መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅወደ ውንብድና ያደገውን ዝርፊያ ለማስቆም እንሥራ!

ወደ ውንብድና ያደገውን ዝርፊያ ለማስቆም እንሥራ!

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከቱ መምጣታቸው ብቻ ሳይሆን ዘግናኝነታቸውና የሚፈፀሙበት መንገድ መራቀቁን እያደር መመልከት ይቻላል። ደቡብ አፍሪካና ኬንያን በመሳሰሉ አገራት ይፈፀማሉ ይባሉ የነበሩ የጭካኔ ውንብድናዎችን አሁን አገራችን ውስጥ መስማት እየተለመደ ነው።

ከመሸ የማይኬድባቸው ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በጠራራ ፀሐይም የማይታለፍባቸው ጎዳናዎች መበራከታቸውን ማንም ሊያስተውለው የሚችለው ጉዳይ ሆኗል። በተለምዶ “ሿሿ” እየተባለ የሚፈፀመው የማጭበርበር ሂደትን የመሳሰለ ወንጀልን የሚያስቆም አስተማሪ እርምጃ ባለመወሰዱ፣ ተግባራቸውን አግዝፈው ወደለየለት ውንብድና ሲገቡ ማየት ይቻላል።

ሌብነት በሚል የምናውቀው ኪስ የማውለቅም ሆነ ቤትን ሰርስሮም ሆነ አጥር ዘሎ የሚካሄድ ስርቆት፣ አድራጊውን ሌባ ከማስባሉ ባሻገር ተሰራቂው እንዳያውቅና እንዳይነቃ ተጠንቅቆ የሚደረግ እንደመሆኑ ወንጀልነቱ እንደሌሎቹም ስለማይከፋ ቅጣቱም በአንፃራዊነት እንደሚቀንስ ይታወቃል። በሌላ በኩል፣ ማጅራት መቺ እያልን የምናውቃቸው ዘራፊዎች ሳይደበቁ ምናልባት ማንነታቸውን ሰውረው አልያም ጨለማን ተገን አድርገው፣ መልካቸውን በኋላ እንዳንለያቸው ራሳችንን እንድንስት አድርገው ስለሚዘርፉ ደኅንነትንም አደጋ ላይ ይጥላሉ። በዚህም ሳቢያ ቅጣቱ ከተራ ሌባ የገዘፈ ይሆናል።

እንደወንበዴ የሚታዩት ሌሎቹ ነጣቂዎች ደግሞ ቀጥታ ተዘራፊውን በመግደል ሕይወትን ካጠፉ በኋላ ንብረቱን የሚገፉ ናቸው። እነዚህ ነፍሰበላ በመባል የሚታወቁት ከሁሉም የከፋ ዝርፊያን በመፈፀማቸው፣ የሚተካን ቁስ ለመውሰድ የማይተካውን ሕይወት በማሳጣታቸው ወንጀላቸው እጅግ የከፋ እንደመሆኑ ቅጣታቸውም ከባድ እንዲሆን ይጠበቃል።

ያም ሆነ ይህ፣ ዝርፊያም ሆነ ውንብድና ዓይነቱና ጉዳቱ ቢለያይም ሊቆም የሚገባ አገርን እንደአጠቃላይ የሚጎዳ ተግባር እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ቀስ በቀስም አሳዛኝ ውንብድናዎችን እየሰማን እንድንለማመደው መደረጉ እንደኅብረተሰብ ኹላችንንም የሚጎዳ መሆኑን አውቀን እንደማኅበራዊ አደጋ ተመልክተነው ልንረባረብበት ይገባናል።

የኑሮ ውድነትም ሆነ ሥራ አጥነት ውንብድና እንዲባባስ አድርገዋል ብሎ ምክንያት ማድረጉ ሌሎች እንዲገቡበት ያደርጋል እንጂ መፍትሄ አይሆንም። ኑሮ የከበደባቸው ወደእንደዚህ ዓይነት ተግባር እንዳይገቡ አስቀድሞ መተጋገዙ ሁሌም መኖር ያለበት ምግባር ነው። ሠው ሠውን እንዳይዘርፈው ማድረግ የጸጥታ ኃይሎች ተግባር ብቻ ሳይሆን የሁላችንም መሆን ነው ያለበት።

መንግሥት ሌብነትንም ሆነ ዝርፊያን ማጥፋት ያለበት ከራሱ ባለሥልጣናት ጀምሮ እንደሆነ ግልፅ ነው። ራሳቸው ከትልቁ መሶብ ላይ ከጋራው ሀብታችን ላይ እየዘረፉ ሌላው እርስ በርሱ እንዳይዘራረፍ ማድረግ እንደማይቻላቸው አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትፈልጋለች። እናም እንዲህ ባለ ድርጊት ውስጥ ያላችሁ ባለሥልጣናትም፤ ጊዜው ሳያመልጣችሁና ሳትዋረዱ በፊት የራሳችሁንም ሆነ የሌላውንም ችግር ለማስወገድ መፍጠን አለባችሁ ስትል አዲስ ማለዳ ታሳስባለች።

