መነሻ ገጽሐተታ ዘ ማለዳእንከን የማያጣው ኮንዶሚኒየምና ፖለቲካው

እንከን የማያጣው ኮንዶሚኒየምና ፖለቲካው

አንዳች እንከን እና ችግር ተለይቶት የማያውቀው የኮንዶሚኒየም ቤቶች ጉዳይ፣ ከሰው ንክኪ ርቆ በቴክኖሎጂ ቢታገዝ ደኅና ይሆናል የሚል እምነት ተጥሎበት ነበር። ሆኖም ግን ያም ከሰዎች ንክኪ የማያልፍ እንደሆነ በቅርቡ የተደረገውን የኮንዶሚንየም ቤቶች የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ተከትሎ ለመረዳት ተችሏል። ያም ብቻ አይደለም፤ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን የቤት ችግር ይቀርፋል ተብሎ ከ15 ዓመት በላይ የዘለቀው ይኸው የኮንዶሚኒየም ልማትና የአሠራር ስርዓቱ በየጊዜው አቧራ የሚያስነሳ ጉዳይ ሆኗል። ጉዳዩም ማኅበራዊ አገልግሎትና የቤት ልማት ከመሆን አልፎም የፖለቲካ አጀንዳነትን ተላብሷል። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ በቅርቡ የተካሄደውን ዕጣ አወጣጥና የነበረውን ክስተት በማንሳት ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሐምሌ 1/2014 ያወጣውን የ20/80 እና የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ቀድሞ በተሠራ መጭበርበር ምክንያት ውድቅ አድርጓል። ከተማ አስተዳደሩ ለ25 ሺሕ 491 ቆጣቢዎች ያወጣውን የ20/80 እና 40/60 ቤቶች እጣ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈው የዕጣ ማውጫ ሲስተም ላይ ማጭበርበር ማጋጠሙ ካረጋገጠ በኋላ ነው የወጣው ዕጣ ውድቅ መደረጉ ይፋ የሆነው። ይህም ከሆነ በኋላ ጉዳዩ ከመንግሥት እስከ ሕዝብ መነጋጋሪያ አጀንዳ ሆኖ ቀጥሏል።

በየጊዜው እንከን የማያጣውና ከውዝግብ ያልወጣው የኮንዶሚኒየም ልማትና ለተጠቃሚዎች የማስተላለፍ ሂደት፣ ከዚህ በፊት የሚነሱበትን የተዓማኒነትና ግልጽነት ጥያቄ ያስቀራል የተባለለት በቴክኖሎጂ የተደገፈ የዕጣ ማውጫ ሲስተም ሌላ ችግር ይዞ መጥቷል። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን የቤት ችግር ለመፍታት ተብሎ 1997 ወዲህ መልማት የጀመረው ኮንዶሚኒየም ከተጀመረበት ጊዜ እስከ አሁን ድረስ በርካታ ችግሮች የሚነሱበት ሲሆን፣ በየጊዜው ከተማዋን የሚመሩ ባለሥልጣናት መጠቀሚያ ሆኗል የሚሉ ክሶች ከቆጣቢዎችና ከከተማዋ ነዋሪዎች ይሰማል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችና የኮንዶሚኒየም ቤት ቆጣቢዎች የሚያነሷቸው ችግሮች ዘርፈ ብዙ ናቸው። በየጊዜው የሚመጡ ባለሥልጣናት መጠቀሚያ መሆኑ ላይ የሚነሳውን ክስም የሚያረጋግጡ ባለቤት አልባና ከሕግ አግባብ ውጪ የተላለፉ በርካታ የጋራ መኖሪያ ቤቶች መኖራቸውን ከተማ አስተዳደሩ ራሱ ይፋ ማድርጉ የሚታወስ ነው።

ታዲያ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን እንከን አያጣሽ የሆነው የኮንዶሚኒየም ቤት ጉዳይ እስካሁን የተፈጠሩ ችግሮች በአግባቡ ሳይፈቱና መተማማን ሳይፈጠር፣ ሐምሌ 1/2014 በቴክኖሎጂ ተደግፎ የወጣው ዕጣ መጭበርበር፣ በኮንዶሚኒየም ላይ የሚታየው ብልሹ አሠራር አሁንም መቀጠሉን ማሳያዎች ናቸው የሚሉ ትችቶች ከሰሞኑ በርትተዋል።

በቴክኖሎጂ የተደገፈው የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓት በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም ለ14ኛ ጊዜ እንዲሁም በ40/60 ፕሮግራም ለ3ኛ ጊዜ ተመዝግበው በመጠባበቅ ላይ ለሚገኙ 25 ሺሕ 491 ሰዎች መውጣቱ ተገልጾ ነበር። በኹለቱ የቤት ልማት ፕሮግራሞች በአግባቡ በመቆጠብ ለዕጣ ውድድር ብቁ ሆነው ከተገኙ 79 ሺሕ 794 ተመዝጋቢዎች መካከል፣ 18 ሺሕ 648ቱ በ20/80 የቤት ልማት ፕሮግራም እንዲሁም 6 ሺሕ 843ቱ ደግሞ በ40/60 ፕሮግራም የቆጠቡ ነበሩ።

ይሁን እንጂ፣ ዕጣ ወጣላቸው የተባሉት ሰዎች ውስጥ በዕጣው እንዲሳተፉ ከተመረጡት ውጭ ሌሎች ተካተው በመገኘታቸውና የዕጣ ማውጫው ሲስተም በመጭበርበሩ ውድቅ ተደርገዋል።

ዕጣው ከወጣ በኋላ ውድቅ የተደረገባቸውን ኮንዶሚኒየም ቤቶች ለማጠናቀቅ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዕጣ ማውጣት ሥነ ስርዓቱን ባስጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር አስረድተው ነበር።

ዕጣው በወጣበት በአራተኛው ቀን መሰረዙ የተነገረለት በቴክኖሎጂ የተደገፈው የዕጣ ማውጣት ሂደት፣ ከዚህ በፊት በተከናወኑ የዕጣ ማውጣት ሂደቶች ላይ ይሰነዘር የነበረውን ቅሬታ ሙሉ በሙሉ በማስቀረት አስተማማኝነቱና ደኅንነቱ በተግባር ተሞክሮ የተረገጋጠ መሆኑን ሲገለጽ ነበር። የዕጣ ማውጫ ሲስተሙ የተጭበረበረ መሆኑ ከመገለጹ በፊት ግልጽነትን የሚፈጥር፣ ኃላፊነትና ተዓማኒነት እንዲኖር የሚያደርግና፣ ፍትሐዊነትንም ያሰፍናል ተብሎለት ነበር።

የዕጣ ሲስተሙ እክልና ውዝግቡ
በቴክኖሎጂ ሲስተም የተሞከረው የኮንደምኒየም እድለኞችን የመለየት ዕጣ በከተማ አስተዳደሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፣ ዋና ዓላማው ግልጽነትንና ፍትሐዊነትን ማረጋገጥ የነበረ ቢሆንም ገና ከመጀመሪያው ከሽፏል። በዕጣ ማውጫ ሲስተሙ ላይ አጋጥሟል በተባለው ማጭበርበር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዕጣ ብቁ ሆነው ለከተማ አስተዳደሩ ከተላለፉ የዕጣ ተሳታፊዎች ውጪ ሌሎች ሰዎች በዕጣው መካተታቸው አንዱና ሲስተሙ ቀድሞ የተመረጠለትን ለይቶ የሚያወጣ መሆኑ ዋና ዋና ግድፈቶች መሆናቸውን የሲስተሙን ችግር ለማጥናት የተቋቋመው ግብረ ኃይል ይፋ አድርጓል።

በዕጣ ሲስተሙ ላይ ያጋጠመውን ችግር የመረመረው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር እና የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሥማቸው ከዕጣው መስተጓጎል ጋር መነሳቱን ተከትሎ በየፊናቸው የሲስተሙን ችግር ይፋ አድርገዋል።

የዕጣ እክሉን ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ የመረመረው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛው (ዶ/ር)፣ በጉዳዩ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ሲስተሙ ተዓማኒነት የሌለው መሆኑን ተቋማቸው ባደረገው ማጣራት ማረጋገጡን ገልጸዋል። የዕጣ ማውጫ ሲስተሙ ፍትህን ያጓደለ ሲስተም ከመሆኑ ባሻገር፣ ሲስተሙ የመልማት ዓለም ዐቀፍ ስታንዳርዱን ያልጠበቀና ሦስቱን አካላት ማለትም አልሚውን፣ ተጠቃሚውን እና አረጋጋጩን አካላት ያላካተተ ነው ተብሏል።

አጣሪ ቡድኑ ባቀረበው ሪፖርት፣ አጠቃላይ ሲስተሙ ሙያዊ በሆነ መንገድ የተሠራ አለመሆኑን፣ ሁሉም በአንድ ሰው የተሠራ መሆኑ፣ የተተገበረው እጣ አወጣጥ ሶፍትዌር የተሻለ አማራጭ የነበሩትን ጭምር ያልተጠቀመና የመረጣው መንገድ ችግር ያለበት መሆኑ፣ የማበልጸግ ሂደቱ በሚከናወንበት ወቅት ከኢንተርኔት ጋር አክሰስ የተደረገ ሲሆን ይህም ፈፅሞ ተአማኒነቱን የሚያሳጣው መሆኑ፣ የተወዳዳሪዎች ዳታ እና ከባንክና ከቤቶች የተገኘው የአያያዝ ችግር ያለበትና ለቅየራ የተጋለጠ መሆኑ እንዲሁም ሲስተሙ የሚፈልገውን አካል እጣ እንዲያወጣ ተደርጎ የተሠራ መሆኑን ይፋ አድርጓል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበኩሉ በጉዳዩ ላይ ባለፈው ቅዳሜ በሰጠው መግለጫ፣ የሰጠሁት ምክረ-ሐሳብ ተግባራዊ ቢደረግና ሲስተሙ የደኅንነት ፍተሻ ቢደረግለት አሁን ያጋጠመው ችግር እንዳይፈጠር መከላከል ይቻል ነበር ብሏል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ጋር ተያይዞ ሥሙ በተደጋጋሚ በመጠቀሱ በሕዝብ ዘንድ ያለውን ብዥታ ለማጥራት ብሎ በሰጠው መግለጫ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ ማውጫ ስርዓት በማልማት ላይ በመሆኑ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጠው ለኤኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ለኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ በደብዳቤ ጠይቆ ምላሽ ሰጥቶ እንደነበር ገልጿል።

ሚኒስቴሩም በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የባለሙያ ቡድን አዋቅሮ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ እና ከሚመለከታቸው የቴክኒክ ባለሙያዎች ጋር የቀረበውን ሶፍትዌር በጋራ በመገምገም ምክረ ሐሳቦችን አቅርቦ እንደነበር አስታውቋል።
ለፍተሻ ጥቅም ላይ የዋለው ኮምፕዩተር ለሥራው የማይመጥን ስለሆነ በአስቸኳይ እንዲቀየር፣ ሲስተሙ ወደ ትግበራ ምዕራፍ ከሄደ በኋላ ከበተስጀርባ ሊኖሩ የሚችሉ ለውጦችን ኦዲት የሚያደርግ፤ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ፤ ለውጦችን መቆጣጠር የሚያስችል ስርዓት እንዲዘረጋ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥቶ ሚኒስቴሩ ምክረ ሐሳብ ሰጥቻለሁ ብሏል።

- ይከተሉን -Social Media

ሶፍትዌሩ ወደሥራ ከመግባቱም በፊት አስፈላጊው የደኅንነት ፍተሻ መደረግ እንዳለበት፣ በተለይም የሲስተሙን ደኅንነት እና አመርቂ ትግበራ ለማረጋገጥ ሲስተሙ በብሔራዊ ዳታ ማእከል ተጭኖ አስፈላጊው የደኅንነት፣ የጫና እና የአቅም ፍተሻ እንዲደረግለት፣ በሶፍትዌሩ ፍትሻ ወቅት እንደ መሠረታዊ ተግዳሮት የታየው ጉዳይ ሲስተሙ ምንም ዓይነት የግንባታ ሰነድ የሌለው መሆኑ፣ እነዚህ ሰነዶች በሌሉበት ሁኔታ ቀጣይ ማሻሻያዎችን ማድረግ አስቸጋሪ ከማድረጉም በላይ የሲስተሙን ሁለንተናዊ ደኅንነት ማስጠበቅ እንደማይችል ምክር ሰጥቼ የነበረ ቢሆንም ተግባራዊ አልተደረገም ሲል የድርሻዬን ተወጥቻለሁ ብሏል።

የዕጣ ማውጫ ሲስተሙ ላይ ከተነሱ በርካታ ችግሮች በላይ ከዕጣው መሰረዝ በኋላ የሚጣረሱ ቁጥራዊ መረጃዎች ተከስተዋል። አዲስ ማለዳ ከኮንዶሚኒየም ዕጣ መጭበርበር ጋር በተያያዘ የተለያዩ ተቋማት የሰጧቸውን ማስረጃዎች በአካል በመገኘትና ተጨማሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ ሞክራለች። በዚህም ከዕጣው መጭበርበር በኋላ ምርመራ ያደረገው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የሰጠው ማብራሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም ፍትሕ ሚኒስቴር ያወጡት መረጃ የተለያየ መሆኑን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር አደረኩት ባለው ምርመራ “ለውድድር ብቁ ናቸው ተብሎ የተገለጸው 79 ሺሕ ያህል ሰዎች የነበሩ ሲሆን፣ ሲስተሙ ግን በድብቅ ያዘጋጃቸው ሰዎች 172 ሺሕ ያህል ሰዎች ነበሩ።” ብለዋል። በአንጻሩ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ ሐምሌ 9/2014 በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከባንክ ለዕጣ ብቁ ሆነው ከባንክ ከተላኩ 79 ሺሕ የዕጣ ተሳታፊዎች በተጨማሪ 73 ሺሕ ሰዎች በዕጣ ማውጫ ሲስተሙ ተካተው ተገኝተዋል ማለታቸውን አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ ሰምታለች።

ከተማ አስተዳደሩና ከንቲባዋ 73 ሺሕ ሰዎች ለዕጣ ብቁ ያልሆኑና በዕጣው መሳተፍ የሌለባቸው ሰዎች በሲስተሙ ተካተው ተገኝተዋል ሲሉ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር 172 ሺሕ ብቁ ያልሆኑ ሰዎች በዕጣው እንዲካተቱ ተድርጓል ማለቱን ብዙዎች ልብ ባይሉትም የመረጃ መጣረሱ ከምክር ቤት እስከ ፍርድ ቤት ቀጥሏል።

ከከንቲባዋና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የመረጃ መጣረስ በተጨማሪ በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ እና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ሙሉቀን ሃፍቱ (ዶ/ር) ያለመከሰስ መብት እንዲነሳ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ሐምሌ 7/2014 በላከው ደብዳቤ “ለዕጣ ብቁ ናቸው ተብለው ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከተላኩ 79 ሺሕ ተመዝጋቢዎች በላይ ለዕጣው ብቁ ያልሆነ 73 ሺሕ ሰዎችን በድብቅ ወደ ኮምፕዩተር በመጫን የተጠቃሚዎችን ቁጥር ወደ 172 ሺሕ እንዲያድግ ያደረገ መሆኑ፣ ለዕጣው ብቁ ናቸው ተብለው ከሚመለከተው አካል ተረጋግጦ ከተላከው ዳታ ውጭ ሌላ ዳታ ማስገባት፣ መረጃ መጨመር፣ ማጥፋት፣ እንዲሁም ማስተካከል የሚያስችል እድል ለአልሚው በድብቅ የሚሰጥ መሆኑን ማረጋገጥ ተችሏል” ይላል። የፍትሕ ሚኒስቴርና የከንቲባዋ ቁጥራዊ መረጃ ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ለዕጣ ብቁ የሆኑት 79 ሺሕ ሰዎችና ለዕጣ ብቁ ሳይሆኑ በዕጣው ተሳትፈዋል የተባሉ 73 ሺሕ ሰዎች ሲደመር የሚመጣው ቁጥር የተባለውን ማለትም 172 ሺሕ ሳይሆን 152 ሺሕ ነው።

በዕጣ ማውጫ ሲስተሙ ላይ ማጭበርበር ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩት ሙሉቀን ሃፍቱና (ዶ/ር) ሌሎች ተጠርጣሪዎች፣ በፍትሕ ሚኒስቴር ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግና በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ የቀረበባቸው ክስ ፍትሕ ሚኒስቴር በከንቲባዋና በፍትሕ ሚኒስቴር በቀረበው ቁጥራዊ መረጃ ማለትም ለዕጣ ብቁ ያልሆኑ 73 ሺሕ ሰዎች ተካተዋል በሚል አይደለም። ይልቁንም 172 ሺሕ ሰዎች ባልተገባ መንገድ በመኖሪያ ቤት ዕጣ እንዲካተቱ አድርገዋል ተብለው ነው።

ለተሰረዘው ዕጣ ብቁ ያልሆኑ 172 ሺሕ ሰዎች ተካተው ተገኝተዋል ያለው የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ቢሆንም፣ ጠቅላይ ዐቃቢ ሕግ በምርመራ አረጋግጫለሁ ብሎ ያቀረበውን ቁጥር ለፍርድ ቤት አላቀረበም።

በሌላ በኩል በሲስተሙ ላይ ዕጣው በወጣበት ወቅትና ዕጣው ከተሰረዘ በኋላ የተሰጡ ማብራሪያዎች እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። ከሚጣረሱ መረጃዎች መካከል የዕጣ ማውጫ ሲስተሙ ቀደም ብሎ በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ይሁንታ ያገኘና በግል ተቋማት ታዛቢዎች ጭምር ታይቶ የተረጋገጠ ነው ተብሎ ነበር። ከዕጣው መሰረዝ በኋላ ሲስተሙ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ያልተረጋገጠና በግለሰቦች ግንኙነት ላይ የተመሠረተ ነው ተብሏል።

- ይከተሉን -Social Media

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙት ሙሉቀን ከመታሰራቸው በፊት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ድጋፍ እንዲሰጥ በዳብዳቤ ቢጠየቅም ምላሽ አልሰጠም ብለዋል። በዚህም ሙሉቀን የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ሹመቴ ግዛውን (ዶ/ር) ለማናገር ጥረት አድርገው ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።

የኮንዶምኒየም ዕጣ ውዝግብ ከዚህ በፊትም የነበረ ሲሆን፣ እንደማሳያ የካቲት 27/2011 ዕጣ የወጣባቸው ከ52 ሺሕ የሚጠጉ የ20/80 እና 40/60 መኖሪያ ቤቶች በተፈጠረው ውዝግብ የዕጣ ዝርዝር በጋዜጣ እንዳይታተም እስከመታገድ ደርሶ ነበር። በወቅቱ ዕጣ የወጣላቸው ሰዎች ዝርዝር እንዳይታተም የታገደው የኦሮሚያ ክልል መንግሥት ተቃውሞ በማሰማቱ ነበር። በወቅቱ ዕጣ የወጣላቸው 52 ሺሕ ቤቶች ጉዳይ በተነሳው ውዝግብ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዶም ነበር። ተቃውሞው በዋናነትም እጣ ከወጣባቸው ቤቶች መካከል በኦሮሚያ ክልል ይዞታ ውስጥ ገብተው የተገነቡ ቤቶች በመኖራቸው ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች አይገቡም የሚል ነበር።

የኮንዶሚኒየም ፖለቲካ
የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን የቤት ችግር ይቀርፋል ተብሎ ከ15 ዓመት በላይ የዘለቀው የኮንዶሚንየም ልማትና የአሠራር ስርዓቱ በየጊዜው አቧራ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው። ኮንዶሚኒየም ቤት ከእነ ችግሩ የቤት ልማት ከመሆን አልፎ የፖለቲካ አጀንዳ ከሆነ ሰነባብቷል።

በኮንዶሚኒየም ጉዳይ የሚነሱ ችግሮች ከአዲስ አበባ ኮንዶሚኒየም ቆጣቢዎች፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ እስከሚገኙ አርሶ አደሮች፣ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥት እስከ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ ከተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ መንግሥት ባለሥልጣናት በአወዛጋቢነቱ አሁንም የዘለቀ ነው።

የቤት ልማቱ በየጊዜው አዲስ አበባን በሚመሩ ከንቲባዎችና ባለሥልጣናት ፍላጎት የሚዘወር ነው የሚሉ ክሶች በተደጋጋሚ ከፖለቲከኞች እስከ ቆጣቢዎች ይነሳል። ይህን የሚያረጋግጡ ግኝቶች ደግሞ ከዚህ በፊት መገኘታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በ2013 ከተማ አስተዳደሩ በጥናት አረጋግጫለሁ ብሎ ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት 21 ሺሕ ቤቶች በሕገ ወጥ መንገድ ተላልፈው ተገኝተዋል።

በሕገ ወጥ መንገድ ተላልፈው የተገኙ 21 ሺሕ ቤቶች መኖራቸው የተረጋገጠው የቀድሞው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ አዲስ አበባን በሚመሩበት ወቅት ምርመራ እንዲደረግ በተለያዩ አካላት ግፊት ከተደረገ በኋላ ነበር። በወቅቱ ተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሳይቀሩ በሕገ ወጥ መንገድ የተላለፉ ኮንዶሚኒየሞችና የመሬት ወረራ መከሰቱን ሲገልጹ ነበር። የቀድሞው ምክትል ከንቲባ በጉዳዩ ላይ የተነሳውን ውዝግብ አስመልክቶ በግል የፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ በሕገ ወጥ መንገድ የተላለፈ ኮንዶሚኒየም አለመኖሩን ነበር የጠቀሱት። ይሁን እንጂ እርሳቸው ከምክትል ከንቲባነታቸው ከተነሱ በኋላ በተደረገው ጥናት 21 ሺሕ ቤቶች በሕገ ወጥ መንገድ ተላልፈው መገኘታቸው የሚታወስ ነው።

ሕገ ወጥ መሆናቸውን በጥናት የተረጋገጡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ካርታ ይኑራቸው እንጂ ለግለሰቦቹ በምን ሁኔታ እንደተላለፉ ማስረጃ አለመገኘቱንና የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ሕጋዊ አለመሆናቸውን ከቤቶች ኮርፖሬሽን መረጃ፣ ከባንክ መረጃና ቤቶች በዕጣ ባስተላለፉበት ማስረጃ ማረጋገጥ መቻሉ በጥናቱ መገለጹ የሚታወስ ነው።

በሌላ በኩል፣ ከኮንዶሚኒየም ጋር የሚነሳው ጉዳይ በየጊዜው አዲስ አበባን የሚመሩ ባለሥልጣናት በተለያየ ሁኔታና ምክንያት፣ ከ1997 ጀምሮ የሚቆጥበው የአዲስ አበባ ነዋሪ በጉጉት ዓመታትን እየጠበቀ ላልቆጠበ ሰው ኮንዶሚኑየም ይሰጣሉ የሚል ነው። ይሄ ጉዳይ በብዙዎች ዘንድ የሚነሳ ሲሆን፣ አዲስ አበባን የሚመሩ ከንቲባዎች በየሥልጣን ዘመናቸው በተለያየ ምክንያት ቤቶችን ለግለሰቦች ሲሰጡ ታይተዋል።

- ይከተሉን -Social Media

አንዳንዶቹ ስጦታዎች በግልጽ ለምስኪኖች የሚሰጡ ቢሆንም፣ የከተማዋ ባለሥልጣናት በድብቅ ለግለሰቦች የሚሰጧቸው ቤቶች መኖራቸውን ከጉምጉምታ ባለፈ በግለሰባዊ ግንኙነት ኮንዶሚኒየም የተሰጣቸው ሰዎች መኖራቸውን የሚያረጋግጡ መረጃዎችን አዲስ ማለዳ ሰምታለች።

እንዲህ ዓይነት ተግባራት መፈጸማቸው ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና መሠረቱን አዲስ አበባ ላይ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ባልደራስ በራሳቸው ተነሳሽነት ባደረጉት ጥናት ይፋ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው።

በአንጻሩ ከተማ አስተዳደሩ ለቆጣቢዎች በዕጣ የሚያስተላልፋቸው ቤቶች ለባለእድሎች በወቅቱ ሳይተላለፉ የሚዘገዩበት ሁኔታ እና ግንባታቸው ሳይጠናቀቅና መሠረት ልማት ሳይሟላላቸው ለባለ እድሎች የሚተላለፉ ቤቶች እስካሁን እልባት ያላገኙ የኮንዶሚኒየም ችግሮች ናቸው። ከተማ አስተዳደሩ ቤቶችን ለባለ እድለኞች አስተላለፍኩ ካለ በኋላ ዕጣ ከደረሳቸው ሰዎች የሚነሱ ቅሬታዎች በከተማ አስተዳደሩ በኩል የፖለቲካ ሥም ሲሰጣቸው ይስተዋላል።

የኮንዶሚኒየም የወደፊት ዕጣ ፋንታ
የአዲስ አበባ የቤት ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ፣ የነዋሪዎቿ የቤት ፍላጎትና የቤት አቅርቦት ተመጣጣኝ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ይገለጻል። ይህን የቤት ችግር ለመፍታት አንዱ መላ የተባለው የጋራ መኖሪያ ቤት ወይም ኮንዶሚኒየም ሲሆን፣ የሚነሱበት ችግሮች ቢኖሩም ፈላጊው አሁንም ብዙ ነው።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ በአዲስ አበባ የቤት ልማት ፕሮግራሙ ከተጀመረ አንስቶ በ10/90፣ 20/80 እና 40/60 የቤት ልማት ፕሮግራሞች ከ278 ሺሕ በላይ ቤቶች ማኅበራዊ ተቋሞችና የቢዝነስ አገልግሎቶች ተሟልቶላቸው ለቆጣቢዎችና ለልማት ተነሺዎች ተላልፈዋል። ከ650 ሺሕ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች እየቆጠቡ እድላቸውን በመጠባበቅ ላይ ናቸው ተብሏል።
ይሁን እንጂ፣ ከተማ አስተዳደሩ በሚገነባቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ፍላጎት ማሟላት እንደማይቻል እየተገለጸ ነው።

በዚህም የቤት ልማት ላይ ሌሎች አማራጮችን ከተማ አስተዳደሩ እየተመለከተ እንደሆነ ከገለጸ ሰነባብቷል። ይህንኑ ተከትሎ በቀጣይ የቤት ልማት የአገር ውስጥና የውጪ ባለሀብቶችን ተሳትፈውበት በግሉ ዘርፍና በመንግሥትና በግል ጥምረት እንዲለማ መንግሥት ፍላጎት እንዳለው ዐሳይቷል።

የቤት ፍላጎት ያላቸውን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በኅብረት ሥራ ማኅበራት በማደራጀት፣ በመንግሥትና በግል ባለሀብቶች በሽርክና የአዲስ አበባን የቤት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ይፋ አድርጓል።


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

አስተያየት

  1. እባካችሁ እናንተ አንኳን ስለ 20/80 የ2005 ባለ 3 መኝታ ቤት ለምን በ 14ኛ ዙር እጣ ማውጣት እንዳልፈለጉና ከዚህ በፊት በ 13ኛ ዙር የ 1997 ባለ 3 ተመዝጋቢዎች ስላለቀ ከ 20/80 2005 ላይ ነው እጣ የሚወጣው ብለው ለ5455 ሰዎች ወጦላቸዋል አሁን ምን መጥቶ ነው እንደገና የ1997 ጥቂት ሰዎች ስላሉ ማለት? ለዚህ ግልፅ ማብራሪያ ብትጠይቁልን እናም በሚቀጥለው የ እጣ አወጣጥ ላይ እንዲካተት እዲደረግ ብትጠይቁልን አመሰግናለሁ !

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች