ድኅረ እውነት

0
1205

የድኅረ እውነትን ምንነት በመበየን የሚንደረደሩት በፍቃዱ ኃይሉ፥ ተጨባጭ ነው ያሉትን አንድ ድርጊት እንደ አብነት በመጥቀስ ሰዎች በጥሬ ሐቅ ላይ ተመስርተው ሳይሆን የሰሙት ነገር የፈጠረባቸውን ስሜት ተከትለው ይወስናሉ ይላሉ። የዚህ መዘዙ አገር እስከማፍረስ ይደርሳል በማለት የሚያስጠነቅቁት በፍቃዱ፥ መፍትሔው በዋነኛነት የመንግሥት ግልጽነት ነው ሲሉ መከራከሪያቸውን አቅርበዋል።

 

“ድኅረ እውነት ቅድመ ፋሺዝም ነው” – ቲሞቲ ስናይደር
እውነት ወይም ጥሬ ሐቅ አድማጭ አጥቷል። ሰዎች ስለሰሙት ነገር ሳይሆን የሰሙት ነገር በፈጠረባቸው ስሜት ውሳኔ የሚወስኑበት ዘመን ላይ ነን። ድርጊት በትክክለኛ በይዘቱ አይለካም። ይህንን ሁኔታ ምሁራን ‘ድኅረ እውነት’ (post truth) እያሉ እየጠሩት ነው። የካምብሪጅ መዝገበ ቃላት ድኅረ እውነት የሚለውን ሐረግ “ሰዎች ከሐቅ ይልቅ ስሜታቸውን የሚቀሰቅስላቸው እና እምነታቸውን የሚያረጋግጥላቸው ክርክሮችን የሚቀበሉበት ሁኔታ ነው” በሚል ይፈታዋል።
በአማራ ክልል ፕሬዚደንት እና አመራሮች እንዲሁም በኢታማዦር ሹሙ ላይ የተፈፀሙት ግድያዎች ከሰዎቹ ሞት በላይ፣ ከድርጊቱ አስፀያፊነት ባሻገር ፖለቲካዊ አንድምታው ነበር የሚያነጋግረው። ድርጊቱ ለሁሉም ሰዎች እኩል “ነውር” ድርጊት ሆኖ አልታየም፤ ገሚሶች ሲያዝኑ፣ ገሚሶች ትርፍ እና ኪሳራቸውን እያሰሉ ሲያወራርዱ ታይተዋል። ጥቂቶች “ከዚህ ድርጊት ጀርባ ያለው እውነት ምንድን ነው?” የሚለውን ለማጣራት ሲፍጨረጨሩ፥ ሌሎች ተዘጋጅቶ የቀረበላቸው የሴራ ትንተና አምነው ተቀብለዋል። በመንግሥት “ገዳይ ናቸው” የተባሉት ጄኔራል በተቃዋሚዎች “ጀግና ናቸው” ተብለዋል። ይህ ክስተት እና ተከትሎት የመጣው ትርክት የድኅረ እውነት ዘመን ላይ ስለመሆናችን በጣም ጥሩ ማሳያ ነው።

እውነትን መሠረት አድርጎ ሳይሆን ስሜትን የሚቀሰቅሱ ቃላቶችን እና ምስል ከሳች ገለጻዎችን በመጠቀም የፖለቲካ ተከታዮችን ማፍራት እና ለፖለቲካ ፍላጎት ማስፈፀሚያነት ማዋል ለረዥም ጊዜ የነበረ ቢሆንም፥ ‘ድኅረ እውነት’ የሚለው ሐረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ እንደዋለ በኦክስፎርድ መዝገበ ቃላት የተመዘገበው ግን በ1992 (እ.ኤ.አ.) ተብሎ ነው። የሰርብ ተወላጅ እና የአሜሪካ ዜጋ የሆኑት ጸሐፌ ተውኔት ስቲቭ ቴሲሽ አንድ መጽሔት ላይ በወጣ መጣጥፋቸው ላይ የዋተርጌት ቅሌት እና የኢራን ኮንትራ ቅሌት የሚባሉትን የአሜሪካ ፖለቲካ ገመናዎች መነሻ አድርገው ነው ድኅረ እውነት የሚለውን ሐረግ የጠቀሱት።

በእውነት ማመን እና ነጻነት
የዬል ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ቲሞቲ ስናይደር “ኦን ታይራኒ” በሚል ርዕስ የጻፉት እና ‘ከኻያኛው ክፍለ ዘመን የተገኙ ኻያ ትምህርቶች’ ያሏቸውን ያጋሩበት የምክር መጽሐፋቸው ላይ ዐሥረኛ አድርገው ያስቀመጡት “በእውነት እመኑ” የሚለውን ምክር ነበር። ፕሮፌሰሩ “ሐቅን መግደፍ ነጻነት መግደፍ ነው” (To abandon facts is to abandon freedom) ብለው ነው ይህንኛውን ምክራቸውን የሚጀምሩት። ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) “ገዳይም፣ ሟችም እኩል የተከበሩበት” በሚል የጠሩትን እና ከላይ የጠቀስነው የድኅረ እውነት ትርክት የፈጠረውን ውዥንብር “የሞራል ውድቀት” አድርገው አንድ መድረክ ላይ ተናግረው ነበር። ለዚህም የቀድሞው ኢሕዴን (ብአዴን/አዴፓ) ሊቀ መንበር የነበሩት ያሬድ ጥበቡ የሞራል እሴት አንጻራዊ ነው ብለው አጣጥለውታል። ፖለቲከኞች እና የፖለቲካ አስተያየት ሰጪዎች የድርጊቱን ምንነት በኀልዮቶች ለመበየን ሲፍጨረጨሩ የተዘነጋው ግን ፍትሕ ነው።

በዚህ መነሻ ትዊተር ላይ “በኢትዮጵያ ፖለቲካ ማስረጃ ካለው ክስተት ይልቅ ማስረጃ የሌለው የሴራ ትንታኔ የበለጠ ተቀባይነት ያገኛል” (እውነት/ሐሰት) የሚል መጠይቅ አቅርቤ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከመለሱት 250 ሰዎች መካከል 84 በመቶዎቹ “እውነት” መሆኑን ተሥማምተውበታል።

ግድያው በአማራ ክልል ስለተከሰተ እና በአገራችን ያለውን ትልቅ ገመና ግልጽ ስላወጣው እንጂ ሁሉም ክልሎች ውስጥ ያለ እውነታ ነው። በተለይም ደግሞ በፖለቲካ ፉክክር ውስጥ ጉልህ ድርሻ ያላቸው ሦስቱ ክልሎች – ኦሮምያ፣ አማራ፣ እና ትግራይ – ፖለቲከኞቻቸው የድኅረ እውነት ስልቶችን በመጠቀም የሥልጣን ጫወታቸውን የሚጫወቱባቸው ክልሎች ናቸው።

ቲሞቲ በመቀጠልም እንዲህ ይላሉ “ምንም ነገር እውነት ካልሆነ፣ ባለሥልጣናትን መተቸትም አያስፈልግም፤ ምክንያቱም ለመተቸት በቂ ምክንያት አይኖርም”። 2016 (እ.ኤ.አ.) ለአሜሪካ ፕሬዚደንትነት እየተወዳደሩ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ እንደ እውነት ከጠቀሷቸው ነገሮች ውስጥ 78 በመቶዎቹ ሐሰት መሆናቸው እንደተረጋገጠ ቲሞቲ በመጽሐፋቸው አክለው ይገልጻሉ። ሆኖም ይህ የሐሰት ቅስቀሳ ትራምፕን ወደ ዋይት ሐውስ ወስዷቸዋል።

በኢትዮጵያም መጪው ምርጫ በሐሰት በተገነቡ አጓጊ ገጽታዎች፣ በሴራ ትንተና በተፈጠሩ በደሎች – በድኅረ እውነት – የሚመራ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። በተቃራኒው በቀኝ ዘመም አክራሪነት የሚታመሱት ጠቅላላ አውሮፓውያንም ይሁኑ፥ የብሬግዚት ውሳኔ እና የትራምፕ መመረጥ ጦስ ቀማሽ እንግሊዛውያንና አሜሪካውያን እንዲህ ያለውን ፈተና የሚቋቋሙበት በርካታ አቅም አላቸው። ከእነዚህም ውስጥ የተቋሞቻቸው ጥንካሬ፣ የመንግሥታቶቻቸው እና የባለሥልጣኖቻቸው ግልጽነት፣ የብዙኀን መገናኛዎቻቸው ገለልተኝነት እና ሥነ ምግባር፣ እንዲሁም የሲቪል ማኅበራቶቻቸው ተጽዕኖ ፈጣሪነት ያድናቸዋል። እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ከተቋማት ይልቅ ኀላፊነት የማይሰማቸው ግለሰቦች የበለጠ ተደማጭነት ያላቸው ሰዎች ያሉባቸው አገራት ግን ድኅረ እውነትን ተቋቁመው እንኳን ነጻ ስርዓት ሊገነቡ፥ የተገነባውንም ይዘው መቆየት እንዳይችሉ ይገዳደራቸዋል።

“ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው”
ፕሮፌሰር ቲሞቲ በናዚ ጀርመን፣ ከአይሁዶች መጨፍጨፍ ቀደም ብሎ፣ ብዙዎች ቀስ በቀስ የናዚን ‘ድኅረ እውነት’ እየተቀበሉ ነበር ይላሉ። ለዚህም የሚጠቅሱት የወቅቱን ሁኔታ ቅልብጭ ባለ ቋንቋ የጻፉትን የሮማ ጸሐፌ ተውኔት ዩጂን አዮኔስኮ ነው። ማስታወሻቸው እንዲህ ይነበባል። “የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች፣ ተማሪዎች፣ ምሁራን ቀስ በቀስ ወደ ናዚነት እየተቀየሩ ነበር። አንድ በአንድ የብረት ዘብ እየሆኑለት ነበር። መጀመሪያ ላይ አንዳቸውም ናዚ አልነበሩም። ዐሥራ አምስት ገደማ እየሆንን እንገናኝና ናዚዎቹን የሚተች መከራከያ እያነሳን እንነጋገር ነበር። ቀላል አልነበረም… ከጊዜ ወደ ጊዜ አንድ ጓደኛችን እንዲህ አለ፦ ‘በርግጥ ከእነርሱ ጋር አልሥማማም፣ ግን አንዳንድ ነጥቦች ላይ፣ ለምሳሌ አይሁዶች… እንደሆነ አልደብቃችሁም’ ምናምን አለ። ይኼ ነበር ምልክቱ። ከሦስት ሳምንታት በኋላ፣ ይህ ሰውዬ ናዚ ሆነ። መዋቅራቸው ውስጥ ገብቶ ሁሉንም ነገር ተቀበለ። ወደ አውሬነት ተቀየረ። ወደ መጨረሻው ገደማ፣ ሦስት ወይም አራታችን ብቻ ነበርን በተቃውሟችን የዘለቅነው።”

በኢትዮጵያም እየሆነ ያለው እንዲህ ነው። መጀመሪያ ማውገዝ፣ ከዚያ መለሳለስ፣ በመጨረሻም መጀመሪያ ያወገዟቸውን ቡድኖች ሆኖ መገኘት የፖለቲከኞች እና ተራ ተርታ ተከታዮች ባሕሪይ ነው።

ሳንሱር መፍትሔ አይደለም
ብዙዎች ድኅረ እውነትን እንደ አሁናዊ ክስተት በመቁጠር እና ለምሣሌ ማኅበራዊ ሚዲያን በመቆጣጠር እና በይነመረብን በመዝጋት የሚቆጣጠሩት ይመስላቸዋል። ነገር ግን ሳንሱር ለድኅረ እውነት ማበብ ሁነኛ መሣሪያ ነው። የማኅበራዊ ሚዲያ ቀላል እና ፈጣን የመረጃ ፍሰቶች የድኅረ እውነት ትርክቶች ስርጭትን ቀላል እና ፈጣን አደረገው እንጂ፥ ለዚህ የመጨረሻውም የመጀመሪያውም መድረክ አይደለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት እና ሳንሱር እጅና ጓንት ናቸው። በጥንት ጊዜ የነገሥታቱ ዜና መዋዕል ጸሐፊዎችም ይሁኑ አዝማሪዎች ነገሥታቱ መሥማት የሚፈልጉትን ይነግሯቸዋል እንጂ እውነቱን ለመንገር ድፍረቱ አልነበራቸውም። ድፍረቱ የነበራቸው ከነበሩም ነገሥታቱ ዘንድ አይደርሱም፣ ከደረሱም በሰላም የመሰናበታቸው ነገር አጠራጣሪ ነው። የሆነ ሆኖ በወቅቱ ለእውነት ተናጋሪነት የሚመረጡት እረኞች እንደነበሩ ይነገራል። ነገሥታቱ “እረኛ ምን አለ?” ይላሉ ይባላል፤ እረኞቹ ያሉትን በትክክል ስለመሥማታቸው ግን እርግጠኛ መሆን አይቻልም። የአሁን ፖለቲከኞችም እንዲሁ ናቸው። የተከበቡት “አዎ፣ አበጃችሁ” በሚሏቸው ተከታዮች ብቻ ነው።
መገናኛ ብዙኀን በአግባቡ ሥራ በጀመሩበት በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ንጉሡ በጋዜጦቹ ላይ የሚወጡበት መንገድ፣ ሥማቸው የሚጻፍበት መንገድ ሌላው ቀርቶ የሚታተመው ፎቷቸው የሚመረጥበት (እሳቸውም ይሳተፉበታል) መንገድ በጥንቃቄ የንጉሡን እና አስተዳደራቸውን ገጽታ የማግነን ዒላማን የታጠቀ ነበር። ሌላው ቀርቶ የታኅሣሥ 1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት እስከ ዛሬ ድረስ እንደተራ ክስተት “የታኅሣሡ ግርግር” በመባል የሚታወሰው ንጉሠ ነገሥቱ “መፈንቅለ መንግሥት” የሚለውን ማዕረግ እንዲሰጠው ስላልፈለጉ ነው።

የደርግ አስተዳደርም ቢሆን ግድያዎቹን እና አምባገነናዊ ስርዓቱን የሚገልጽበት ድኅረ እውነት ነበረው። የራሱን ፕሮፓጋንዳ የሚቀለብሱ ኅትመቶች እና ጥበባዊ ሥራዎች እንዳይወጡ ሳንሱር ማድረጊያ ይፋዊ ተቋምም ነበረው። ኢሕአዴግም ከሳንሱር እስከ የመልስ ፕሮፓጋንዳ ድረስ ዘዴ አድርጎ ይጠቀም ነበር። “ልማታዊ ጋዜጠኝነት” የድኅረ እውነት ማሰራጫ የዳቦ ሥሙ ነበር። ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጸሐፍት ቀጥሮ ትርክት እስከመፍጠርም ደርሷል። አሁንም በይነመረብ በመዝጋት የአንድ ወገን የመረጃ ፍሰትን ብቻ ‘እውነት’ን ለመቆጣጠር ጥረት እየተደረገ ነው።

ድኅረ እውነት ዴሞክራሲን አያጎናጽፍም። ይልቁንም ፅንፈኝነትን እና ