መነሻ ገጽዜናየእለት ዜናካቻ የመጀመሪያውን የግል የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት ፍቃድ ማግኘቱን አስታወቀ

ካቻ የመጀመሪያውን የግል የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት ፍቃድ ማግኘቱን አስታወቀ

አርብ ሐምሌ 15 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የግል የሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎትን ለመስጠት በ200 ሚሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል የተቋቋመው ካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ አ.ማ. አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችለውን ፍቃድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማግኘቱን አስታወቀ።

ይህም ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያገኘው የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት ፍቃድ በአገሪቱ የመጀመሪያው የግል የዲጂታል ፋይናንስ ኩባንያ እንዲሆን ያስችለዋል ተብሏል።

የካቻ ሞባይል ገንዘብ ዝውውር አገልግሎት በጥሬ ገንዘብ የሚከናወኑ ግብይቶችን በማስቀረት የዜጎችን ኑሮ ለመሻሻል ጉልህ ሚና ይኖረዋል የተባለ ሲሆን፤ አካታችነት፣ ፈጠራን፣ ተመጣጣኝ ዋጋን እና ዘላቂ እድገትን የሚያራምድ የፋይናንስ አቅርቦትን የሚያጎለብት፣ ምቹ እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ የዲጂታል ፋይናንሺያል አገልግሎቶችን መሆኑን ኩባንያው ለአዲስ ማለዳ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ለዚህም ሥራው ይረዳው ዘንድ በመላ የአገሪቱ ክፍሎች ከ30 ሺህ በላይ ወኪሎችን በማሰማራት በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባም ኩባንያው ገልጿል፡፡

በተጨማሪም ላለፉት 3 ዓመታት በኢትዮጵያውያን እና የውጪ አገር ባለሙያዎች የካቻ የሞባይል ገንዘብ አገልግሎት መስጫ ቴክኖሎጂን ሲያበለፅግ መቆየቱንም አስታውቋል፡፡

አገልግሎቱን በመጠቀም የሞባይል ሂሳብ መክፈት፣ ገንዘብ ገቢ እና ወጪ ማድረግ፣ አነስተኛ ቁጠባ፣ ዋስትና የማይጠየቅባቸው አነስተኛ ብድሮች፣ አነስተኛ የኢንሹራንስ አገልግሎቶች ፤ የቀጥታ ክፍያዎች ፤ ዓለም አቀፍ ሃዋላ፣ ገንዘብ ማስተላለፍ፣ የሞባይል አየር ሰዓት፣ የኤቲ ኤም ገንዘብ-አልባ ግብይቶችን መከወንና ሌሎች አዳዲስ አገልግሎቶችን ማግኘት እንደሚቻልም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የካቻ ዲጂታል ፋይናንሺያል ሰርቪስ አ.ማ የዋና ሥራ አስፈጻሚ አብርሀም ጥላሁንን ጨምሮ የሰባት ቦርድ አባላትን ሹመት ማጽደቁም ታውቋል፡፡

አብርሃም በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ16 ዓመታት በላይ ልምድ ያላቸው ሲሆን፤ በተለይ ባለፉት 8 ዓመታት በዲጂታል ባንክ አገልግሎት ሰፊ ልምድ እና ተሞክሮ ያላቸው ባለሙያ እንደሆኑ ኩባንያው ገልጿል።

ኩባንያው ለዘርፉ ዋና ተዋናዮች፣ አጋሮች እና ባለድርሻ አካላት የፊታችን ሐሙስ ሐምሌ 21 ቀን 2014 አግልግሎቱን በይፋ ለማስተዋወቅ ማቀዱም ተነግሯል።

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች