በጎንደር፣ በወራቤና በጂንካ አካባቢ በተከሰተው ግጭት የተፈጸሙ ወንጀሎች የምርመራ ግኝት ይፋ ተደረገ

0
1285

አርብ ሐምሌ 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ጋር በመተባበር በሚያዚያ ወር በጎንደር እና በወራቤ ሀይማኖትን መሰረት አድርጎ እንዲሁም በጂንካና አካባቢው ማንነትን መሰረት አድርጎ በተከሰተው ግጭት የተፈጸሙ ወንጀሎችን የምርመራ ግኝት ይፋ አደረገ፡፡

የምርመራ ግኝቱን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ፍቃዱ ጸጋ እና በፌዴራል ፖሊስ በወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ኦፕሬሽን መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ሙልኢሳ አብዲሳ በጋራ በመሆን ለሚዲያዎች አብራርተዋል፡፡

በሚኒስቴሩ ይፋ የተደረገው መሉ የምርመራ ግኝት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

በጎንደር ሚያዝያ 18 ቀን 2014 በአንድ የእስልምና ኃይማኖት አባት ሥርዓተ-ቀብር ላይ ለቀብር የሚሆን ድንጋይን ሰበብ በማድረግ በተከሰተው ግጭት በ20 ሰዎች ላይ ሞት፣ በ100 ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንዲሁም በ1 መስጊድ ላይ ሙሉ በሙሉ ውድመት እና በ8 መስጊዶች ላይ ከባድ ጉዳት እንዲሁም በ2 መስጊዶች ላይ ደግሞ ቀላል ጉዳት መድረሱን ሙልኢሳ አብራርተዋል፡፡

ሙሊሳ በማብራሪያቸው ፖሊስ የ250 ሰዎችን የምስክርነት ቃል ተቀብሏል፤ ሌሎች ከወንጀል አፈጻጸሙን የሚያስረዱ የተለያዩ ማስረጃዎችን አሰባስቧል፡፡

በዚሁም መሰረትም 509 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል በወንጀል ድርጊቱ የተሳተፉ ሰዎችን የመለየት ሥራ ተሰርቷል፡፡ በዚህም መሰረት የተደራጀውን የምርመራ መዝገብ ለዐቃቤ ሕግ አስረክበናል ያሉ ሲሆን፤ ዐቃቤ ሕግም የክስ መመስረት ሂደቱን ጀምሯል ብለዋል፡፡

በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ጎንደር የተፈጸመውን የሀይማኖት ግጭት መነሻ በማድረግ ወንጀሉን ከህዝብ ጋር ሆኖ ከመከላከል ይልቅ፤ አንዳንድ ጽንፈኛ ኃይሎች በጎንደር መስጊድ ተቃጥሏል ውጡና የክርስቲያን ቤቶችን አቃጥሉ በማለት በከተማው ማይክራፎን ይዘው በመቀስቀስ በ4 የኦርቶዶክስ እንዲሁም በ3 የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያኖች ላይ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ ሲሆን፤ ጉዳት አድራሾቹ የሞተር ሳይክልና ገጀራዎችን በመጠቀም በ2 ሰዎች ላይ ሞት፣ በ79 ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት እንዲሁም 12 በሚሆኑ በግለሰብና በንግድ ቤቶች ላይ ከባድ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል ሲሉ ሙልኢሳ በመግለጫቸው አመላክተዋል፡፡

ጂንካ ከተፈጠረው ችግር ጋር በተያያዘም የአሪ ብሄረሰብ ዞን እንሁን በሚል የከተማውን ከንቲባ ጨምሮ ሻንካ /ወጣት/ የሚል ቡድን በማደራጀት ቅስቀሳ በማድረግ ማንነትን መሰረት ያደረገ ጥቃት በአማራ ተወላጆች ላይ ፈጸመዋል ያሉት መልኢሳ፤ በተጨማሪም 247 ሚሊዮን ብር የሚገመት የንብረት ጉዳት ደርሷል፤ 1150 የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል ብለዋል፡፡

ሙልኢሳ አክለውም የህግ ማስከበር ሂደቱን የፌዴራል ፖሊስ ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር በመሆን እንደሚቀጥል ተናግረው፤ ህብረተሰቡም ወንጀል ፈጻሚዎችን ከመደበቅ ይልቅ በማጋለጥ ወንጀልን በመከላከሉ ረገድ ከህግ አካላት ጋር በመሆን በጋራ እንዲሰራ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የክስ ሂደቶችን እና ጥልቅ የሆኑ የምርመራ ሥራዎችን በተመለከተም በፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሚኒስቴር ዴኤታ የሆኑት ፍቃዱ ጸጋ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ በጂንካ ማንነትን መሰረት ያደረገው ጥቃት ሚያዚያ 1 ቀን መፈጸሙን አውስተው፤ ነገር ግን ጉዳዩ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ዝግጅት ሲደረግበት መቆየቱን የምርመራ ግኝቱ እንደሚያመላክት ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴር ዴኤታው አክለውም፤ በደቡብ ኦሞ ዞን የተፈጸመው የወንጀል ምርመራ መሰረት የሚያደርገው ጂንካና አራት የአሪ ብሄረሰብ ተወላጆች የሚኖሩባቸው ወረዳዎች ላይ የተፈጠረውን ግጭት መሆኑን አንስተዋል፡፡

በአሪኛ ሸከን ወይም ወጣት ተብሎ የተደራጀ ቡድን፤ በደቡብ ኦሞ ዞን ከሚኖሩ 16 የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች ውስጥ እኛ ለብቻችን የጂንካን ከተማን ጨምሮ አራት ወረዳዎችን በመያዝ ዞን መሆን አለብን፤ የሚል ዓላማን በማንገብ ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በመፍጠር በወረዳውም በዞኑም ያሉ የመንግስት ኃላፊዎች ጭምር ያደራጇቸው ወጣቶች፤ የዞን ጥያቄያችን የማይቀበለው የአማራ ብሄር ተወላጅ ነው፤ ስለዚህ በመጀመሪያ የአማራ ተወላጅን ነው ከአካባቢው ማስወጣት ያለብን የሚል ይዘት ያለው ቅስቀሳ አድርገዋል ሲሉ አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከመጋቢት 26 ቀን 2014 ጀምሮ የኑሮ ውድነትን ሰበብ በማድረግ የአማራ ነጋዴዎችን ሱቅና ቤት በመበርበር ተለያዩ ዕቃዎችን ወደ ማዘጋጃ ቤት ወስዶ በማከማቸት ሂደት ላይ ከቆዩ በሗላ፤ በተለይ በወረዳዎች ላይ ሚያዚያ 21 ቀን 2014 የሸከር ዋነኛ አደራጅ የነበረው ማቲያስ በአማረው ተገድሏል በማለት ወሬ በማናፈስ በጂንካ ደግሞ ሰልፍ እንዲኖር በማድረግ አስቀድመው በለዩት የአማራ ተወላጆች ቤት ላይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የምርመራ ግኝታችን ያመላክታል ብለዋል፡፡

በዚህ ጊዜ ወደ 144 የአማራ ተወላጆች ቤት ሙሉ በሙሉ መቃጠሉንና፤ 46 ቤቶች በድንጋይና በተለያዩ ቁሳቁሶች ጉዳት እንዲደርስባቸው መደረጉንም የገለጹት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ በተጨማሪም አንድ መስጊድ ተቃጥሏል፣ 232 የንግድ ድርጅቶች ተዘርፈዋል ጥቃቶቹም የተፈጸሙት በአማራ ብሄር ተወላጆችና በሌሎች የእነሱን መደራጀት አይደግፉም ያሏቸው ብሄሮች ላይ ነው ብለዋል፡፡

በሂደቱ 782 ተጠርጣሪዎችን ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ያዋለ ሲሆን፤ ከ782 ተጠርጣሪዎች ውስጥ በፌዴራል መንግስቱ ስልጣን ሥር ይወድቃሉ የተባሉ 142 ተከሳሾች ላይ በፍትህ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ ክስ ተመስርቶባቸዋል። ሌሎቹ በዞን በወረዳ እንደየስልጣናቸው ክስ እንዲመሰረትባቸው መደረጉንም ፍቃዱ በመግለጫቸው አብራርተዋል፡፡

በወንጀሉም ላይ የጂንካ ማዘጋጃ ቤት ሀላፊ፣ የጂንካ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ሀላፊ፣ የጂንካ ከተማ ፋይናንስ ጽ/ቤት ሀላፊ፣ የደቡብ አሪ ወረዳ አስተዳደር፣ የጂንካ ዩኒቨርስቲ መምህርና የተለያዩ የመንግስት ሰራተኞች የተሳተፉበት ከመንግስት ፋይናንስ እየወጣ ለወጣቶቹ አበል በተለያየ መንገድ የተከፈለበት ሂደት እንደነበር የምርመራ ግኝታችን ያሳያል ብለዋል፡፡

ምርመራው በደረሰበት ልክም የመንግስት አስተዳደር ላይ ያሉ ሰዎች በወንጀሉ ውስጥ በመሳተፍ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ተረጋግጧል ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ እስከዛሬ ከመረመርናቸው በተለየ ከ8 ሰዎች ውጭ ሌሎቹ በቁጥጥር ሥር ውለዋል፤ በተጨማሪም ምንም የሰው ህይወት ሳይጠፋ 8 ሰዎች ላይ ብቻ የተለያያ ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል፡፡

“መከላከያ፣ የፌዴራል ፖሊስና ልዩ ኃይል በቶሎ መግባታቸው ከዚህ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ እንድንከላከልም አግዞናል” ያሉት ሚኒስቴር ዴኤታው፤ ይህ ጉዳት የደረሰውም አንዳንድ ወረዳዎች ላይ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር የለም በሚል አመራሮቹ በወንጀሉ ላይ በመሳተፋቸው የጸጥታ አካላት እንዳይገቡ በማድረጋቸው ነው ብለዋል፡፡

አጠቃላይ በነበረው ሂደት 142 ክስ የተመሰረተባቸው ሰዎች ላይ የፌዴራል አቃቤ ህግ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አርባ ምንጭና አካባቢው በሚያስችለው ችሎት ላይ ክስ መስርቷል፤ ተጠርጣሪዎቹ ካሉበት ቦታ ወደዚያ ተዛውረው ክሳቸውን የሚከታተሉ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ አካባቢ ከተከሰተው ግጭት ጋር ተያይዞ 247 ሚሊዮን ብር የዋጋ ግምት ያለው ንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በተጨማሪም ሚያዚያ 18 ቀን 2014 በተፈጥሮ ሞት የሞቱትን ታላቅ የእምነት አባት ሸክ ከማል ለጋስ የቀብር ሥርዓታቸውን ለመፈጸምና፤ በጎንደር ከተማ ቀበሌ 8 አካባቢ በሚገኘው ወደ ሀጅ ኤልያስ መካነ መቃብር የእስልምና እምነት ተከታዮች መካነ መቃብር ላይ አስከሬናቸውን ለማኖር ወዳጅ ዘመዶቻቸው ወደ ቦታው በሄዱበት ከቀኑ 7 ሰዓት ከ30 ላይ፤ በተለምዶ ቀሀ ወንዝ ከሚባለው ድንጋይ በማውጣ መቃብሩን ለማመቻቸት በሚደረግ ሂደት ውስጥ አስቀድሞ በአጎራባችነት የነበረ የኦርቶዶክስ አማኞች የሚያመልኩበት አበራ ጊዮርጊስ የሚባል ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ የአብነት ተማሪዎች ከዚያ በፊት የድንበር ችግር በመኖሩ ድንጋዩን የሚወስዱት ድንበር ሊያካልሉ ነው በሚል ድንጋይ መወራወር ይጀምራሉ፤ በዚህ ሂደት አንደኛ ተከሳሽ የሆነው የቤተክርስቲያኑ ጥበቃ ጥይት ወደ ህዝቡ በመተኮስ ቦንብ እንዲወረወር በማድረጉ ምክንያት በዚያን ቅጽበት ብቻ ሦስት ሰዎች ሂይወታቸው አልፋል ብለዋል፡፡

ግጭቱ ተስፋፍቶ ወደ ከተማው በመሰራጨቱ በተከታታይ ቀናት የተለያዩ ግጭቶች መኖራቸውን የምርመራ መዝገባችን ያስረዳል ያሉት ፍቃዱ፤ መጀመሪያ የጸጥታ ሀይሉ 509 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ 310 ወንጀል ውስጥ መሳተፋቸውን የሚያሳይ ማስረጃ ባለመገኘቱ ወዲያው እንደተለቀቁ ተናግረዋል፡፡

199 ቀድመው የተያዙና 17 ከዚያ በኋላ የተያዙ ሰዎችን አንድ ላይ በማድረግ በ216 ሰዎች ላይ የጊዜ ቀጠሮ እየተጠየቀ በአጭር ጊዜ ውስጥ 121ቹ ወንጀል ስለመፈጸማቸው ማስረጃ ባለመኖሩ እንዲለቀቁ ተደርጎ በአጠቃላይ 77 የተያዙ፣ 62 ያልተያዙ ሰዎች ላይ ምርመራ ሲጣራ ቆይቷል፡፡

መጨረሻ 250 የሰው ምስክሮች ከተሰበሰበቡ በሗላ በፍርድ ቤት ክስ ሊያስመሰርትባቸው በሚችል 103 ሰዎች ከኹለቱም ዕምነቶች ተለይተው ክስ ተመስርቶባቸዋል፤ 69 ተይዘው የታሰሩ 34 ደግሞ ተፈላጊዎች ሲሆኑ፤ 24 የእስልምና እምነት ተከታዮች፤ 79 ደግሞ የክርስትና ዕምነት ተከታዮች ናቸው ያሉት ፍቃዱ፤ ከእነዚህም ውስጥ 3ቱ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ግጭቱ ባህሪው ቀድሞ ታስቦበት ያልነበረ በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የተፈጠረ ነገር ግን የሰፋ፤ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች የእስልምና ዕምነት ተከታዮችን የማምለኪያ ቦታ እና የንግድ እንዲሁም የመኖሪያ ቤቶችን በመምረጥ ጉዳት በማድረስ፤ የእስልምና ዕምነት ተከታዮችም ደግሞ አጸፋው የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች የንግድ ቦታ ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን የምርመራ ግኝታችን ያመለካክታልም ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው፡፡

አያይዘውም 20 ሰዎች ከኹለቱም ዕምነት በግጭቱ ለሞት ተዳርገዋል፣ ከ100 ሰዎች በላይ የአካል ጉዳት ደርሷል፣ 60 ሚሊዮን ግምት ያለው ንብረት ውድሟል፤ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች በዕምነቱ በኩል ያቋቋሟቸው ኮሚቴዎች ደግሞ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳት ደርሷል ብሎ ያመጣ ሲሆን፤ በከተማ አስተዳደሩ በኩል ግን 60 ሚሊዮን የሚል እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በስልጤ ዞን ከተፈጸመው ወንጀል ጋር በተያያዘ ወራቤ ሳንቁራ ወረዳ በአለም ገበያ ከተማና መንዝር ጦር በርበሬ ወረዳ በተባሉ አካባቢዎች የተፈጸመ ወንጀል በሚያዝያ 18 ቀን 2ዐ14 ጎንደር የተከሰተውን ወንጀል ተከትሎ ማታ 2፡00 ሰዓት ከሰላት በሗላ አንድ አሰጋጅ እና አንድ ኡስታዝ “ጎንደር የፈሰሰው ደም የናንተ ደም ነው፤ ጎንደር ሙስሊሙን የገደለው ክርስቲያን ነው ስለዚህ እንዲኖሩ መፍቀድ የለብንም” ብለው የቀሰቀሱ በመሆኑ በማግስቱም ከቀኑ7፡00 ሰዓት ላይ በነበረው ሰላት ተመሳሳይ ቅስቀሳ በማድረጋቸው በትምህርት ቤቶችም በመቀስቀስ መስጊድ ተቃጥሏል ብሎ በማስወራት ወደ ብጥብጥ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡

በወራቤ ከተማ ቅዱስ ሩፋኤል በተባለ ቤተክርስቲያን ላይ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ በመሄድ ቤንዚል እና የተለያዩ ስለታማ ነገሮችን በመያዝ ውድመት መጀመራቸውን የወራቤ ዩንቨርስቲ የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች ቤተክርስቲያናችን ተቃጠለ ብለው በመምጣታቸው ብጥብጡ መባባሱን በአካባቢው ባለው መስጊድም ሊቃጠል ነው የሚል የአዛን ድምጽ በማሰማት የሰው ቁጥር እንዲመጣ ተደርጎ ቤተክርስቲያኑ መቃጠሉን የምርመራ መዝገቡ ያሳያል፡፡

ከላይ በተጠቀሱት ሌሎች ወረዳዎችም ጭምር 4 የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ቤተክርስቲያን ንዋየ ቅዱሳትን ጨምሮ እንዲሁም 3 የፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያናት መቃጠላቸውን እንዲሁም የዋጋ ግምቱ ወደ 46 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ንብረት መውደሙን የምርመራ ግኝቱ ያመላክታል፡፡

ሚኒስትር ዴዔታው እንደገለጹት ከሆነም፤ የምርመራ መዛግብቱን መሰረት በማድረግ በ97 ሰዎች ላይ ክስ ተመስርቷል፡፡

በመጨረሻም ሚኒስቴር ዴኤታው በኹሉም ግጭት በተፈጸመባቸው ቦታዎች ውስጥ የጸጥታ መዋቀሩ ገብቶ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አንስተው፤ በቅርቡ በወለጋ ግንቢ አካባቢ የተፈጸመው ወንጀልን ጨምሮ መቻሬን እና ጋንቤላ የተፈጸመው ወንጀል ላይ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።

ወንጀል ሀይማኖትንና ብሄርን የማይወክል መሆኑን በመገንዘብ በየደረጃ ያለው የመንግስት አደረጃጀትና ህብረተሰብ ትብብር ሊያደርግ ይገባል ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

(የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here