ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ለዘመናት ሥሟ ከፍ ብሎ ከሚሰማባቸው የስፖርት ውድድሮች መካከል ሩጫ ቀዳሚውን ደረጃ ይይዛል። የኢትዮጵያ አትሌቶች በተሳተፉባቸው ሩጫዎችም የኢትዮጵያ ሠንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ ይታያል። ዓለም ኢትዮጵያን ከሚያውቅባቸው መድረኮች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያውያን የሚያስመዘግቡት ድል ዛሬም እንደቀጠለ ነው።
በአሜሪካ ኦሪገን ግዛት ውስጥ እየተካሄደ በሚገኘው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች አንጸባራቂ ድሎችን እያስመዘገቡ ይገኛሉ። ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በተካሄዱ ውድድሮች ኢትዮጵያ በሦስት ወርቅ፣ በአራት ብር እና በአንድ ነሐስ በጠቅላላ በስምንት ሜዳልያ የኹለተኛ ደረጃን ይዛ በድንቅ ልጆቿ እየመራች ትገኛለች። ኢትዮጵያ በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኹለተኝነት ደረጃን የመራችው ውድድሩ ስድስተኛ ቀኑ ላይ እያለ ሲሆን፣ ውድድሩ ሊጠናቀቅ ገና አራት የውድድር ቀናት እየቀሩት ነው።
የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ ሐምሌ 09/2014 በተጀመረው የአሪገን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ውድድር፣ ኢትዮጵያ ከማራቶን እስከ 10 ሺሕ ሜትር በአንደኝነት በማጠናቀቅ የወርቅ ሜዳልያ አግኝታለች።
የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ በዓለም አደባባይ በተደጋጋሚ በድላቸው ከፍ አድርገው ከሚያውለበልቡ አትሌቶች መካከል አንዷ የሆነችው፣ አትሌት ለተሰንበት ግደይ በሴቶች በ10 ሺሕ ሜትር ውድድር በአስደናቂ አጨራረስ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊ ሆናለች። የ24 ዓመቷ አትሌት ለተሰንበት በዚህ ውድድር 30 ደቂቃ ከ9 ሰከንድ ከ94 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት በመግባት ነው የአንደኛነት ስፍራን በማግኘት የወርቅ ሜዳልያን ለአገሯ እና ለራሷ ያሸነፈችው።
በኹለተኛው ቀን ሐምሌ 10/2014 በተካሄደው 18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ባለድል ያደረገው አትሌት ታምራት ቶላ ሲሆን፣ አትሌት ታምራትን ተከትሎ በመግባት የብር ሜዳሊያ ለኢትዮጵያ ያስገኘው አትሌት ሞሰነት ገረመው ነው።
በዚህም በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ የአንደኝነትና የኹለተኝነት ደረጃን በመያዘ የወንዶች ማራቶን መሪ እንድትሆን በማስቻል፣ አትሌቶቹ ተከታትለው ባስመዘገቡት ድል ኢትዮጵያ የበላይነቱን እንድትይዝ አድርገዋል።
አትሌት ታምራት ሻምፒዮን ለመሆን የቻለው ተፎካካሪዎቹን በረዥም ርቀት ጥሎ በመውጣት ውድድሩን በ2 ሰዓት ከ05 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ በመግባት ማጠናቀቅ ከቻለ በኋላ ነው። አትሌት ታምራት ቶላ ኦሪገን ላይ እየተካሄደ በሚገኘው የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የማራቶን ውድድር ማሸነፍ ብቻም ሳይሆን የውድድሩን ክብረ ወሰን መስበር ችሏል።
አትሌት ታምራት ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት፣ “ውስጤን አሳምኜ የመጣሁበትን ነው ያደረኩት” ሲል ተደምጧል። ወደ ውድድሩ ከመግባቱ በፊት የመጨረሻዎቹን 10 ኪሎ ሜትሮች ከፊት ወጥቶ ለብቻው ሮጦ ለማሸነፍ አቅዶ እንደነበረ የገለጸው ታምራት፣ ወርቅና ብር ማግኘታችን የማራቶን የበላይነቱን እንድንይዝ አድርጎናል ብሏል።
በሴቶች ማራቶን የ27 ዓመቷ ጎተይቶም ገብረሥላሴ በ2 ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ በመግባት ለኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ያስገኘች ሲሆን፣ የአንደኝነት ደረጃዋን አስጠብቃ ማሸነፍ የቻለችው በከፍተኛ ሁኔታ ስትፎካከራት የነበረችውን ኬንያዊቷን አትሌት ጁዲት ኮሪርን በመቅደም ነው። አትሌቷ ከዚህ ቀደም በብሪታኒያዊቷ ፓውላ ራድክሊፍ ተይዞ የነበረውን የዓለም ሻምፒዮና ክብረ ወሰንም በማሻሻልም አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግባለች።
ሐምሌ 11/2014 በተካሄደው የሴቶች ማራቶን ውድድር ሲፎካከሩ የነበሩት ኢትዮጵያዊቷ ጎተይቶም እና ኬንያዊቷ ጁዲት የየራሳቸውን ምርጥ ሰዓት ያስመዘገቡ ሲሆን፣ ጎተይቶም ለኢትዮጵያ ሦስተኛውን ወርቅ ያስገኘችው ከጁዲት ዘጠኝ ሰከንድ ቀድማ በመግባት ነበር። ሌላኛዋ ትውልደ ኬንያዊት እስራኤላዊት ሎናህ ሳልፕተር በ2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ በመግባት የነሐስ ሜዳሊያ አግኝታለች።
ጎተይቶም አሸናፊ ያደረጋት ምስጢር ስትናገርም ‹‹40ኛው ኪሎሜትር ላይ ስደርስ አፈትልኬ ለመውጣት አቅጄ ነበር። ያንን ስልት በመጠቀሜም ወርቅ ማምጣት ችያለሁ” ብላለች። አያይዛም፤ ‹‹ዋናው ነገር ጠንክሮ መሥራት ነው። ጠንክሮ ከተሠራ ማንንም ቢሆን ማሸነፍ ይቻላል። አገሬ እያለሁ ጠንክሬ ሠርቻለሁ። በእርግጥ ኬንያዊያን ከባድ እንደሆኑ አውቃለሁ።›› ያለችው አትሌቷ ‹‹ፍጥነት የመቀየር ዓላማ ይዤ ነው የገባሁት። እናም በመጨረሻው ሰዓት ከፍተኛ ፍጥነት ስለነበረኝና ያንን መጠቀም ስለቻልኩ አሸንፌያለሁ።›› ብላለች።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኤርትራዊቷ ናዝሬት ወልዱም 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ29 ሰከንድ በመግባት አራተኛ ደረጃን ይዛ በማጠናቀቅ አዲስ ብሔራዊ ክብረ ወሰን አስመዝግባለች።
ጎተይቶም ከውድድሩ በኋላ በሰጠችው አስተያየት፣ ‹‹ሁሉም ነገር ሰላም ሆኖ እኔ እንደተደሰትኩት አባትና እናቴም ይደሰታሉ ብዬ አምናለሁ›› በማለት ተናግራለች። ትግራይ ክልል፣ ከመቀለ ወጣ ብላ በምትገኘው አዲ ጉዶም በሚባል ስፍራ የተወለደችው ጎተይቶም፤ መስፍን ኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግ የአትሌቲክስ ቡድን አባል ነበረች።
በአሜሪካዋ ኦሪጎን ግዛት እየተካሄደ ባለው የዓለም ሻምፒዮና ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች አስደናቂ ፉክክር አድርገው ሪከርድ በመስበር፣ በኹለቱም ጾታ ኢትዮጵያን በማራቶን ወርቅ እንድታገኝ አድርገዋታል።
በሴቶች 1500 ሜትር ውድድርም አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ 3 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ ከ52 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ለኢትዮጵያ የብር ሜዳሊያ አስገኝታለች። በወንዶች 3000 ሜትር መሰናክልም አትሌት ለሜቻ ግርማ 8 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ ከ1 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።
በሴቶች 3000 ሜትር መሰናክል ሩጫ የወርቅውኃ ጌታቸውና መቅደስ አበበ ባስመዘገቡት ድል ኢትዮጵያ የብርና ነሐስ ሜዳልያ አግኝታለች።
በሴቶች 10 ሺሕ ሜትር በአትሌት ለተሰንብት ግደይ የወርቅ ሜዳልያ የቀናት ኢትዮጵያ፣ በወንዶች የ10 ሺሕ ሜትር ፍጻሜን ፍድድር ድል አልቀናትም። ኢትዮጵያ በ10 ሺሕ ሜትር የወንዶች ውድድር የዚህ ዘመን ጠንካራ አትሌት በሆኑ እንደ ሰለሞን ባረጋ ባሉ ጠንካራ አትሌቶች ተወክላ የነበረ ቢሆንም፣ ኡጋንዳ የበላይነቱን ይዛ አጠናቃለች።
ከፍተኛ ፉክክር በታየበት በዚህ ውድድር ጆሱ ቼፕቴጊ 27 ደቂቃ ከ27 ሰከንድ ከ43 ማይክሮ ሰከንድ በሆነ ሰዓት ወርቁን ሲወስድ፣ ኬንያዊው ስታንሊ ኡምቡሩ ኹለተኛ ሆኖ አጠናቋል። ሌላኛው ኡጋንዳዊ ጃኮብ ኪፕሊሞ ሦስተኛ ደረጃን ይዟል። በዚህ ውድድር ከወርቅ እስከ ነሐስ አሸናፊ የሆኑት አትሌቶች በሙሉ በመድረኩ የዓመቱን ምርጥ ሰዓት ማስመዝገባቸው የውድድሩን ጠንካራነት ያስመሰከረ ነው ተብሏል።
በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ውስጥ ይገባል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው እና በቶኪዮ ኦሎምፒክ በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘው ሰለሞን ባረጋ 5ኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ የቆየው በሪሁ አረጋዊ 7ኛ ሆኖ ውድድሩን ጨርሷል። ጠንካራ ፉክክር በታየበት በዚህ የወንዶች 10 ሺሕ ሜትር ውድድር ሰለሞን ባረጋና በሪሁን አረጋዊ እስከመጨረሻው ድረስ በከፍተኛ ጥረት ፉክክር ያደረጉ ቢሆንም፣ ኹለት ኡጋንዳውያንና ኹለት ኬንያውያን አትሌቶች ጋር የገጠማቸው ፉክክር በመጨረሻ በሰከንድ ልዩነት እንዲበለጡ አድርጓቸዋል።
በስፖርት ድል የሚደምቀው ኢትዮጵያዊነት
የኢትዮጵያ አትሌቶች በ18ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዩና በኹለቱም ጾታ የማራቶን ወርቅና በ10 ሺሕ ሜተር ሴቶች በበላይነት ማሸናፋቸውን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያዊያን ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል። ኢትዮጵያ ባጋጠማት የፖለቲካ ስብራት በየቦታው የሚታየው ጤነኛ ያልሆነ ልዩነት፣ የኢትዮጵያ አትሌቶች የኢትዮጵያን ሠንድቅ በዓለም አደባባይ ከፍ አድርገው ሲያውለበልቡ ያለ ልዩነት ሁሉም ኢትዮጵያን በሚል ደረጃ ደስታቸውን ሲገልጹ ማየት የተለመደ ነው።
በሰሞኑ የኦሪገን ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ያስመዘገቡትን ድል ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ያለ ልዩነት ደስታቸውን በተለያየ መንገድ ሲገልጹ፣ ብዙዎች የስፖርት ድል የኢትዮጵያዊያንን ኢትዮጵያዊነት የሚያደምቅ ክስትት መሆኑን እየገለጹ ነው።
ኢትዮጵያዊያን በስፖርት ድል ላይ ያላቸው አቋም በውስጥ እንደሚታዩ ችግሮች ልዩነት ያለበት ሳይሆን፣ ከእነ ሻምበል አበበ ቢቂላ የሮም ድል እስከ አሁን ድረስ በአንድነት የሚኮሩበትና የሚደሰቱበት ክስተት ነው።
ሻምበል አበበ ቢቂላ እኤአ በ1960 በጣልያን መዲና ሮም በተካሄደው የዓለም ኦሎምፒክ ውድድር በባዶ እግሩ ሮጦ አሸናፊ በመሆኑ ዓለምን አስደምምሞ ለኢትዮጵያ ኩራት ሆኗል። በዚያ ውድድር ከ83 አገራት የተወጣጡ ከአምስት ሺሕ በላይ ስፖርተኞች መሳተፋቸው ይነገራል።
ኢትዮጵያን በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ኦሎምፒክ አሸናፊ በማድረግ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካዊያን የሩጫ አቢዮት በር የከፈተው አበበ ቢቂላ “ሮምን የወረረው ብቸኛ ወታደር” እየተባለ በደማቅ ታሪክ ሥሙ ሲወደስ ይኖራል። አበበ በባዶ እግሩ ሮጦ በሮም አደባባይ ካሸነፈ በኋላ ለአገሩ ያለውን ክብር ሲገልጽ “እኔ ዓለም ሁሉ እንዲያውቀው የምፈልገው አገሬ ኢትዮጵያ ሁል ጊዜ የምታሸንፈው በቆራጥነት እና በጀግንነት እንደሆነ ነው” ሲል ተደምጦ ነበር።
ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014