መነሻ ገጽዜናየእለት ዜና“በመዲናዋ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዞናል የታክሲ አገልግሎት ተግባራዊ ሊደረግ ነው”- የአዲስ አበባ ትራንስፖርት...

“በመዲናዋ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዞናል የታክሲ አገልግሎት ተግባራዊ ሊደረግ ነው”- የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ

👉ከመስመር ውጭ በጫኑና ከታሪፍ ውጭ ባስከፈሉ 74 ሺህ የታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ የቅጣት እርምጃ ተወስዷል

አርብ ሐምሌ 8 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአዲስ አበባ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ዞናል የታክሲ አገልግሎት ተግባራዊ ሊደረግ መሆኑ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

ቀደም ሲል ሲተገበር የነበረው የታክሲ ዞናዊ ስምሪት ላይ የተሳፋሪው እና የታክሲዎች አለመመጣጠን ክፍተት መኖሩ በጥናት ማረጋገጡን የገለጸው ቢሮው፤ ዳግም ተግባራዊ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር እጸገነት አበበ በተለይ ለኢቢሲ ሳይበር ሚዲያ ተናግረዋል።

በዞናዊ የታክሲ ሥምሪት አገልግሎት አተገባበር ላይ ከታፔላ ውጭ አገልግሎት የመስጠት ችግር እንዳለ ማስተዋላቸውን የገለጹት ኃላፊዋ፣ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች 490 በሚደርስ የሰው ኃይል ሲደረግ የነበረውን የቁጥጥር ሥርዓት በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

አንዳንድ ቦታዎች ላይ ረዘም ያሉ የታክሲ ሰልፎች እንዳሉ የተናገሩት ኃላፊዋ፤ ይህን ክፍተት ለመሙላት የትኛው ቦታ ላይ ምን አይነት የታክሲ ዞናዊ ሥምሪት ማድረግ እንደሚያስፈልግ በጥናቱ ተለይቶ ተግባራዊ ሊደረግ ነው ብለዋል።

ኃላፊዋ ምሽት እንዲሁም ቅዳሜና እሁድ ከታሪፍ ውጭ የሚያስከፍሉ ታክሲዎች መኖራቸውን በክትትል አረጋግጠናል ያሉ ሲሆን፤ የቁጥጥር ሥርዓቱን ጠንካራ በማድረግ አሰራሩን በጣሱት ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

ከተመደቡበት መስመር ውጭ በመጫንም ሆነ ከታሪፍ ውጭ ባስከፈሉ 74 ሺህ የታክሲ አሽከርካሪዎች ላይ የቅጣት እርምጃ መወሰዱንም ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።

ባለፉት 3 ወራት የታክሲ ዞናል የትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ቁጥጥር እንዲያደርጉ ተመድበው የመልካም አስተዳደር ችግር የፈጠሩ 23 የቁጥጥር ሰራተኞች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ መስመሮች ላይ የቆርቆሮ ታፔላ ምርት ባለመኖሩ በወረቀት የተሰራ ታፔላ ዳሽቦርድ ላይ አድርገው ታክሲዎች የትራንስፖርት አገልግሎቱን እንዲሰጡ አሰራር መዘርጋቱንም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

በቀን ከ2 ሚሊዮን በላይ ለሚልቁ ሰዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጥ የሚነገርለት የአዲስ አበባ ታክሲ ትራንስፖርት አገልግሎት፤ የቁጥጥር ሥርዓቱ ግን ውስን በሆነ የሰው ኃይል የሚከናወን በመሆኑ ለአስተዳደር አመቺ አለመሆኑን ኃላፊዋ ተናግረዋል።

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች