ፋኖ… ፋኖ…

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለያየ ዓላማ የተደራጁ፣ ለአንድ ዓላማ የቆሙ ቡድኖች እንዲሁም በስፋት ደግሞ ለጥፋት የተሰማሩ ኃይሎች ሥማቸው በተደጋጋሚ ይጠቀሳል። የተወሰኑት በተደጋጋሚ ፈጽመዉታል በተባለ ወንጀልና ጅምላ ግድያ አሸባሪ ተብለው የተበየኑ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ የተለያየ ሥም እየተሰጣቸውና ሙግት እየተነሳባቸው ዘልቀዋል። ከነዛ መካከል ፋኖ አንዱ ሲሆን፣ ግዛቸው አበበ ይህን በማውሳት ዕይታቸውን ያሰፈሩበትን ኹለት ክፍል ያለው ጽሑፍ አቅርበዋል። በመጀመሪያውም የፋኖዎችን ድል የሚያበስሩ እየመሰሉ ፋኖነትን የሚያስወነጅሉና ሐሰተኛ ወሬ የሚያሰራጩ ማኅበራዊ ሚድያዎችን በሚመለከት ተከታዩን አንስተዋል።

በወረዳው፣ በአውራጃው፣ በቀየው ሥም የሚጠራ የፋኖ ወሬ አማራ ክልልን ሞልቶታል። የሸዋ ፋኖ፣ የወሎ ፋኖ፣ የጋይንት ፋኖ፣ የጎንደር ፋኖ፣ የጎጃም ፋኖ ወዘተ…. እየተባለ ብዙ ነገር ይወራል። ሕወሐት አማራውን በጅምላ ፈርጆ ከተስፋፊው አማራ ጋር የማወራርደው ሒሳብ አለኝ እያለ ነው። የኦሮሞ ነጻ አውጪ ነን የሚሉት ደግሞ ‹ነፍጠኞች› ከክልሌ ይውጡ እያለ አማራውን በወረዳው፣ በአውራጃውና በሐይማኖቱ ሳይለያይ በጅምላ እያጠቃው ነው።

እናም ፋኖ ነን የሚሉ ሰዎች የወረዳቸውና የአውራጃቸው ታጣቂዎች በመሆን መበታተናቸው ግርምትን የሚያጭር ነው። በኦሮምያ ክልል አማራዎች መጤዎች ተብለው በግፍ በተጨፈጨፉ ቁጥር ይህን የፈጸሙኩት እኔ ነኝ ባይ መጥፋቱና አንዱ በሌላው ላይ ጣቱን መቀሰሩ የሚናገረው አንድ ብርቱ ጉዳይ አለ፤ ‘ዋናው ነገር ዓላማን የማራመድ ጉዳይ ሳይሆን አማራን መግደሉ ነው። እናም የአማራ ወጣቶች አማራው ሕዝብ በጅምላ በጠላትነት በተፈረጀበትና ወረዳውና ሐይማኖቱ ሳይለይ እየተገደለ ባለበት በዚህ ጊዜ የወረዳቸውና የአውራጃቸው ነጻ አውጭዎች ናቸው በሚያስብል አደረጃጀት ላይ መጠመዳቸው ግራ አጋቢ ነው።

በአገር ቤትና በስደቱ ዓለም ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች የተወለዱበትን ወረዳ ፋኖ አስመልክተው አንዴ ተበደለ ብለው ሌላ ጊዜ ደግሞ ድል አገኘ ብለው ብዙ ያወራሉ። ጠመንጃ ተሸክሞ፣ አለበባስን አሳምሮ፣ ሲልም የሐይማኖት ምልክት አንጠልጥሎ ምስልን ለፌስቡክና ለዩትዩብ ነጋዴዎች መስጠት እንደ ትልቅ ሥራ እየታየ ነው። ነገሩ በዚህ አያበቃም፤ የወረዳው ፋኖ ነኝ ባዩ የወረዳውን የብልጽግና ሹማምንት ሆዳሞች፣ ገረዶች፣ ተላላኪዎች ወዘተ እያለ መዝለፍና ጠመንጃውን እየነቀነቀ ዛቻና የብቀላ ማስጠንቀቂያን መሰንዘር የተለመደ ነገር እየሆነ ነው።

ኢትዮ360 የመሳሰሉ የስደተኞች ሚዲያዎች እነዚህን የሚሳደቡና የሚዝቱ ፋኖ ነን ባዮችን በማቅረብ ተወዳዳሪ አይገኝላቸውም። በብልጽግና ላይ ለየት ያለ ጥላቻ የሰነቁት የኢትዮ360 ሚዲያ ሰዎች ‹‹ጠመንጃ ታጥቀው በአካባቢያቸው የብልጽግና ሹማምንትና በቤተሰቦቻቸው ላይ ዛቻ፣ ዘለፋና የግድያ ማስጠንቀቂያ ያለ ጥንቃቄ የሚሰነዝሩ ግለሰቦችን አታቅርቡ ወይም ምስላቸውን አታሳዩ” ተብለው ቢመከሩም ስደተኞቹ ኢትዮ360ዎች ‘ፋኖዎቹ ራሳቸው አቅርቡን አንፈራም ብለዋል’ እያሉ በዚያው ቀጥለዋል።

ይህን በመሳሰለው የዩትዩብ ሥራ ስደተኞቹ ዶላር ይነክሳሉ፤ ፋኖ ነኝ ባዮቹ ደግሞ ጥርስ ይነከስባቸዋል። ብዙም ሳይቆይ እነ ኢትዮ360 ፋኖ እገሌ ተገደለ፣ ፋኖ እገሌ ተገደለች፣ ፋኖ እገሌ ታሰረ፣ ፋኖ እገሌ ተሰደደች ወዘተ… የሚሉ ዜናዎችን ያሰማሉ፣ የዩትዩብ ንግዳቸው ይቀጥላሉ። የኢትዮ-360 ሰዎች በሕወሐት/ኢሕአዴግ ዘመን የስርዓቱ ዋና አገልጋዮች ነበሩ። የነበሩበትን ስርዓት አረመኔነት ከውስጡ ሆነው በተባባሪነት ነው የሚያውቁት።

አንዱ በደኅናው ሌላው ከሞት አፋፍ ደርሶ ነው ወደ አሜሪካ የተጓዙት። ለውጥ መጣ ሲባል ወደ አገር ቤት ያልተመለሱት ለውጥ የለም ብለው ነው። ታዲያ እነሱ ለሕይወታችን አደገኛ ነው ብለው የሸሹትን ስርዓት ሌላውም አደገኛ ነው ብለው ብስለት ለጎደላቸው ጠመንጃ ያዦች መጠንቀቁን ያልፈለጉት ለምን ይሆን?

በውጪ እና በአገር ውስጥ ሆነው በፌስቡክ፣ በዩትዩብ ወዘተ… የሚነግዱ ግለሰቦች በርካቶች ናቸው። አድማጭና ተከታታይ ለማብዛት በማሰብ ብቻ የፈጠራ ወሬዎችንና የተጋነኑ ዘገባዎችን ‘መረጃ ደረሰኝ’ እያሉ እያሰራጩ ነው። በችግሩ ላይ ነዳጅ አርከፍካፊዎች ሆነው በመሥራት ላይም ናቸው። በሺሕ የሚቆጠር ወጣት ዱር ቤቴ ብሎ ሸፈተ፣ በእገሌ የሚመሩ ፋኖዎች ኹለት ክፍለ ጦር ደመሰሱ፣ ፋኖ እገሌ ተገደለ፣ የፋኖ መሪ እየታደነ ነው፣ ብአዴኖች ፋኖዎችን ረሸኑ፣ ፋኖዎች በዚህ ተራራ ላይ መሽገዋል፣ ፋኖዎች መንግሥትን የራስህ ጉዳይ ብለው በዚህ ከተማ እየሠለጠኑ ነው፣ ብአዴኖች ፋኖዎችን ሙሉ በሙሉ ያጠፉ ዘንድ ከመንግሥት ትዕዛዝ ተቀብለዋል ወዘተ… የሚሉ ወሬዎች የዩትዩብ መነገጃዎች ሆነው ከተስተጋቡ ወሬዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

ራሳቸውን ለዩትዩብ ነጋዴዎች መጠቀሚያ ያደረጉና ከአፍንጫቸው ስር አርቀው ማሰብ የተሳናቸው ፋኖ ነን ባዮችም ሞልተዋል። ግለ ማስታወቂያ ለመሥራት ሲሉ የዩትዩብ ነጋዴዎችን ገቢ ለማዳበር ራሳቸውን ያመቻቹ ፋኖ ነን ባዮች ናቸው ማለት ይቻላል። ፋኖነት ጠመንጃ ታጥቆና ጥቁር መነጽር ዐይን ላይ ደንቅሮ በከተሞች ድራፍት ቤቶችና ቁርጥ ቤቶች መንጎማለያ እየሆነ ነው። ፋኖነት አለባበስን አሳምሮና ጠመንጃ ተሸክሞ በልጃገረዶችና በልጆች ተከቦ ሳይዋጉ ድል አድራጊ ጀግና ሆኖ ለመቆጠር የሚቻልበት ሥራ ሆኖ እየተቆጠረ ነው።

ውሎ አድሮ ምን ይመጣል፣ ነገሩ ምን ያህል አደገኛ ነው ብለው ለማሰብ ትንሽም ደንታ የሌላቸው በስደቱ ዓለምና በአገር ቤት ያሉ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ነጋዴዎችም የእነዚህ ፋኖ ነን ባይ የከተማ አውደልዳዮች ፎቶዎችንና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በፈጠራ ወሬዎች አጅበው ኪሳቸውን የሚሞሉበትን ቢዝነስ እያጧጧፉት ነው። ከየወሬው ጋር ሼር አድርጉ፣ ሰብስክራይብ አድርጉ፣ ላይክ አድርጉ ወዘተ.. እያሉ ንግዳቸውን እያስፋፉ ነው። በአማራነት ሥም መሰሪ ዩትዩቦችን ከፍተው ወሬ የሚያሰራጩ የአማራ ሕዝብ ጠላቶችም የፋኖዎች ድል የሚያበስሩ እየመሰሉ ፋኖነትን የሚያስወነጅል፣ ፋኖነትን አረመኔነት የሚያስመስልና ፋኖነት የጋጠወጦች መሰባሰቢያ የሚያስመስል ወሬ ያለ ማቋረጥ እያሰራጩ ነው።

ሐበሻው ሕዝብ ሙያ በልብ ነው ባይ ሕዝብ ነው። ሐበሻው ሕዝብ በቅኔ ተናግሮ በቅኔ የሚግባባ ሕዝብ ነው። ዛሬ ዛሬ ግን ሙያ በፌስቡክ ነው፣ ሙያ በዩትዩብ ነው ባዮች በዝተው እየታዩ ነው። ለብዙዎች በተለይም ተሞክሮ ለሌላው ጠመንጃ ያዦች ፉከራው ዩትዩብ ላይ ነው፣ ቀረርቶው ዩትዩብ ላይ ነው። እነሱ የማይሞቱ ይመስል በሌላው ሕይወት ላይ ዛቻ መሰንዘሩ ተራ ጨዋታ ነው። እነዚህ ዩትዩብና የፌስቡክ ደንበኞች የሆኑ ባለ ጠመንጃ ግለሰቦች የትግል ሀ…ሁ…. ያልገባቸው፣ በአማራው ሕዝብ ላይ የተደቀነው የሕልውና አደጋ በደንብ ያልተገለጠላቸው፣ አማራውን መታደግ የሚቻለው እንዴት እንደሆነ ጭራሽ ፍንጭ የሌላቸው ናቸው።

የሕወሐት/ኢሕአዴግ ስርዓት አማራውን ሕዝብ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የብሔሬ ጠላት ነው ብሎ እንዲያስብ፤ ለጥላቻ ተነሳስቶም አማራውን እንዲጎዳ ለማድረግ ሰፊ ሥራ የሠራ መሆኑን፣ ይህ መሰሪ የሕወሐት/ኢሕአዴግ ሥራ አማራውን በያለበት ለበቀል ዱላ ያመቻቸ መሆኑንና ላለፉት 30 ዓመታት አማራው በያለበት የሚጠቃው ለዚህ መሆኑን ልብ ማለቱ ላይ ትልቅ ችግር ያለባቸው ናቸው። ለዚህ ነው እነዚህ ጠመንጃ አንጋቾች ወደ ወረዳዬ አትምጡብኝ እኔም ከወረዳዬ አልወጣም ባይ ዓይነት አቋም ይዘው የሚታዩት።

ሱዳን የኢትዮጵያን መሬት በሰፊው ወርሮ ይዟል የወረዳዬ መሬት አይደለም ያሉ ፋኖ ነን ባዮች ይህ ብዙም አያሳስባቸውም። ሕወሐት ሰፋ ያለ የአማራ መሬትን እንደያዘ ነው የወረዳዬ መሬት አይደለም ያሉ ፋኖ ነን ባዮች ይህም ብዙ አያሳስባቸውም፣ በኦሮምያና በደቡብ ብዙ አማራዎች መጤዎች እየተባሉ የጥቃት ሰለባ እየተደረጉ ነው። ጉዳዩ የሚፈጸመው ከወረዳዬ እርቆ ነው ያሉ ፋኖ ነን ባዮች ይህ ምናቸውም አይደለም።

በተቃራኒው አንዳንድ ፋኖ ነን ባዮች ወረዳዊ አስተሳሰባው እንቃወመዋለን ለሚሉት ቡድን ወይም ከእነሱ ጋር የዓላማ ዝምድና ለሌለው ቡድን ወይም ግለሰብ አሸርጋጆች አድርጓቸው ይታያሉ። ብልጽግና ቡድንን በጠላትነት የፈረጁ አንዳንድ ፋኖ ነን ባዮች የብአዴን ብልጽግናውን እነ ደመቀ መኮንን ለአማራ ሕዝብ በመሟሟት ላይ ያለ ታጋይ አስመስለው ሲሰብኩ ይሰማሉ። ሌሎች ፋኖ ነን ባዮች ከብልጽግናዎች ጋር የሚሠሩ ሰዎችን በሙሉ ሆዳምና አድርባይ አድርገው ፈርጀው አሁን የብልጽግና ቡድን ቤተ-መንግሥት ባለሟል ሆኖ አስቀድማ ሹመትና ሽልማት የሰጠችውን ቤተ-ክርስቲያን ሳይቀር የዘነጋውን ዳንኤል ክብረትን፤ ለአማራ ክብር ላይ ታች እያለ የሚደክም ግለሰብ አድርገው ያወሩለታል።

ይህን መሰሉ አውራጃዊና ወረዳዊ ተለጣፊነት በርከት ብሎ በየወረዳው የሚታይና የወረዳውና የአውራጃ ተወላጅ የሆኑ ብልጽግና ሰዎችን ጲላጦስ መሰል ከደሙ ንጹሕ ነው ብሎ ከመከራከር አልፎ ፋኖነትን የአውራጃቸውና የወረዳቸው ተወላጅ ለሆነ ለስደተኛ (አሜሪካ አውሮፓ ለሚኖር) ጀሌዎች ማሰባሰቢያ አድርገው ሊጠቀሙበት የሚሞክሩ፣ ፋኖነትን የአብን ወይም የባልደራስ የወጣቶች ቡድን የመሰለ ስብስብ ለማድረግ የሚሞክሩ ሁሉ የሚታዩበት ነው።

በሕወሐት ቦምብ ቀባሪነት እና በብአዴን ተባባሪነት አማራውን ሕዝብ በቀጣይነት በክፉ ዐይንና በጥርጣሬ እንዲታይ የሚያደርግ ሥራ ተሠርቷል። ሸዋ ተቆርሶ፣ ወሎ ተቆርሶ፣ ጎጃም ተቆርሶ፣ ጎንደር ተቆርሶ ትርፍራፊው ተገጣጥሞ አማራ የሚባል ክልል ተመሠረተ። እነዚህ የቀድሞ የአማራ ክፍለ ሀገሮች የተቆረሰ መሬታቸውን ሲጠይቁ ሕወሐትና አፍቃሪ ሕወሐት ግንባሮች ተስፋፊው አማራ እያሉ ጥያቄው በተለየ መልክ እንዲታይ እያደረጉ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ተቆርሰው በተወሰዱ መሬቶች ላይ የሚኖረው፣ ከእልቂትና ከስደት የተረፈው የአማራ ሕዝብ የተረሳ ሰለባ እንዲሆን ጠንካራ ሥራ እየተሠራ ነው። ከዚህ ሌላ በሰፈራና በሌላም ምክንያት ከክልሉ ውጭ ለረዥም ጊዜ የኖረው አማራ ከክልሌ ውጣልኝ እየተባለ ነው። ካልወጣህ ተብሎም ሕጻን፣ አዛውንት፣ ወንድ ሴት ሳይባል በጅምላ በግፍ እየተደገለ ነው። ይህ ባለበት ሁኔታ ነው የአካባቢያችን፣ የወረዳችን ፋኖዎች ነን ባይ ቡድኖች እዚህና እዚያ የሚታዩት። አንዳንዶቹ ደግሞ ፋኖነት የተጀመረው እኔ በተወለድኩበት ወረዳ ነው በሚል ክርክር ውስጥ ተዘፍቀው ራስን የመካብ ትግል ውስጥ ተውጠዋል።

ማንኛውም ሰው ፋኖ ለመሆን ስድስተኛ ስሜት ሕዋስ ያስፈልገዋል። የወቅቱን ሁኔታ መረዳትና መጭውን ነገር መገመት የሚያስችል ሕዋስ የሌለው ሰው ፋኖ መሆን አይችልም። ብልጽግና ማለት ያልተበጠረና ያልጠራ ኢሕአዴግ ማለት ነው። ብልጽግና ማለት ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን ግፍና ሰቆቃ በሕወሐቱ ጌታቸው አሰፋ ላይ አላክኮ፣ ለ27 ዓመታት የተካሄደውን ዝርፊያ ሁሉ በበረከት ስምዖንና በታደሰ ጥንቅሹ ላይ ለጥፎ ከደሙና ከወንጀሉ ንጹሕ ነኝ የሚል ድርጅት ነው።

ብልጽግና ወንጀለኞቹንና ዘራፊዎቹን መንጥሮ ያላወጣ ቡድን ነው። ብልጽግና ተረኛ ነኝ ያለው ጌታ ሌላው ተላላኪ ሆኖ ለመኖር ግልጽም ስውርም ስምምነት ያላቸው ሰዎች የሞሉበት ቡድን ነው። ብልጽግናዎች እርስ በእርስ እየተጠራጠሩ ከመኖር ውጪ ሌላ አማራጭ ያላቸው አይደሉም። ስለዚህ ፋኖ መሆን የሚገባው ሰው ዘመኑን ማነፍነፍ የሚችል፣ በየሰበቡ መንጨርጨርንና ማማረርን እንደ ትግል ስልት አድርጎ የማይቆጥር፣ ራሴን እንዴት ላስተዋውቅ ብሎ ሳይሆን ለወገኖቼ ሰላምና ፍትሕን እንዴት ላምጣ ብሎ የሚያስብ አስተዋይ ሰው ብቻ ነው።

አንድ ፋኖ መሆን የሚገባው ሰው የብልጽግና ዝርክርክነት እየሰፋና እየከፋ እንደሚሄድና ይህ ዝርክርክነት ራሱን ብልጽግናን በአፍጢሙ እስኪደፋው ሳይቋረጥ የሚቀጥል መሆኑን መገመትና እስከዚያው በኢትዮጵያውያን ላይ ብዙ ጥፋት፣ ብዙ ውድመት፣ ብዙ እንግልት ወዘተ… እንደሚያደርስም መጠርጠር ይገባዋል። የፌዴራሉ ብልጽግና (የፌዴራሉ መንግሥት) እና የኦሕዴዱ ብልጽግና የሚለያዩበት የሥልጣን ድንበር ጠፍቶ መደበላለቁም በዝቶ መታየቱም ብዙ ችግሮችን የሚያስከትል መሆኑ ለማንም ግልጽ መሆን ይገባዋል።

በሌላ በኩል ሕወሐት በ1984 አካሄድኩት በሚለው የአካባቢው ሕዝብ ውሳኔ ወልቃይት ጠገዴን ወደ ትግራይ ጠቅልያለሁ እያለ ወልቃይት ወደ ነበረበት ወደ ጎንደር ይከለል ማለት ጦርነት ይቀጥል እንደ ማለት ነው ሲል እየተደመጠ ነው። ሕወሐት ወልቃይት-ጠገዴ-ራያን ከመሬቱ ይልቅ የትግራይን ሕዝብ በዘላለማዊ ጦርነት አዙሪት ውስጥ ለማኖር፣ ጦርነት የሚመራው ደግሞ ልምድ ባለው በሕወሐት ነው በሚል ሰበብ ዕድሜ ልኩን ተዋጊና ገዥ ሆኖ ለመኖር ሲል እንደ መሣሪያ ሊጠቀምበት የሚፈልገው ምድር ነው።

በእርግጥ ሕወሐት ይህ ምድር ቢሰጠው እንኳ ጦርነቱ እንዲቆም የሚያደርግ ምንም ዓይነት ሐሳብ ያለው ቡድን አይደለም። ሕወሐት ሙሉው የአገው ምድር፣ ሁሉም የአፋር ምድር የትግራይ ግዛት ነው ባይ ነው። አፋር ሲባል ኤርትራንና ጅቡቲንም ይጨምራል። የቲግረስ (በመካከለኛው ምሥራቀ የሚገኘው) ወንዝ ትግራይ ከሚለው ቃል የመጣ ነው። የባቢሎን ሥልጣኔ የተጋሩ ሥራ ውጤት ነው የሚሉ ምሁራንን ያሰማራው ሕወሐት ጦርነቱን ወደ አፍሪካ ምድር ብቻ ሳይሆን ወደ ኤዥያ ምድር አስፋፍቶም እየተዋጋና እየገዛ ሊኖር የሚከጅል ቡድን ሳይሆን እንደማይቀር ሊጠረጠር የሚገባ ነው። እናም ፋኖ ነኝ ባዩ ሆይ! ስድስተኛ የስሜት ሕዋስህን ተጠቀም። ይህ ሕዋስ ከሌለህ ፋኖ መሆን አይገባህም።

ለመሆኑ ፋኖ የሚለው ቃል ትርጉም ምንድን ነው? በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች በተሳሳተ መንገድ ሊያዩት እንደሚሞክሩት ፋኖ ማለት በዕድሜ ገደብ ወይም በጾታዊ ልዩነት ላይ ተመስርቶ የሚሠራ የሰዎች ስብስብ አይደለም። ፋኖ ማለት የአንድ አካባቢ ታጣቂዎችን የሚወክል መጠሪያም አይደለም። ፋኖ የሚለው የአማርኛ ቃል ቄሮ ከሚለው የኦሮምኛ ቃል ጋር ሊመሳሰልም አይገባም። ቄሮ ማለት የተወሰነ የዕድሜ ክልልን ብቻ የሚወክል መጠሪያ ሲሆን ፋኖ ግን ከዕድሜ ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም።

ፋኖነት ለፍትሕና ለነጻነት መቆምን፣ አልገዛም፣ አልረገጥም ባይነትን የሚወክል ቃል ነው። ፋኖነት አንድ ሰው እሱ ራሱ የተነፈገውን ፍትሕ ወይም ማኅበረሰቡ የተነፈገውን ፍትሕ ለማስመለስ የመቆም ጉዳይ ነው። የአማርኛ መዝገበ ቃላት ፋኖ ማለት ፋነነ፣ ሳይታዘዝ በፈቃዱ ዘመተ፣ ውኃ ስንቁን ኾኖ ዘመተ እያሉ ነው የሚገልጹት። ፋኖነት ከጀግናው በላይ ዘለቀ አልፎ ለአገራቸውና ለሰው ልጅ ለነጻነት የቆሙትን ሆቺ-ሚኒን እና ቼ-ጉቬራን የመሳሰሉ የነጻነት ታጋዮችን ለመጥራት ጥቅም ላይ የዋለው ለዚህ ነው።

- ይከተሉን -Social Media

በእርግጥ ፋኖነት በባለሥልጣናት ዐይን ሲታይ ፋነነ፣ አልታዘዝም አለ፣ ልቅ ሆነ ወዘተ… በሚል እንደሚተረጎምም መዝገበ ቃላቱ ያስረዳሉ። በዚያም ሆነ በዚህ ግን ፋኖነት መሣሪያ እንግቦ የከተማ አውታታ መሆን ማለት አይደለም። ፋኖነት መሣሪያ እንግቦ በሕዝብ ላይ መዝመትም አይደለም። ፋኖነት ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናትበጥሩ ዐይን እየታየ የኖረ የእንቅስቃሴ ዘርፍ ነው። ፋኖነት ብቃትን፣ ብስለትን፣ ጀግንነትን፣ ድፍረትን፣ ወኔንና ሕዝባዊነትን የሚወክል እንቅስቃሴ ነው። ፋኖነት ከሽፍታነት በጣም የተለየ ነው። ፋኖ… ፋኖ… የሚሉ በርካታ ዘፈኖች በማኅበረሰቡ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በመንግሥት መገናኛ ብዙኀንም ጭምር ሲደመጡ ኖረዋል። ትንሽ ቀደም ብሎ፣ የቅርብ ሩቅ በሚባል ጊዜ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት እነዚህን መሰል ዘፈኖች ለመቁጠር በሚያዳግት መጠን የተለያዩ የፕሮግራሞች በተለይም የጦር ሜዳ ውሎዎች የሚዘገቡባቸው ፕሮግራሞች ማጀቢያ ሆነው በሰፊው ጥቅም ላይ ሲውሉ ነበረ።

በቅርቡ ደግሞ ከሕወሐት ጋር የተፈጠረውን ጦርነት ተከትሎ ፋኖነት ከዘፈን አልፎ በአካል የሚያስፈልግበት ጊዜ እንደመጣ በመንግሥት ጭምር ተነግሮ፣ ፋኖነት አገር አድን መሆኑ ታምኖበት የአማራ ክልል ሕዝብ በፋኖነት ይዘምት ዘንድ ተጠይቆ ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከወጣቶች፣ ከገበሬዎች፣ ከመንግሥት ሠራተኞችና ከሌሎችም የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ በሺሕ የሚቆጠሩ ሰዎች የራሳቸውን መሣሪያ አንግበው ወደ ጦር ሜዳ ዘምተዋል። መሣሪያ የሌላቸው ደግሞ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ጠላትን ተፋልመው የማረኩትን ማንኛውንም ዓይነት የጦር መሣሪያ አንግበው ጦርነቱን እንዲቀላቀሉ፣ ሰፈራቸውንና ከተማቸውን እንዲጠብቁ በተደረገው ተደጋጋሚ ጥሪ በርካቶች የፍልሚያው ተሳታፊዎች ሆነው ነበረ።

በፋኖነት ዘምተው ሕይወታቸውን ያጡና አካላቸው የጎደለ በርካቶች ናቸው። ዋናውን መከላከያ ጦር ጨምሮ የፌዴራልና የክልል መደበኛ ታጣቂ ኃይሎች ስልታዊ ማፈግፈግ እየተባለ በርካታ የአማራ መሬቶችን እየተዉ ወደኋላ በሚመለሱበት ወቅት ፋኖዎች በተበታተነና አንድ ወጥ አመራር ባልነበረው ሁኔታ በየወረዳቸውና በየአካባቢያቸው እየተሽሎኮሎኩ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርገዋል። ታንኮችን፣ መድፎችን፣ ዲሽቃዎችን፣ መትረየሶችንና ዙ-23 የተባሉና በርቀት ዒላማ የሚመቱ ከፍተኛ የጦር መሣሪያዎችን ታጥቆ የመጣውን የሕወሐትን ተዋጊ ኃይል ዝቅተኛ የተኩሰ አቅም ባላቸው ጠመንጃዎች ለመጋፈጥ የተገደዱት ፋኖዎች በአማራ ምድር በተካሄደው ጦርነት እጅግ ትልቅ ዋጋ መክፈላቸውን ምንም ሊክደው አይችልም።

በእርግጥ በዚህ ጊዜ ለየት ያሉ በፋኖ ሥም የሚነግዱ ግለሰቦችም ተከስተዋል። ከከተማ ወደ ከተማ ከብልጽግና ሹማምንት ጋር እየሸሹ፣ ጠላት በተቃረበባቸው ከተሞች ፎቶ እየተነሱ፣ ራሳቸውን በፌቡክና በዩትዩብ፣ በመንግሥትና በብልጽግና ሚዲያዎች እያቀረቡ ራሳቸውን ያስተዋወቁ ፋኖ ነን ባዮችም ተስተውለዋል። እነ ብ/ጄኔራል ተፈራ ሲታሰሩም አንዳንዶቹ ተሹመዋል፣ ተሸልመዋል።

አሁን ጦርነቱ ጋብ ሲል ፋኖዎችን በሚመለከት ነገሮች ሁሉ የተቀያየሩ ይመስላሉ። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ እስከ ሕወሐቶች ፋኖዎችን በአንድ ድምጽ ማጥላላቱን፣ ማጣጣሉንና መወንጀሉን ተያይዘውታል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የአማራ ክልል ገዥ የተደረገው የብአዴን ብልጽግና የዚህ ማጥላላትና ውንጀላ ተባባሪ መሆኑ ነገሩን አሳሳቢ ያደርገዋል። በእርግጥ የባሕርዳርና የአዲስ አበባ የብልጽግና ባለሥልጣናት ፋኖዎችን ሲተቹ በጥሩና በመጥፎ ፋኖዎች መካከል መስመር ያለ መሆኑን እየተናገሩና በፋኖነት ሥም ወንጀል የሚሠሩ ያሉ መሆኑን ሲገልጹ ይሰማሉ።

በቅርቡ በወለጋ ምድር የተካሄደውን ጭፍጨፋ አስመልክቶ ከአንድ የዩቲዩብ ሚዲያ ጋር ሰፋ ያለ ቃለ ምልልስ ያደረገው የኦነግ ‘ሸኔው’ ጃል መሮም በስነ-ስርዓት የሚታገሉ ፋኖዎችና በፋኖነት ሥም ውንብድናን የሚያራምዱ ግለሰቦች መኖራቸውን ሲናገር ተደምጧል። አሳሳቢው ነገር እስራቱና ስደቱ ከተማ ውስጥ ሆነውም ሆነ በሰዋራ ቦታዎች መሽገው፤ በፋኖነት ሥም ወንጀል የሚሠሩ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ከጦር ሜዳ የተመለሱ ፋኖዎችንም ያጠቃለለ ሆኖ እየተካሄደ ነው የሚል እሮሮ በሰፊው እየተሰማ መሆኑ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

ግዛቸው አበበ በኢሜይል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ላይ ይገኛሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች