መነሻ ገጽዜናትንታኔሦስተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በምን መልኩ?

ሦስተኛው ዙር የህዳሴ ግድብ የውኃ ሙሌት በምን መልኩ?

በጉባ ሸለቆ እየተገነባ ያለውና በአፍሪካ ትልቁ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተያዘው ክረምት ሦስተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት እንደሚያስተናግድ ይታወቃል።

ይህን ተከትሎም በተለይ ግብጽ በአንደኛውና በኹለተኛው ዙር ሙሌት ወቅት ከነበረው የበለጠ በሚመስል ሁኔታ ሙሌቱን እንደምትቃወም እየገለጸች ትገኛለች።

የመጀመሪያው ዙር የውኃ ሙሌት ከ4 ሺሕ 8 መቶ ባላነሰ ሄክታር መሬት ላይ 4 ነጥብ 9 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በመያዝ ከኹለት ዓመት በፊት ሐምሌ አጋማሽ መጠናቀቁ ይታወቃል። ኹለተኛው ዙር ሙሌትም ባለፈው ዓመት ክረምት ወቅት መከናወኑ የሚታወስ ነው።
ይህን ተከትሎ በዓመቱ ክረምት የግድቡ የውኃ ሙሌት ሲከናወን በሱዳንና ግብጽ በኩል የተለመዱ ተቃውሞዎች መኖራቸው አይካድም።

ለአብነትም ሱዳን ባለፈው ዓመት ኹለተኛው ዙር ሙሌት ሕጋዊ ስምምነት ሳይደረስና ግድቡ የሚያስከትላቸው ተፅዕኖዎች ላይ ጥናት ሳይደረግ የሚከናወን ከሆነ በኢትዮጵያ መንግሥትና የግድቡን የሲቪል ግንባታ በሚያከናውነው የጣሊያኑ ሳሊኒ ድርጅት ላይ ክስ እንደምትመሠርት ዝታ ነበር። ኢትዮጵያም የግድቡ ሙሌት በምንም መልኩ የሚቀር አይደለም ስትል ገልጻ፣ ኹለተኛው ዙር ሙሌት መጠናቀቁ ይታወሳል።
በዚህ ክረምትም ሦስተኛው ዙር የውሃ ሙሌት እንደሚከናወን ተመላክቷል።

ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የውኃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያ፣ የግድቡ የውኃ ሙሌት የግንባታ ሂደቱን ይከተላል ሲሉ ገልጸው፣ የትኛውም ዙር ሙሌት በግድቡ ግንባታ ሂደት ላይ ተፅዕኖ አይኖረውም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ስለሆነም የሙሌት መጠኑን የሚወስነው የግድቡ የግንባታ ደረጃ መሆኑን ካነሱ በኋላ፣ በኹለተኛው ዙር ሙሌት 13 ነጥብ 5 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ ለመያዝ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ የተሞላው ግን ከ3 ቢሊዮን ኪዩቢክ ያነሰ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም የሆነው በወቅቱ በነበረው የፀጥታ ሁኔታ የግድቡ ግንባታ ሂደት በመጓተቱ እንደሆነ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

በዚህ ክረምትም ሦስተኛው ዙር የውኃ ሙሌት በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል በይፋ ባይገለጽም፣ ግብጽና ሱዳን ግን ሙሌት እየተከናወነ መሆኑን እየተናገሩ ነው ያሉት ባለሙያው፣ ይህን ተከትሎም በየአቅጣጫው የውጭ ጫናዎች እየበረቱ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህን ተከትሎም በፊት ድጋፍ ሲሰጡ የነበሩት እነ አውሮፓ ኅብረት ኹሉ አስገዳጅ ስምምነት ላይ ድረሱ እያሉ ነው። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም ከሰሞኑ ይህን ነው ያለው፣ ከአረብ ሊግም ከገልፍ አገራትም ጫናው እየጨመረ ነው በማለት አብራርተዋል።

ለመሆኑ ሦስተኛው ዙር የውኃ ሙሌት ከእስከ አሁኑ በምን የተለየ ሆኖ ነው ጫናው ሊጨምር የቻለው በሚል ለተነሳላቸው ጥያቄም፣ በአንደኛውና በኹለተኛው ከተያዘው የውኃ መጠን እጥፍ በአሁኑ ሊያዝ ይችላል የሚል ፍራቻ በመኖሩ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም በኢትዮጵያ በኩል ይፋ የተደረገ ነገር ባይኖርም፣ 10 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውኃ በዚህ ዙር ሊሞላ እንደሚችል ባለሙያው ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ይህን የሚወስነው የግድቡ ግንባታ ደረጃ ነው ብለዋል።

ይህን አስመልክቶ የግበጹ ዕለታዊ ጋዜጣ፣ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሦስተኛ ዙር ሙሌት መርኃ ግብር 10 ቢሊዮን ኩዩቢክ ሜትር ውኃ ለመሙላት 17 ሺሕ ሄክታር መሬት ተዘጋጅቷል ሲል ከወራት በፊት ማስነበቡ ይታወሳል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር እንዲሁም የአባይ ጉዳይ ተመራማሪ ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የግድቡ ግንባታና የውኃ ሙሌት የማይነጣጠሉ መሆናቸው ከግብጽና ሱዳን ጋር በፈርንጆች 2015 ስምምነት የተደረሰበት ጉዳይ መሆኑን ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።

‹‹ጫና ቢኖርም አዲስ ችግር ተፈጥሮ አይደለም፣ እነሱና ደጋፊዎቻቸው በሌሎች ጉዳዮችም ብዙ ይላሉ። አሁንም ጫና ብለው ያሰቡትን ነገር ሊያደርጉ ይችላሉ። ኢትዮጵያን ግን ግድቡን ከመሙላት የሚያግዳት ነገር የለም።›› ብለዋል።

ኢትዮጵያ የግድቡን የውኃ ሙሌት በምታደርግበት ወቅት ማሳወቅ ለምን አስፈለጋት? ለማንም ሳታሳውቅ በዝግ መሙላት አትችልም ወይ የሚሉ አስተያየቶች ይሰነዘራሉ። የውኃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው፣ ኢትዮጵያ ግድቡን በምትሞላበት ወቅት የማሳወቅ ግዴታ እንዳለባት ይናገራሉ።

ይህም ሙሌቱ ሲካሄድ ግብጽና ሱዳን የሚያደርጉት ዝግጅት ካለና ራሳቸውን ከአደጋ መጠበቅ የሚያስፈልጋቸው ከሆነ ስለሙሌቱ ማሳወቅ አስፈላጊ ነው ይላሉ። ተቀበሉትም አልተቀበሉትም፤ ተዘጋጁም አልተዘጋጁም ማሳወቁ ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮ ነው ሲሉም አክለዋል። ኢትዮጵያ እያሳወቀች እንደፈለገች የመሙላት መብት አላት ነው የሚሉት።

ያዕቆብ አርሳኖም (ዶ/ር) ‹‹ድሮስ ግድቡ ሊሞላ አይደለም ወይ የተሠራው? ኢትዮጵያ ስለሙሌቱ የምታሳውቀው በበጋ ሳይሆን በክረምት ከጎርፍ ውኃ እንደምትሞላው ለማሳወቅ ይህም አገራቱን የመጉዳት እሳቤ እንደሌላት፣ መልካም ስነምግባሯንም ለማሳወቅ ነው።›› ሲሉ ተናግረዋል። ‹‹ስለሆነም፣ ኢትዮጵያ ሙሌቱን እንደፈለገች የማከናወን ሙሉ መብት አላት፤ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው›› ብለዋል።

የውኃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው አክለው፤ ‹‹ሦስቱ አገራት በፈረንጆች 2015 ካርቱም ላይ የተደረሰው ስምምነት (ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕልስ) የሙሌት መመሪያው ላይ እስማማለሁ ብለው ነበር። በተግባር ግን መስማማት አልቻሉም። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ላለመሙላት የገባችው ግዴታ ባለመኖሩ በግብጽና ሱዳን ጉዳት አያደርስባቸውም ብላ ባሰበችው መንገድ በፈለገች ጊዜ መሙላት ትችላለች።›› ባይ ናቸው።

- ይከተሉን -Social Media

አሳሪ ስምምነት ምንድን ነው?
ከሰሞኑ ሦስተኛው ዙር ሙሌት ሊከናወን መሆኑ መነገር ከጀመረ ወዲህ፤ በተለይ ግብጽ የተለመደ የተቃውሞ ድምጿን ማሰማቷን ቀጥላለች።
በዚህም ሰሞኑን ወደ መካከለኛው ምሥራቅና ወደ አውሮፓ አቅንተው የነበሩት የግብጹ ፕሬዘዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ከጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሾልዝ ጋር ስለግድቡ አንስተው፣ የህዳሴ ግድቡ የግብጽን የውኃ ደኅንነት ስጋት ላይ የሚጥል በመሆኑ ከኢትዮጵያ ጋር አሳሪ ስምምነት እንዲደረስ እገዛ የምትሻ መሆኑን መግለጻቸው ተሰምቷል።

ከአገራቸው ወጥተው እግራቸው በረገጠው ምድር ሁሉ የህዳሴ ግድቡን ጉዳይ ሳያነሱ የማይመለሱት ሲሲ፣ ከቀናት በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ በተሰናዳው የገልፍ አገራት ጉባኤ ላይ ይህንኑ ጉዳይ አንስተውም ከምክር ቤቱ አባል አገራት ድጋፍ እንደሚቸራቸው ተገልጾላቸዋል።

በዚሁ ቀጠና ከአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ጋር በተገናኙበት ወቅትም፣ ሲሲ የተጠናወታቸውን የህዳሴ ግድቡ የስምምነት ጉዳይ ገልጸዋል። አሜሪካም የኹሉንም አገራት ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ስምምነት እንዲደረስ የበኩሏን ትወጣለች የሚልና ንግግራቸው ወደ ተግባር ሲመጣ ምን እንደሚመስል ያልታወቀ መልስ ሰጥተዋል።

እንደ ውኃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው ገለጻ፣ በተለይ ግብጽና ሱዳን አሁን እየተደራደሩበት ያለው ቀደም ብሎ በአሜሪካ አገር ተሞክሮ ውድቅ የተደረገ ስምምነት ነው። ይህን ስምምነትም ኢትዮጵያ አስገዳጅ መሆን የለበትም የሚል ፅኑ አቋም አላት። በአንጻሩ ግብጽና ሱዳን ደግሞ ስምምነቱ አስገዳጅ እንዲሆን ይፈልጋሉ።

‹‹እንበልና ኢትዮጵያ ስምምነቱ ላይ ባሉት ይዘቶች ተስማማታ ብትፈርምና አስገዳጅ ሆኖ ቢጸድቅ፣ ከዚያ በኋላ በአባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም እድላችን አደጋ ውስጥ ይወድቃል። ለዚህም ነው ይህን ስምምነት እነሱ ቢፈልጉትም በኢትዮጵያ በኩል ግን አሳሪ በመሆኑ እስከ አሁን አልቀበልም የሚል አቋም ያለው።›› ሲሉ አብራርተዋል።

ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ አሳሪ ስምምነት ይደረግ የሚለው በተለይ በግብጽ በኩል ከ2018 ጀምሮ በተደጋጋሚ የሚነሳ ጉዳይ ነው ሲሉ ይናገራሉ። ይህም ኢትዮጵያ ግድቡን እንዳትሞላ፣ በውኃ ሀብቷ እንዳትጠቀምና በውኃ ሀብቷ ላይ ማንኛውንም እንቅስቃሴዋን ለግብጽ አስቀድማ እንድታሳውቅ የሚያደርግ ነው። ስለሆነም፣ ኢትዮጵያ ይህን ተቀብላ አታውቅም፣ ክብርና ጥቅሙን ለሚያስከብር ማንኛውም አገርም ይህ ጥያቄ ተቀባይ አይደለም ብለዋል።

ከግብጽና ሱዳን እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው የሚቀርበው ተቃውሞ የኢትዮጵያን እድገት ከመቃወም በቀር አዲስ ነገር የለውም የሚሉት ተመራማሪው፣ ግድቡ ኹለቱ አገራት ላይ የሚያሳድረውን ጫና እስከ አሁን በማስረጃ ያቀረበ የለም። አሁንም ያቀረቡት ማስረጃ የላቸውም። ይህን ያህል የሚጮኹትም ጉዳዩን የፖለቲካ ጨዋታ ስላደረጉት ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

ስለሆነም፣ እያስፈቀድን አይደለም የምንሞላው። ጫናውን መቋቋም፣ ግድቡን መሙላትና ወደፊት መራመድ ዋናው መፍትሄ መሆኑን ተመራማሪው አስምረውበታል።

- ይከተሉን -Social Media

ተቋርጦ የቆየው ድርድር
ባለፈው ጥር ወር በኢትዮጵያ በተቀሰቀሰው ጦርነትና በሱዳን በነበረው የአገር ውስጥ ውጥረት ሳቢያ ለአንድ ዓመት ያህል ተቋርጦ የቆየው ድርድር እንዲጀመር ግብጽ ጥሪ አቅርባ ነበር። ይሁን እንጂ፣ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ በግድቡ ጉዳይ ለመደራደር ከመሞከር ይልቅ በጦርነቱ የተፈናቀሉና የተራቡ ሚሊዮኖች ጉዳይ ያሳስባታል። በዚህም ድርድሩ ያን ያህል ተስፋ የለውም ስትልም አክላ ነበር።

ጦርነቱ ከተነሳ ወዲህ በተለይ በግብጽ የፖለቲካ ምሁራን ዘንድ በኢትዮጵያ በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶች ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን በሙሉ አቅሟ እንዳትገነባና በጀቷን ወደዚያ እንድታዞር ያደርጋታል የሚል ደስታ አዘል አስተያየቶች ሲዘነዘሩ ከርመዋል።

በኢትዮጵያ በኩል ድርድሩ ለምን እንደተቋረጠ የተገለጸ ነገር ባይኖርም፣ የውኃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው ኢትዮጵያም የተካተተችበት ድርድር በምሥጢር አረብ ኢሜሬት ውስጥ እየተካሄደ እንደሆነ ዓለም ዐቀፍ መገናኛ ብዙኀን እየዘገቡ ነው ብለዋል። ከዚህ ባለፈ በመንግሥት በኩል የታወቀ ነገር የለም፣ ሦስቱም አገራት ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውን ግን እያሳወቁ ነው በማለት ተናግረዋል።

ያዕቆብ አርሳኖ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በሦስቱ አገራት ሲካሄድ የነበረውን ድርድር ሳይሆን ውይይት ብዬ ነው የምጠራው ይላሉ። ምክንያቱም አንድ ነገር ሰጥቶ ሌላ መቀበል ሳይሆን የነበረው፣ በተለይ በኢትዮጵያ በኩል ግብጽና ሱዳን ስጋት እንዳያድርባቸው ማብራሪያዎች መስጠትና እነሱንም የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ እንዳልሆነ ለማሳያት ነበር የሦስትዮሽ መድረኩን ስትካፈል የቆየችው ብለዋል።

‹‹እነሱ ግን ይህን አልቀበልም በማለት አሳሪ ስምምነት ላይ መድረስ አለብን በማለት ሲፈልጉ ሲቀሩ ሌላ ጊዜም ረግጠው ሲወጡ ነበር። ወደፊትም ቀልብ ገዝተውና የኢትዮጵያን የቀደመ አቋም ለመቀበል ዝግጁ ሆነው ከመጡ ውይይቱ የማይቀጥልበት ምክንያት የለም።›› ሲሉ አስረድተዋል።

የግድቡ የውኃ ሙሌት በስንት ዙር ይጠናቀቃል?
የውኃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው፣ የግድቡ ሙሌት በምን ያህል ዙር እንደሚጠናቀቅ ለመግለጽ የሦስተኛ ዙር ሙሌቱ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል፡፡ አያይዘውም የባለፈው ዓመት ዕቅድ ተሳክቶ ቢሆን ኖሮ ከዚህ በኋላ በአንድ ዙር ይጠናቀቅ ነበር ነው ያሉት። አሁንም ሦስተኛ ዙር ሙሌቱ በታቀደው ልክ ይሞላል ወይ የሚለውን ስጋት በማንሳትም፣ ከዚህ በኋላ በምን ያህል ዙር እንደሚጠናቀቅ መገመት እንደማይቻል ገልጸዋል።

የአባይ ጉዳይ ተመራማሪው እንደሚሉት ደግሞ፣ የህዳሴ ግድቡን አጠቃላይ ሙሌት በሰባት ዙር ለማካሄድ በሦስቱ አገራት ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ ሰባት መሆን የለበትም ወደ 20 ዙር ከፍ ይበል የሚል ሐሳብ ቆይተው አመጡ። ‹‹ነገር ግን፣ ኢትዮጵያ ዝናብ ካለና በቂ ውኃ ካገኘች ከሰባት ክረምት ባነሰ ጊዜም መሙላት ትችላለች። ዋናው ነገርም ሙሌቱ በስንት ዙር ይጠናቀቃል የሚለው ሳይሆን የግድቡን የግንባታ ደረጃ ተከትሎ ሙሌቱ በየክረምቱ መሞላቱና ኃይል ማመንጨት መቻሉ ነው።›› ብለዋል።

በአባይ ወንዝ ላይ የሚገነቡት ተጨማሪ ግድቦች
ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ ከዓለም በውኃ ሀብት ከቀዳሚዎች ተርታ የምትሰለፍ መሆኗ ይታወቃል። ስለሆነም፣ በተለይ በታላቁ የአባይ ወንዝ ላይ እየገነባችው ያለው የህዳሴ ግድብ ሲጠናቀቅ ቀጣይ ሌሎች ግድቦችም መገንባት እንዳለባቸው ይነሳል። ምንም እንኳን የተናገሩት እውን ሆኖ ባይታይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድም 100 ግድቦች በአባይ ወንዝ ላይ እንገነባለን ሲሉ ተናግረው ነበር።

- ይከተሉን -Social Media

የአባይ ጉዳይ ተመራማሪው ያዕቆብ አርሳኖም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር በማውሳት፣ የሚገነባው ግድብ ቁጥር መቶም ይሁን አንድ ሺሕ በአገሪቱ አቅም ልክ ከተፋሰስ አገራት ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ መገንባታችን አይቀርም ሲሉ ገልጸዋል።

ምን ያህል ግድብ፣ በምን ያህል ፍጥነትና በምን ያህል ወጪ እንዲሁም ምን ያህል የኃይል መጠን የሚያመነጩ ግድቦችን እንገነባለን የሚሉትን ለአሁኑ መግለጽ ባይቻልም፣ በአባይ ወንዝ ላይ ተጨማሪ ግድቦችን መገንባቱ አስፈላጊ ነው። የማይገነባበት ምክንያትም የለም፣ ይልቅስ ባንገነባ ነው የሚገርመው በማለት ሐሳባቸውን ሰጥተዋል።

የግብጽ ትንኮሳ
የውኃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው የህዳሴ ግድቡ በግብጽ ላይ ተፅዕኖ ይኖረዋል፣ የጎላ ግን አይደለም ሲሉ ተናግረው፣ ለአብነትም ለኃይል ማመንጫ ግድቦቻቸው የሚደርሰው የውኃ መጠን ሊቀንስ ይችላል ይላሉ።

ከሰሞኑ ታዋቂ ባለሙያዎችና ተደራዳሪዎች ግደቡ አይጎዳንም ዝም ብለን ብናልፈው ይሻላል የሚል እንቅስቃሴ እያደረጉ መሆኑንም የውኃ ሀብት አስተዳደር ባለሙያው ጥቆማ ሰጥተዋል።

ይሁን እንጂ ግብጽ ከኢትዮጵያ በላቀ ስለአባይ ወንዝ በምትሠራቸው የተለያዩ የዲፕሎማሲና ሌሎች ጉዳዮች የወንዙ ባለቤት የሆነች ያህል ራሷን አስተዋውቃለች።

በቅርቡም ‹‹አባይ በየቀኑ›› የተሰኘ ኤግዚቢሽን በማዘጋጀትና ከአባይ ተፋሰስ አገራት የተወጣጡ ጋዜጠኞች በመጋበዝ አባይ ወንዝ ለግብጽ ማኅበረሰብ ምን እንደሆነ ለማስገንዘብ ሞክራለች።

ግብጽ የህዳሴ ግድቡ ከመገንባቱ በፊትም ቢሆን ኢትዮጵያ ኋላቀር ሆና እንድትዘልቅ በተለያዩ ምክንያቶች ስትሠራ መኖሯን ተደጋጋሚ ስሞታ ይቀርብባታል።

በተለይ ኹለቱን አገራት በሚያስተሳስረው የአባይ ወንዝ የተነሳ በየጊዜው የቃላት ጦርነቶች ከመወራወር ባለፈ ግብጽ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጇን እንደምታስገባም ነው የሚነገረው። ይህም በቅርቡ መሆን የጀመረ ሳይሆን፣ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ዘመን ተሻጋሪ ንትርክ በኢትዮጵያና ግብጽ መካከል ዘልቆ መቆየቱ ይገለጻል።

ለአብነትም በ1960ዎቹ ገደማ የግብጽ መሪ የነበሩት ከማል አብዱልናስርም አፄ ኃይለሥላሴን በጸያፍ ንግግር ይዘልፏቸው እንደነበረ ታሪክ አዋቂዎች ይመሰክራሉ። በተለይም የአባይን ወንዝ አስመልክቶ ኢትዮጵያ በግብጽ የውኃ ደኅንነት ላይ ስጋት የምትደቅን ከሆነ የወቅቱ የግብጽ መሪ በጃንሆይ ላይ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ይዝቱባቸው ነበር ነው የሚባለው።

ይሁን እንጂ፣ አፄ ኃይለሥላሴም የአገር ውስጥ ሥነ መንግሥታቸውን ለማረጋጋት ተጠምደው ስለነበርና ከግብጽ ጋርም አላስፈላጊ ድርጊት ውስጥ ላለመግባት በዝምታ ያልፉት እንደነበር ይነገራል። ስለሆነም፣ የዚህ ዋናው መፍትሄ የውስጥ ሰላምና አንድነትን በማረጋገጥ አባይን ማልማት እንደሆነ ይነሳል።

አዲስ ማለዳ ሦስተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት አስመልክቶ ከውኃና ኢነርጅ ሚኒስቴር ማብራሪያ የጠየቀች ሲሆን፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የማውቀው መረጃ የለም ሲል ገልጿል።

መጋቢት 24/2003 የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ እስከ አሁን ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደወጣበትና የግንባታ ሂደቱም ከ80 በመቶ በላይ ተጠናቆ፣ ኹለት ተርባይኖቹ ኃይል ማመንጨት መጀመራቸው ይታወቃል።


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች