10ቱ በርካታ የአውሮፕላን ማረፊያ ያላቸው አገራት

0
492

ምንጭ:ጋዜት ሪቪው (2017/18)

ኹለቱ የራይት ወንድማማቾች (ዊልበርእና ኦርቪል ራይት) አውሮፕላንን በተግባር ከፈጠሩ በርካታ ዓመታት በኋላ፣ አሁን ዓለማችን በአየር በረራ ሊደረስበት ከሚችለው የቴክኖሎጂ ደረጃ መጨረሻ እየደረሰች ይመስላል። ጉዞን ፈጣንና ቀላል የሚዲርጉ አውሮፕላኖችና ለእነዚህም ማረፊያና መነሻ የሚሆኑ አውሮፕላን ማረፊያዎችም ከጊዜ ጊዜ እየጨመሩና እየዘመኑ ሔደዋል። ታድያ አገራትም እነዚህን የሕዝብ ማመላለሻዎች በመጠቀም የገቢ ምንጫቸውን ከፍ ያደርጋሉ፤ የእርስ በእርስ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶችንም ያሳልጣሉ።

አየር ማረፊያዎች ለአውሮፕላን ማረፊያና መነሻ ምቹና ሰፊ ሜዳዎች፣ መጠገኛ ስፍራዎች፣ ለተሳፋሪዎች የተመቻቸ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ፣ ደኅንነቱ የተተበቀ የሻንጣ ማስቀመጫና መረከቢያ፣ ትኬት ሲቆርጡ እንግልት የሌለበት ወዘተ እንዲያሟሉ ይጠበቃል።

ጋዜት ሪቪው የተባለ ድረገጽ በ2017 የተገኘና እስከ 2018 መጨረሻ ድረስ ታይቶ የተሻሻለ ነው ብሎ ባወጣው መረጃ መሠረት ታድያ፤ አሜሪካ በዓለማችን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአውሮፕላን ማረፊያ ያላት አገር ሆና ተመዝግባለች። ከእርሷ ቀጥሎ የሚገኙት አገራት ሁሉ ቢያንስ በአውሮፕላን ብዛት በ10 ሺሕ የሚያንሷት ናቸው። ምንአልባት ይህ ለጎብኚ መዳረሻነቷ መንስኤ አልያም የጎብኚ መዳረሻነቷ ውጤት ሊሆንም ይችላል።

ይኸው መረጃ ጨምሮ እንደሚያመለክተው በአሜሪካ ሰማይ ላይ በቀን 87 ሺሕ አውሮፕላኖች ይገኛሉ። ከሌላ አገር የሚነሳው ቢቀር እንኳ በአገር ውስጥ በረራ በምድረ አሜሪካ እጅግ ከፍተኛ ነው ማለት ነው።

ብራዚል በዚህ ዝርዝር በኹለተኛ ደረጃ ስትቀመጥ፤ ምንም እንኳን አየር መንገዶቿ በጥራት የተመሰገኑ ባይሆንም ቁጥራቸው ግን በርካታ ነው። ኢንዶኔዥያ የመጨረሻዋ ሆና በአስርቱ ዝርዝር ትመዝገብ እንጂ በዚህ ዝርዝር ውስጥ የተገኘች ብቸኛዋ እስያዊት አገር ናት። አፍሪካ ግን ከዚህ ዝርዝር አልተጠጋችም። ፐሮኬራላ (www.prokerala.com) የተባለ ጉዞና ጉብኝት ነክ ዜናዎችን የሚያሰራጭ አውታር ላይ ኢትዮጵያ በጠቅላላው 53 አውሮፕላን ማረፊያዎች እንዳሏት ዘግቧል፤ ከዚህ ውስጥ ታድያ መደበኛ በረራ የሚካሄድባቸው 23 ናቸው።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here