ጉዞ ዓድዋ በዓድዋ ጉዞ ዋዜማ

0
1046

ከ124 ዓመታት በፊት ጥቅምት 2/1888 ነበር የዓድዋ ጉዞ ጥሪ የተደረገው፤ አዋጅም የተሰማው። በዚህ የዳግማዊ አጼ ምኒልክ አዋጅ የጀመረው የዓድዋ ጉዞ ዛሬ ድረስ ዓለም የማይረሳውና የኢትዮጵያንም ሥም አድምቆ ያስመዘገበው ድል መዳረሻው ሆኗል። የሚያስማሙ ታሪኮች፣ ሐሳቦችና ጉዳዮች የተዘነጉ በሚመስልበት በአሁኑ ጊዜ እንደ ዓድዋ ያሉ አንድነትን የሚያስታውሱ የታሪክ ክስተቶችን ማንሳት ተገቢ ነው። በዚህና ተያያዥ በሆነ ዓላማ የተጀመረው “ጉዞ ዓድዋ” ዘንድሮ 7ኛ ጉዞ ለማድረግ ምዝገባ እንደሚጀምር አስታውቋል።

በ2006 በሰባት የመገናኛ ብዙኀን እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ነበር የተቋቋመው፤ ጉዞ ዓድዋ። ይህ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በእግር የሚደረግና አንድ ሺሕ ዐሥራ ኹለት ኪሎ ሜትሮችን የሚሸፍን ጉዞ፣ መድረሻው የዓድዋ ድል እውን የሆነባቸው ተራሮች ናቸው። ጉዞውም ለ46 ተከታታይ ቀናት የሚካሔድ ሲሆን ተጓዦች ልክ የዓድዋ ድል በዓል በሚከበርበት ዕለት የካቲት 23 ቦታው ላይ ይደርሳሉ።

ረጅሙንና ከባዱን መንገድ በእግር ለመሔድ ታድያ ብዙዎች ይመዘገባሉ። ይህ የእግር ጉዞ የተለያዩ ለሕይወትም ጭምር የሚጠቅሙ ልምዶችን መቅሰሚያ ብቻ አይደለም፤ ታሪክ መጋራትም ነው። ኢትዮጵያን ከነክብሯ ትቆይ ዘንድ መስዋዕት ከመሆን ራሳቸውን ያልሰሰቱ የቀደሙ ኢትዮጵያውያን ካለፈባቸው ድካም፣ ከወጡት ውጣ ውረድ እንደመቅመስ ነው። ትውልድ ሲያመሰግናቸው እንደሚኖር፣ ሞታቸውና ድካማቸው ለከንቱ እንዳልሆነ መናገሪያም ነው፤ ጉዞ ዓድዋ። ተጓዦችም ይህን የዓድዋ ጉዞ መንፈስ ወደ ራሳቸው ለማቅረብ በጉዞው ወቅት መጠሪያ ሥማቸውን በጀግኖች ሥም እንደሚያደርጉና በሥማቸው ስለተጠሩት ጀግኖች ታሪክና ማንነተም በሚገባ እንደሚማማሩ ባለፈው ዓመት የጉዞ ዓድዋ መክፈጫ ሥነ ስርዓት ተገልጾ ነበር።

ፍሬወይኒ ተሾመ በ2009 የአምስተኛው ጉዞ ዓድዋ ተጓዥና ከዛ በኋላ ደግሞ ከጉዞው አስተባባሪዎች መካከል ናት፤ ተጓዦችን ከመመዝገብ ጀምሮ በጉዞው ቅድመ ዝግጅትና ሒደት አስፈላጊ ሥራዎች ላይ አለችበት። ብዙ ጊዜ ለልዩነት የሚዳርገው ታሪክን በሚገባ አለማወቅ ነው የምትለው ፍሬ፤ ጉዞ ዓድዋ ላይ ከዓድዋ ድል መነሻ ታሪክ ጀምሮ እስከ ድሉ ድረስ ያለው ታሪክ እየተነበበ ውይይት የሚደረግበት በመሆኑ ተጓዦች ከመከራከር ወደ አንድ መሆን እንደሚሻገሩ ትገልጻለች።

በአምስት ሰዎች የእግር ጉዞ ተጀመረው ጉዞ ዓድዋ፤ በስድስተኛው ጉዞ ላይ ሃምሳ ሦስት የሚጠጉ ተጓዦችን ይዞ እንደነበርና ከወትሮው በተለየም ከሐረርና ሽሬ ጉዞውን የተቀላቀሉ እንደነበሩ ታስታውሳለች። ይህም የተጓዦች ቁጥር ከዓመት ዓመት ከፍ ለማለቱ ማሳያ ነው።

ጉዞው ቀላል ነው ወይ? ለ46 ተከታታይ ቀናት የሚደረግ የእግር ጉዞ ቀላል ሊሆን እንደማይችል ተደራሲ መገመት አይቸግረውም። ፍሬወይኒ በአምስተኛው ጉዞ ዓድዋ ላይ በተጓዥነት ተሳትፋለችና እንዲህ አለች። “የአካል ጥንካሬን ይጠይቃል፤ ይህ ትግል (ቻሌንጁ) ደስ ይላል። ጉዞውን ማጠናቀቅ ለራስ የሆነ ነገር እንደማሳካት ነው።”
ታድያ ግን ቀላል ሆኖ አይደለም። ምናልባት ደግሞ እንደሚገመተው የመጀመሪያው ሰሞን ቀላልና አስደሳች ላይሆን ይችላል። ይህም ከሰውነት ጋር በተያያዘ ረጅም መንገዶችን የማያደርግ ሰውነት በ‘ስትራፖ’ እና እብጠት በመጀመሪያው ቀን አዳር ይፈተናል። እናም ሰውነት ጉዞውን እስኪላመደው ድረስ ፈተናው የሚከብደው የመጀመሪያ ሰሞን ነው ብላለች። እያደር ታድያ በየዕለት በሳህን እንደሚቀንሱለት የእህል ክምር፤ ቀሪ ቀናት እየቀነሱ ሲሔዱ “ኧረ ሊያልቅብን ነው!” ዓይነት ስሜት እንደሚፈጠር ትገልጻለች።

አካላዊው ፈተና መጀመሪያ መጥቶ እያደር ሲሻር ሌላ ፈተና ደግሞ ይመጣል፤ መተዋወቅ። መተዋወቅ ፈተና አይደለምን? መጀመሪያ ተጓዥ ጸባዩን ደብቆ ይቆይና በጊዜ ሒደት ግን የተደበቀ እውነተኛ ጸባይ ይወጣል። ይህ ተፈጥሯዊና ሰዋዊ ብሎም ኢትዮጵያዊ የሆነ ፈተና ሳይሆን ይቀራል!

እንዲህ ያለውና ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዘ ፈተና ጉዞውን በርትቶ ሳይፈትነው አልቀረም። በ2011 በአንድ ተጓዥ ምክንያት የተለያዩ ውዝግቦች ተነስተው ነበር። እንዲህ ያሉ ክስተቶች ዳግም እንዳይፈጠሩ ሊደረግ የሚችል አዲስ ነገር ባይኖርም ተጓዦች በሚፈርሙት ውል መሠረት እንዲስናገዱና፤ እርምጃ መወሰድ ካለበትም ጊዜ ሳይሰጡ እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል። የሥነ ምግባር ነገር በጉዞ ያሉ መረጃዎችንና ፎቶዎችን በማኅበራዊ ድረ ገጽ በግለሰብ ደረጃ ካለመልቀቅ (‘ፖስት’ አለማደረግ) የሚጀምር ነው።

ከዚህ በተረፈ 46 ቀናቱን ነጻ ማድረግና ለጉዞ መጠቀም የሚችል የትኛውም ጉዞ ለማድረግ ጤናው የሚፈቅድለት ሰው ሁሉ በጉዞ ዓድዋ እንዲሳተፍ በየዓመቱ ጥሪ ይቀርባል፤ ብዙዎች ይሳተፋሉም። ዘንድሮም ይኸው ጥሪ ነገ ጀምሮ የሚሰማ ይሆናል።

አዲስ ማለዳ ከፍሬወይኒ ጋር ባደረገችው አጭር ቆይታ ይህ ተነሳ እንጂ፤ ጉዞ ዓድዋ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ በነበረው ሒደት ያስገኛቸውና አስቀድሞ መነሻ ከሆነው ዓላማ አንጻር ያስመዘገባው አመርቂ ውጤቶች እንዳሉ ይነገራል። ይልቁንም የ2009 የበጎ ሰው ሽልማት በዓመቱ በቅርስና ባሕል ዘርፍ በአሸናፊነት በቀረበበት ጊዜ፤ የጉዞ ዓድዋ ስኬቶች በጉልህ የታዩ ነበሩ። እንደክብሪት ራስ አንዲት የምትመስል ትንሽ ሐሳብ እንዴት አገር ልታዳርስ እንደምትችልም የጉዞ ዓድዋ አጀማመርና ጉዞ ብቻውን ማሳያ ነው።

የትኛውም ተመልካች ወይም ታዛቢ ከዚህ ጉዞ ሊረዳው የሚችለው አንድ ጥሩ ስኬት አለ። ይህም ጥሪው ለሁሉም መሆኑ ነው። የተወሰነ የሚተዋወቅ ቡድን የደንቡን ለማድረስ የሚጓዝበት ሳይሆን በዓላማና በግብ የሚደረግ መሆኑ ያስታውቃል። ከዚህ በሻገር ደግሞ የበጎ ሰው ሽልማት በቅርስና ባሕል ዘርፍ ጉዞ ዓድዋን የ2009 ተሸላሚ ሲያደርግ ቀጥለው የተቀመጡትን መልካም ውጤቶች ዘርዝሮ ነበር። ከመጽሔቱ ላይ ቃል በቃል እንዲህ ተውሰናል፤ “ጉዞውን ከማካሔድ በተጓዳኝ፤ በየመንገዱ ተንቀሳቃሽ የመጻሕፍት ንባብ መሰናዶ በማካሔድ በየዓመቱ የሚጓዙ አባላትን በዓድዋ ጦርነት እና ድል ዙሪያ በቂ የሆነ ግንዛቤ እና የእውቀት ማጋራት ዝግጅቶችን ሲያካሒድ ቆይቷል። ከአንድ ወር በላይ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኀን ሰፊ ሽፋን የሚሰጠው የጉዞው የዕለት ተዕለት ውሎ፣ በዓሉ ከመድረሱ አስቀድሞ በበርካታው ሕዝባችን ላይ የካቲት 23 ዕለትን በጉጉት የመጠበቅ ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል።”

ጉዞ ዓድዋ ለዓድዋ ድል በዓል ትኩረት እንዲሰጥና በጉጉት የሚጠበቅ በዓል እንዲሆን ከመቀስቀሱ በተጓዳኝ ታድያ፤ መቀሌ ከተማ በሚገኘው የእንዳየሱስ ምሽግ ለማስለቀቅ ከጣልያን ጦር ጋር ሲዋጉ ሕይወታቸው ያለፉ ጀግና ኢትዮጵያውያን አጽም ተሰብስቦ በክብር እንዲያርፍ አስችሏል። በዛው ስፍራም (እንዳየሱስ) የካቲት 26/2009 በመቀሌ ዩኒቨርስቲ ወጪ “የጀግኖች ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ሙዝየም” የተሰኘ ጣራ አልባ ቤተመዘክር ተገንብቶ ተመርቋል።

በበጎ ሰው የ2009 ዓመታዊ መጽሔት ላይ ከዚህም በተጨማሪ የዓድዋ ጦርነት መንስኤ የነበረው የውጫሌ ውል የተፈረመበት ‘ይስማ ንጉሥ’ የተባለው ታሪካዊ ስፍራ ተከልሎ ጥበቃ እንዲደረግለት የሆነው አንድም በዚህ የጉዞ ዓድዋ ቀስቃሽነት ነው። አላበቃም፤ በዳግማዊ አፄ ምኒልክ የትውልድ መንደር በሆነችው ‘አንጎለላ’ የሚገኘው የዳግማዊ አፄ ምኒልክ መታሰቢያ ክሊኒክ እንዲከፈትና በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ድጋፍ ክሊኒኩ የጤና ጣብያ ሆኖ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ በኩል የጉዞ ዓድዋ ድርሻ የላቀ ነው።

የጉዞ ዓድዋ ተጓዦች በደረሱበት ሁሉ ያለው አቀባበል ከዓመት ዓመት እየደመቀ የሚሔድ ነው። ታድያ ይህን አጋጣሚ ችላ ያላለው ጉዞ ዓድዋ፤ ተጓዥ ቡድኑ በደረሰበት ሁሉ ስለ ዓደዋ ግንዛቤ የሚሰጡ መልዕክቶችን ከማስተላፍ አይቆጠብም። ይህም እያደር በበዓሉ አከባር ላይ ለመጣው ለውጥ ሰበብ ሆኗል። እንዴት ቢሉ፤ የድል በዓሉ በብቸኝነት ከሚከበርባቸው የአዲስ አበባ እና የዓድዋ ከተሞች አልፎ ከ28 በላይ የሚሆኑ የክልል ከተሞች እና በርካታ ሕዝብ የሚኖርባቸው የገጠር ወረዳዎች አሁን ዓድዋ ድል በዓል ይከበራል።

እንጨምር፤ የዓድዋ ጀግና የሆኑት ራስ አሉላ አባ ነጋ የቀብር ቦታ በሆነው የአባ ገሪማ ገዳም ውስጥ ለኹለቱም ጾታዎች ጉብኝት ምቹ በሆነ ቦታ ላይ ሐውልት እንዲቆም ተደርጓል፤ ይህም ጉዞ ዓድዋ ባመቻው ዕድል በአንድ ባለሀብት ምክንያት የተሠራ ነው። በድምሩ ጉዞ ዓድዋ የተረሱትን ታሪካዊ ኩነቶች በማስታወስና እንዲከበሩና እንዲከብሩ በማድረግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል ማለት ይቻላል። ቅርሶች እንዲጠበቁ፣ ለበለጠ ጥናትና ምርምር እንዲውሉና እንዲታወቁ በማድረግ በኩል የጉዞ ዓድዋ አስተዋጽዖ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይሆንም።

የዘንድሮው ሰባተኛ ጉዞ ምዝገባ ነገ ጥቅምት 2/2012 እንደሚጀምር የተለያዩ መረጃዎች በማኅበራዊ ድረ ገጽ በአስተባባሪዎቹ በኩል ተሰምተዋል። እንዲህ ያለው ታሪክን በተግባር እያዩ፣ ማኅበራዊ ትስስርን እያጠናከሩና እየተማማሩ የሚሔዱበት ሥራ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ፤ ከዓድዋ ባሻገር ያሉ መልካም የታሪክ ክስተቶችና አጋጣሚዎችንም በማውጣት በኩል አሁንም ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅ ግልጽ ነው። የዓድዋ ተጓዦች ጥሪውን ተከትለው የድርሻቸውን እያደረጉ ነው። ለመንግሥትና ለታሪክ ሰዎች ደግሞ ተጨማሪ ነጥብ የሚያሰጥ የቤት ሥራ ሆኖ ይቆያል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here