በሕወሓት ቁጥጥር ስር ለሚገኙ ኹለት የዋግ ኽምራ ወረዳዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሰብዓዊ ድጋፍ ሊላክ ነው

0
1116

በአማራ ክልል ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በሕወሓት ቁጥጥር ስር ለሚገኙ 29 ሺሕ የአበርገሌና የፃግብጅ ወረዳ ነዋሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ዩኤስኤይድ እና ሲአርሲ በተባሉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሰብዓዊ ድጋፍ ሊላክ ነው ተብሏል።

የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ፣ በከፍተኛ የሰብዓዊ ችግር ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደረግ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አስታውቋል።

አካባቢው በሕወሓት ቁጥጥር ስር የሚገኝ መሆኑን ተከትሎ እስከ አሁን አበርገሌና ፃግብጅ ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዮች በመንግሥት በኩል ምንም ድጋፍ አልተደረገም ተብሏል። የመጀመሪያው ሰብዓዊ ድጋፍ የሚላከው የዓለም ምግብ ፕሮግራም ድርጅት አጥኚ ቡድን አካባቢውን ከተመለከተ በኋላ፣ ምንም ዓይነት የምግብና የጤና አገልግሎት አለመኖሩን ሪፖርት ማድረጉን ተከትሎ ነው ተብሏል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም በአካባቢው አጥኚ ቡድን ልኮ ምንም ዓይነት ምግብ አለመኖሩን ካረጋገጠ በኋላ፣ አበርገሌ ወረዳ ለሚገኙ 29 ሺሕ 600 ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች እርዳታው ቦታው ድረስ እንዲገባ መፈቀዱን ጽሕፈት ቤቱ ገልጿል።

በግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሚሰራጨው ሰብዓዊ ድጋፍ በዓለም ምግብ ፕሮግራም አማካኝነት 35 ተሳቢ መኪኖች ስንዴ፣ ክክ እና የምግብ ዘይት መሆኑ ተመላክቷል። ከእነዚህ ውስጥም ኹለት ሺሕ 991 ኩንታል ስንዴ፣ 928 ነጥብ 59 ኩንታል ክክ እና 278 ነጥብ 58 ሊትር የምግብ ዘይት የጫኑ 14 ተሳቢዎች ባለፈው ሐሙስ እለት ሰቆጣ ከተማ መግባታቸው ተሰምቷል።

ለሰብዓዊ ድጋፍ ሰቆጣ ከተማ መግባታቸው የተነገረላቸው የጭነት ተሽከርካሪዎች በአጭር ጊዜ በችግር ላይ ለሚገኘው ማኅበረሰብ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ቀሪዎቹ 21 ተሳቢዎችም የጤና ነክ መድኃኒቶችንና የሕፃናት አልሚ ምግቦችን ጨምረው ያመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጽሕፈት ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል።

ረጂ ድርጅቶቹ ዩኤስኤይድ (USAID) እና ሲአርሲ (CRS) የተባሉ ግብረሰናይ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ሲሆኑ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም(WFP) ከኮምቦልቻ ጀምሮ እስከ አበርገሌ ድረስ ያጓጉዛል ተብሏል። ስርጭቱን የሚያካሂደው ደግሞ FH Ethiopia የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ሲሆን፣ በአጠቃላይ ድርጅቶቹ ምግብ የማቅረብ፣ የሎጂስቲክስና የማሰራጨት ተግባርን እንደሚያከናውን ተመላክቷል።

ከፃግብጅ ወረዳ እና በዝቋላ ወረዳ በሕወሓት ቁጥጥር ስር የሚኖሩ የስድስት ቀበሌ ነዋሪ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማስቻል፣ ችግሩን የሚያጠና ቡድን ወደ አካባቢው እንደሚያቀና ይጠበቃል።

በዝቋላ የሚገኙ የስድስት ቀበሌዎች ተጋላጮች ፅፅቃ ከተማ እንዲረዱ እና ፃግብጅ ወረዳ የሚኖሩ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ ወረዳው ላይ መኪና መግባት ስለማይችል በሦስት አማራጮች ማለትም ሦስት ቀበሌዎች ፀመራ እና ቀሪዎቹ ቀበሌዎች ደግሞ ከመፅርዋ እንዲረዱ የተወሰነ መሆኑን ጽሕፈት ቤቱ በመግለጫው ይፋ አድርጓል። ከዚህ ውጭ የሆኑት ቀበሌዎች ደግሞ በማይጨው ወድሰምሮ በኩል የሚገባላቸው በመሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶቹ ከሕወሓት ጋር ተስማምተው እንዲገባላቸው ጥያቄ መቅረቡ ተሰምቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here