዊ ትግል እናደርጋለን ብለው ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።

በወቅቱ በኤርትራ በርሃ መሽገው የትጥቅ ፖለቲካ ትግል ላይ የነበሩ እንደ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ፣ የጋምቤላ ሕዝቦች ነፃነት ንቅናቄ (ጋሕነን)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ)፣ የአፋር ነጻ አውጪ ግንባር – አጉጉም፣ የጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ ግንቦት ሰባትና ሌሎችም ተፎካካሪ የፖለቲካ ኃይሎች የጠቅላይ ሚኒሰትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው የሚታወስ ነው።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የገቡ መቀመጫቸውን በውጭ አገራት አድርገው በትጥቅ ትግልና በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች በመንግሥታዊ ለውጡ ተስፋ አድርገው ሰላማዊ ትግል ለማድረግ መወሰናቸውን በወቅቱ ወደ ኢትዮጵያ በገቡበት ወቅት ገልጸው ነበር።

አንዳንዶቹ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩትን የፖለቲካ ኃይሎች ጭምር ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እናደርጋለን ብለው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ሲንቀሳቀሱ፣ ከአንዳንዶቹ ውስጥ ራሳቸውን ነጥለው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ የተጠናከረ የትጥቅ ትግል ውስጥ ገብተዋል። በዚህም ከመንግሥታዊ ለውጡ በፊት በኢትዮጵያ ከነበረው የታጣቂዎች ጥቃትና እንቅስቃሴ የገዘፈ ጥቃት ከለውጡ በኋላ ተስፋፍቷል።

“ለውጥ”ያጎለበታቸው ታጣቂዎች
በኢሕአዴግ ስርዓት ተቃውሞ የነበራቸው የፖለቲካ ኃይሎች አልፎ አልፎ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ስርዓቱን የመገዳደር ሙከራዎች ሲያደርጉ ነበር። ይሁን አንጂ፣ ኢሕአዴግ የትጥቅ ትግል የመረጡትን ኃይሎችን ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ላይ የነበሩ ተፎካካሪዎቹን ሳይቀር ከኢትዮጵያ እንዲሰደዱ አድርጓል።

የኢሕአዴግ ስርዓት ከአገር እንዲሰደዱ ባደረጋቸው የፖለቲካ ኃይሎችና በሕዝብ ግፊት ከተቀየረ በኋላ፣ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የፖለቲካ ኃይሎች አሰላላፍ ሰላማዊ ይሆናል ተብሎ ቢጠበቅም እንደተጠበቀው ሳይሆን ቀርቶ ከመንግሥታዊ ለውጡ በኋላ በየአካባቢው አመጽ የሚፈጥሩ የታጠቁ ኃይሎች ተፈጥረዋል።

በለውጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የገቡ የፖለቲካ ኃይሎች በኹለት የሚከፈሉ ሲሆን፣ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩና ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ላይ የነበሩ መሆናቸውን ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉና በሚሠሩበት ተቋም ምክንያት ሥማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የሰላምና ደኅንነት ተመራማሪና ባለሙያ ይገልጻሉ።

የሰላምና ደኅንነት ተመራማሪው እንደሚሉት የፖለቲካ ኃይሎቹ ወደ አገር ቤት ሲገቡ በትጥቅ ትግል ላይ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎች ለኹለት ተሰንጥቀው ግማሹ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሲያቀኑ፣ ግማሾቹ በኤርትራ በርሃ የነበረውን የትጥቅ ትግል በኢትዮጵያ በርሃዎች ማድረግን መርጠው የትጥቅ ትግል ውስጥ መቆየታቸውን ያስታውሳሉ።

ከመንግሥታዊ ለውጡ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና በትጥቅ ትግል ከተከፋፈሉ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል፣ ኦነግ አንዱ ሲሆን፣ የኦነግ አመራሮች ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ቢገቡም በኤርትራና በአገር ቤት የነበሩ የኦነግ አባላት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በሚል የትጥቅ ትግል ውስጥ ገብተዋል።

የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ መንግሥትን ከሚገዳደሩ ቀዳሚ የታጠቁ ኃይሎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በጋምቤላ ክልል፣ በአማራ ክልልና በደቡብ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ጥቃት እየፈፀመ የሚገኝ በአሸባሪነት የተፈረጀ የታጠቀ ኃይል ነው።

ታጣቂ ኃይሉ በኦሮሚያ ክልል በተደጋጋሚ በሚፈጽማቸው ግድያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች፣ ሕጻናትና አቅመ ደካሞችን ጨምሮ ንጹሐን ዜጎችን በጅምላ የገደለ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞንና አጣዬ አካባቢ የሰሞኑን ጥቃት ጨምሮ በተደጋጋሚ ከባድ ጥቃት በዜጎች ላይ እየፈጸመ ነው።

በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚንቀሳቀሰው ራሱን የጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጌሕዴን) ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል፣ በኢሕአዴግ ስርዓት እንደሌሎቹ የታጠቁ ኃይሎች ሁሉ በኤርትራ በርሃ የነበረ ሲሆን፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ኃይሎች መካከል አንዱ ነው። ይህ ታጣቂ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ ላለፉት አራት ዓመታት፣ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለይም በመተከልና በካማሺ ዞኖች በንጹሐን ዜጎች ላይ በፈጸመው ጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሲገደሉ፣ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።

በጋምቤላ ክልል የሚንቀሳቀሰውና ራሱን የጋምቤላ ነጻነት ግንባር (ጋነግ) ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል፣ አልፎ አልፎ ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ጥቃት እየፈጸመና የጸጥታ ስጋት ሆኖ ይገኛል።

በቅርቡ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ የጋምቤላ ነጻ አውጭ ግንባርና የጉምዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ጌሕዴን) ታጣቂ ኃይሎች ጥምረት ፈጥረው በጋምቤላ ከተማ በከፈቱት ጥቃት በንጹሐን ዜጎችና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ላይ የሞትና አካል ጉዳት ማድረሳቸው የሚታወስ ነው።

የሦስቱ ታጣቂ ኃይሎች ጥምረት ነው የተባለለት ኃይል በቅርቡ የጋምቤላ ክልል መቀመጫ በሆነው ጋምቤላ ከተማ ከፈጸመው ጥቃት በተጨማሪ፣ በኦሮሚያ ክልልና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የተቀናጁ ጥቃቶችን ሲፈጽሙ ነበር።

በአፋር ክልል ራሱን የአፋር ነጻ አውጪ ግንባር (አጉጉም) ብሎ የሚጠራ ታጣቂ ኃይል፣ በሰሜን ኢትዮጵያ በፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ሕወሓት ጋር ወግኖ ሲዋጋ እንደነበር መንግሥት ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

መሠረታቸውን በአማራ ክልል ያደረጉ እንደ ቅማንት ነጻ አውጪ ሠራዊትና የአማራ ሕዝባዊ ሠራዊት (ፋኖ) ያሉ የታጣቁ ኃይሎች በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሲሆን፣ ከመንግሥት ጋር ካላቸው ቅራኔ ውጪ በክልሉ ሕዝብ ላይ ጥቃት መፈጸማቸው አይሰማም። በተለይ ራሱን ፋኖ ብሎ የሚጠራው የታጠቀ ኃይል መንግሥት ጋር በጥርጣሬ የሚተያይ ኃይል ይሁን እንጂ፣ በመንግሥት ከሚቀርብበት ውንጀላ ውጪ በሕዝብ ላይ ጥቃት መፈጸሙ እስከ አሁን አልተሰማም።

እነዚህ ሁሉ የታጠቁ ኃይሎች ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀሱት፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስተዳደር ከመጣ በኋላ መሆኑ፣ ከአራት ዓመት በፊት ተስፋ ተጥሎበት የነበረውን ኢትዮጵያን ከችግር የማውጣት ጉዞ ከድጥ ወደ ማጡ ያደረገ መሆኑን የሰላምና ደኅንነት ተመራማሪው ይገልጻሉ።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የነበሩት መቶ አለቃ ታሪኩ በቀለ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ በኢትዮጵያ አሁን የተፈጠረው የእርስ በእርስ መገዳደልና የታጣቂ ኃይሎች መስፋፋት ሕወሓት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያዘጋጀው የቤት ሥራ ውጤት ነው ይላሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት በኢሕአዴግ የሥልጣን ዘመን መራሽ የነበረው ሕወሓት በተለይ አማራና ኦሮሞ እርስ በእርሱ እንዲገዳደል የዘራው የሐሰት የጥላቻ ዘር መኖሩን ያነሳሉ።

በተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች በኢትዮጵያ ታሪክ አሳዛኝ ድርጊት እየፈጸሙ ነው የሚሉት መቶ አለቃ ታሪኩ፣ በግለሰቦች ጥቅም የተነሳ የነጻ አውጪነት አባዜ ቀስ በቀስ ወደ ቡድንና ወደ ማኅበረሰብ ሰፍቶ ኢትዮጵያን ውስብስብ ችግር ውስጥ የከተተ ፈተና ሆኗል ሲሉ ያነሳሉ።

የሰላምና ደኅንነት ተመራማሪው በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በአሸባሪዎችና በታጣቂ ኃይሎች እንድትፈተን እድል የከፈተው፣ በሕዝብ ትግል የመጣው የለውጥ መንግሥት በአግባቡ መምራት አለመቻሉን ተከትሎ በሕወሓት የተዘራው የጥላቻ ፖለቲካ በየአካባቢው በመፈንዳቱ ነው ይላሉ። የታጠቁ ኃይሎች ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በኋላ የተቋጠረው የጥላቻ ፖለቲካ ቀስ በቀስ እየፈነዳ መምጣቱን የሚገልጹት ባለሙያው፣ የፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቱ ለታጠቁ ኃይሎች ጥቃት መስፋፋት በር መክፈቱን ያነሳሉ።

መንግሥት የታጠቁ ኃይሎች በተለያዩ አካባቢዎች ላለፉት አራት ዓመታት በዜጎች ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ማስቆምና ዜጎችን ከጥቃት መከላከል አለመቻሉ ደግሞ ችግሩን የከፋ እንደሚያደርገው ተመራማሪው ይገልጻሉ።

በተለያዩ አካባቢዎች በታጣቂ ኃይሎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች ባለመቆማቸው፣ የመንግሥት ኃይሎች የታጣቂ ኃይሎች ተባባሪ ናቸው ተብለው ይተቻሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚነሳው የታጠቁ ኃይሎች በየጊዜው አቅማቸው ሲጎለብት የመንግሥት ሰዎች ከጀርባ ድጋፍ ያደርጋሉ የሚሉ ክሶች ሲሆኑ፣ በዚህ ረገድ ቤንሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን በነበረው የጸጥታ ችግር ከክልል እስከ ፌዴራል የሚገኙ የመንግሥት አመራሮች ሲሳተፉ እጅ ከፈንጅ መያዛቸው የሚታወስ ነው።

ምን ይበጃል?
በኢትዮጵያ የሽብርተኝነት እና የኃይል አሰላላፍ የመረጡ የታጠቁ ኃይሎች መበራከት በየአካባቢው ከፍተኛ የጸጥታ ችግር እየፈጠረ ይገኛል። የታጠቁ ኃይሎች በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች የዜጎች ሞት፣ የንብረት ውድመት እና አለመረጋጋት ከተከሰተ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል።

ወታደራዊ ባለሙያው መቶ አለቃ ታሪኩ እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ አሁን ያጋጠመውን የታጠቁ ኃይሎች ጥቃትን ለማስቆም፣ በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት አገር የማረጋጋትና በታጣቂዎች እጅ የሚገኙ አካባቢዎችን ማስተዳደር እንዳለበት ይመክራሉ። አገር የማስተዳደር ሥልጣን የተሰጠው መንግሥት ከዳር እስከ ዳር የኢትዮጵያን ሰላም ማስጠበቅ እንዳለበት የሚገልጹት መቶ አለቃ ታሪኩ፣ አገር የማረጋጋትና የታጠቁ ኃይሎችን ጥቃት ካስቆመ በኋላ የታጠቁ ኃይሎች የሚያነሷቸውን ችግሮች በጋራ ቁጭ ብሎ መወያየትና የጋራ መፍትሔ መፈለግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ይህን ለማድረግ መንግሥት በቅድሚያ የታጠቁ ኃይሎችና በአሸባሪነት የፈረጃቸው ኃይሎች በስፋት የሚንቀሳቀሱባቸውን አካባቢዎች፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እንዲተዳደሩ ማድረግ እንዳለበት መቶ አለቃ ታሪኩ ይመክራሉ። በጣም አስቸጋሪ የሆኑ አካባቢዎችን ለይቶ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር በወታደራዊ ኃይል እንዲተዳደሩ ማድረግ የዜጎችን ሞት ለማስቀረትና የታጠቁ ኃይሎችን እንቅስቃሴ ለመግታት ሁነኛ መፍትሔ መሆኑንም ይመክራሉ።

በአገር ውስጥ የጦር ማሠልጠኛ ከፍቶ የሚሠለጥንና እንዳሻው የጦር መሣሪያ የሚያንሸራሽር ኃይል በተፈጠረበት ሁኔታ፣ መንግሥት አለ ለማለት የሚያጠራጥር ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያነሱት መቶ አለቃ ታሪኩ፣ መንግሥት ያለውን አቅም አደራጅቶ የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ አስፈትቶ ወደ ሰላማዊ ስምምነት ማምጣት አለበት ይላሉ።

መንግሥት የታጠቁ ኃይሎችን ጥቃት ማስቆም የሚችል አቅም እንዳለው የሚያምኑት መቶ አለቃ ታሪኩ፣ እንደ አገር ያሉ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ተነጋግሮ ለመፍታት በቅድሚያ መንግሥት ተመጣጣኝ በሆነ ወታደራዊ እርምጃ ትጥቅ ማስፈታት እንዳለበት ተናግረዋል።

የሰላምና ደኅንነት ተመራማሪው በበኩላቸው፣ አሸባሪዎችንና የታጠቁ ኃይሎችን ትጥቅ ማስፈታትና ወደ ሰላማዊ ንግግር ማምጣት፣ የተቀናጀ ጥረትና አቅም የሚጠይቅ መሆኑን ይገልጻሉ። ለአሸባሪዎችና ለታጠቁ ኃይሎች መፈጠር ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች እንደ መንስኤ ሊጠቀሱ ይችላሉ የሚሉት ተመራማሪው፣ በቀዳሚነት ችግሩን ለማስቆም ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት በአብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገራት የተለመደ ተሞክሮ መሆኑን ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ችግር ለመፍታት መንግሥት በቅድሚያ ከተመጣጣኝ ወታደራዊ እርምጃ ጎን ለጎን ሰላማዊ ጥረቶችን በማድረግ፣ ለንግግርና ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር እንደሚጠበቅበት ተመራማሪው ይጨምራሉ።

ትኩረቱን ሰላምና ደኅንነት ላይ አደርጎ የሚሠራ አኮርድ (African Centre for the Constructive Resolution of Disputes -ACCORD) የተባለ ተቋም፣ “በአፍሪካ ውስጥ ሽብርተኝነትን እና ጽንፈኝነትን መዋጋት” በሚል ርዕስ በ2017 ባወጣው ጥናታዊ ጽሑፍ፣ በአፍሪካ ውስጥ ሽብርተኝነትን እና ጽንፈኝነትን ለመከላከል በዋናነት አፋጣኝ ወታደራዊ ምላሾች ተሰጥተዋል ይላል።

ወታደራዊ ምላሾች በአንዳንድ ሁኔታዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ወታደራዊ እርምጃ የሰው ሕይወት መጥፋት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ የጅምላ መፈናቀልና የመሠረተ ልማት ውድመት እንደሚያስከትል በአፍሪካ አገራት ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን ያትታል። ወታደራዊ ምላሽ ምንም እንኳን የተጠቀሱትን ችግሮች ቢያስከትልም፣ ለአፍሪካ አገራት ውጤታማ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ሊሆን እንደሚችል የአኮርድ ጥናት ይመክራል።

ለሽብርተኝነት እና ለኃይለኛ ጽንፈኝነት አስተዋጽኦ የሚያደርጉ ምክንያቶች ውስብስብ መሆናቸውን የሚገልጸው ጥናቱ፣ ችግሩን ለመቋቋም ከሚቻልበት መንገድ በተጨማሪ ውስብስብ ነገሮችን ይፈጥራል ይላል። በመሆኑም የአሸባሪዎችንና የታጠቁ ኃይሎችን ጥቃት ለመግታት የሰውን ስቃይ የሚቀንስ አማራጭ መንገዶችን ማሰስ አስፈላጊ መሆኑን ይጠቁማል።

የአኮርድ ጥናት እንደሚመክረው፣ በለስላሳ የኃይል እርምጃዎች የሽብርተኝነትን እና የአመጽ ጽንፈኝነትን አደጋዎች በብቃት ለመፍታት ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ቢሆንም አስፈላጊ መፍትሄ ነው። በውይይት እና በሽምግልና ላይ የሚደረጉ ሙከራዎች ሽብርተኝነትን እና ጽንፈኝነትን ለመከላከል ቅድሚያ የሚሰጣቸው ወሳኝ እርምጃዎች መሆናቸውንም ጥናቱ ይመክራል።

ሌላኛው ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ አገራት የተለያዩ ጥናቶችን በማካሄድ የሚታወቀው ‹አፍሮ-ባሮሜትር› የተሰኘ የጥናት ተቋም፣ “አደገኛ ጽንፈኝነት በአፍሪካ” በሚል ርዕስ ከኹለት ዓመት በፊት ባወጣው ጽሑፍ፣ አደገኛ ጽንፈኝነት በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ባሉ መንግሥታት እና ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ የደኅንነት ስጋት ይፈጥራል ይላል።

ባለፉት ኹለት ዐስርት ዓመታት ውስጥ በአሸባሪ ቡድኖች የሚሰነዘሩ ብሔራዊ አመጾች ድንበሮችን እያቋረጡ ውስብስብ ክልላዊ ግጭት ፈጥረዋል የሚለው የአፍሮባሮሜትር ጥናት፣ አሸባሪዎች በሚፈጠሩበት ወቅት መንግሥት እንቅስቃሴያቸውን መገደብ መቻል እንዳለበት ያሳስባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 193 ሀምሌ 9 2014

አስተያየት

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here