መንግሥት ሰላሜን ያስጠብቅልኛል ብሎ አምኖ የሚኖረው ኅብረተሰብ እንደእምነቱ ደኅንነቱን ሊጠብቅለት እንዳልቻለ እሙን ነው። ተደራጅተውና ታጥቀው በዱር በገደሉ እየተሽሎከሎኩ ንፁሐንን የሚገሉትን በየበረሓውና ጫካው አሳዶ በማጥፋት ከተማና ገጠር ገብተው ጭፍጨፋ እንዳያካሂዱ ማስቆም አለመቻሉ እያስነቀፈው ያለው መንግሥት፣ ጉያው ተቀምጠው ያልተደራጁና በቡድን ያልታጠቁ ዘራፊዎችን ማስቆም አለመቻሉ እጅግ የሚያስተቸው ተግባር ነው።

መንግሥትም ሆነ የፀጥታ ኃይሎች አልጠበቁኝም ብሎ ያሰበ የኅብረተሰብ ክፍል ምን ሊያደርግ እንደሚችል ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ተሞክሮ ዘራፊዎች ጭምር ሊማሩ ግድ ይላል። በማኅበረሰቡ የሚወሰዱ ዘግናኝ የቅጣት እርምጃዎች አንዴ ከተጀመሩ ማንም በቀላሉ ሊያስቆማቸው የሚችል አለመሆኑን አዲስ ማላዳ ልታስገነዝብ ትወዳለች።

ሌባና ዘራፊ ያስቸገራቸው አንዳንድ የአፍሪካ አገራት ያሉ ማኅበረሰቦች የራሳቸውን እርምጃ መውሰድ የጀመሩት አሁን ባይሆንም መነጋገሪያ የሆነው በቅርቡ ነው። እንደምንም ብለው በየተራ እየጠበቁ ድንገት አንዱን እጃቸው ላይ ከጣለላቸው፣ ጎማ አጥልቀውበት በእሳት እያቃጠሉት ሌላውን አስፈራርተው ሠፈራቸውን ሌባ እንዳይደፍረው ለማድረግ ተችሏቸዋል። በዚህ መንገድ መጠቀም የጀመሩ ማኅበረሰቦችን ሊሰርቅ ሲሞክር ድንገት የተነቃበት ሌባም እንዲያስጥሉት እየሮጠ ፖሊስ ጣቢያ ገብቶ እሰሩኝም እያለ ይለማመጥ እንደነበር ተዘግቧል።

ይህ ዓይነት ፍትሐዊነትን ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ መንገድን የሚያስቀር አካሄድ ዘግናኝ በመሆኑም ብቻ ሳይሆን አንዳንዴም ለበቀልና ለግል ቁርሾ ማስፈፀሚያ እንዲሆን እድል በመፍጠሩ መንግሥት ማስቆም ተስኖት እንደነበር ይነገራል።

በሌላ በኩል፣ ደርግ ሥልጣን ለቆ በነበረበት ወቅት የወያኔ ታጋይ ይባሉ የነበሩት ታጣቂዎች ከተማ የገቡ ሰሞን ዝርፊያና ውንብድና እንደአሁኑ ተባብሶ እንደነበር ጊዜውን ታዝቦ ያለፈው ያስታውሰዋል። ታዲያ የተባባሰው ወንጀል ያሳሰባቸው ታጣቂዎች በየገበያው ያደረጉት የማይረሳ ታሪክ ነበር። የሚሮጠውን እዛው በጥይት እየደፉ፣ አንዳንዶችም የግለሰብ በራፍ ላይ አንጠልጥለው እየገደሉ ለሌባ ያላቸውን ጥላቻና እርምጃ በግልፅ አሳይተው ተግባሩ እጅግ ቀንሶ እንደነበር ይታወሳል።

ይህ ዓይነት መንገድ ግን ሁሌም ውጤታማ ይሆናል ማለት ሳይሆን ተመሳሳይ ዘመኑን የሚመጥኑ መንገዶችን መንግሥትም ሆነ ማኅበረሰቡ ማሰብ እንዳለበትና ተመካክሮ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት አዲስ ማለዳ ትመክራለች።

ሠሞኑን የራይድ አገልግሎት ሲሠጥ የነበረ ወጣትን ለመዝረፍ ብለው እንደተሳፋሪ ገብተው ማጅራቱን በስለት ወግተው በመግደል መኪናውን ጨምሮ ያለውን ሀብት ይዘው የዘረፉት ወንበዴዎችን ጉዳይ ብዙዎች ተነጋግረዉበታል። በየክፍለ አገር አውራ ጎዳናዎች ያለውን ተመሳሳይ ዝርፊያ ማስቆም ቢከብድም ቅድሚያ ለመቀመጫዬ እንደሚባለው ከወዲሁ የመዲናዋም ችግር ሊታሰብበት ይገባል።

ኅብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት ብቻ ሳይሆን ቢያንስ እንዲህ ዓይነት አገልግሎት ሰጪዎች ለአደጋ እንዳይጋለጡ የሚከላከልላቸው መከለያ መስታወት እንዲኖራቸው ለመተጋገዝ ቢታሰብበትም መልካም ይሆናል። የመንግሥት አካላትም መኪናን ጨምሮ የተሰረቀ እቃ የት እንደሚሸጥ እውቀቱ ስላላቸው፣ ችግሩ ተባብሶ ከመቀጠሉ በፊት በዘመቻ መልክ አድኖ ማቆም ብቻ ሳይሆን ለሁልጊዜ የሚቀጥል ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በአፋጣኝ ወደ ሥራ ሊገባ ይገባል።


ቅጽ 4 ቁጥር 194 ሐምሌ 16 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች