የ”መስበር” እና የ“መሰበር“ ነገር

0
659

ከሰሞኑ አዲስ አበባ በተለይም ደግሞ መስቀል አደባባይ በሳምንት ልዮነት ኹለት ታላላቅ በዓላት ሲካሔዱበት ከተማዋም እንደየበዓላቱ ስታሸበርቅ አሳልፋለች። መስከረም 24/2012 በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ዐይነ ግቡ የሆነ ትዕይንት የታጀበ እና ለቁጥር በሚያዳግት ታዳሚ የኢሬቻ በዓል ተከብሯል። በዚህ ክብረ በዓል ላይ ታዲያ የኦሮሞ ልጆች ‹ደስታችን ደስታችሁ ነውና በበዓላችን ላይ ተገኙልን› በሚል የክብር እንግዶችን ጋብዘው የክልል መንግሥታትም የቻሉት በአካል ያልቻሉት ደግሞ በተወካዮቻቸው ተገኝተው የበዓሉ ታዳሚዎች ለመሆን ችለው ነበር።

በዚህ ጊዜ ታዲያ መድረክ ላይ ተቀምጠው ከክብር እንግዶች ጋር ሲጨዋወቱ የነበሩት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ንግግር ለማድረግ ማይክራፎን ጨበጡ እናም በንግግራቸው መሀል ከ150 ዓመት በፊት የኦሮሞ ልጆች በነፍጠኛው በተሰበሩበት ቦታ ነፍጠኛውን ሰብረን ዛሬ ኢሬቻን ለማክበር በመቻላችን እንኳን ደስ አላችሁ የሚል ንግግር አሰሙ። ከዛች ሽራፊ ሰከንድ በኋላ ኹሉም ማኅበራዊ ትስስር ገጾች የሽመልስ አብዲሳን ንግግር በፈርጅ በፈርጁ እየሰነጠቁ ትችታቸውን፣ ነቀፌታቸውን፣ ከፍ ሲል ደግሞ ስድባቸውን አስተጋብተው የሰሞኑ መወያያ ርዕስ እስከ መሆን አድርሰውት ነበር።

የምክትል ርዕሰ መስተዳደሩን ንግግር መሰረት አድርገው ጉምቱ ባለሥልጣናት የነበሩ የቀድሞ የአማራ ክልል ኮምኒኬሽን ኀላፊ የነበሩት አሰማኸኝ አስረስን ጨምሮ ደርዝ ያለው ምላሽ በሰከነ አንደበት እና በቱባ ብዕር ሰጥተዋል። ከውጭም ከአገር ውስጥም የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችም ንግግሩን በይፋ ተችተዋል። “ላለፉት ዓመታት ስንሰማው እና ሰዎች በጅምላ ሲፈረጁበት የነበረ ቃል እንዴት ለውጥ መጥቷል በሚባልበት በአሁኑ ሰዓት ልንሰማው ቻልን” ሲሉም ቅሬታቸውን በለውጡ ኀይል ላይ አሰምተዋል።

የሽመልስን ንግግር የተቃወሙትን ያህል ድጋፋቸውን በመስጠት “አበጀህ” ያሉትም አልታጡም። የግራ እና የቀኙን በሐሳብ መጠዛጠዝ በትንሹም ቢሆን ረገብ ያደረገ ድርጊት በሳምንቱ ግማሽ ላይ ተከስቷል። የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አስታራቂ እና አንድነትን የሚሰብክ መግለጫ በይፋ አውጥቶ ከኢሬቻ ቀን ጀምሮ ሲንቀለቀል የነበረው እሳት ላይ ውሃ በመቸለስ አቀዝቅዞታል። ‹‹ከመጣንበት መንገድ በላይ ወደፊት አብረን የምንጓዘው ጉዞ ረጅም ነው” በሚል ርዕስ ያወጣው በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያለው መግለጫ በሕዝቦች መካከል ፍቅርን፣ አንድነትና ሰላም ከሚያመጡ ድርጊቶች በተቃራኒው የሚቆሙትን በድርጅቱ ደንብ መሰረት እንደሚቀጣ አስታውቋል።

የአዴፓ እና የኦዲፒ የዓላማ እና ተግባር አንድነት ከዚህ ቀደም ያጋጠሙትን ችግሮች በጋራ እንደፈታ ኹሉ፣ ከዚህ በኋላ ለሚያጋጥሙ ችግሮችም በአንድነት በመፍታት እንደሚዘልቁ ኦዲፒ መግለጫ በግልፅ አስነብቧል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here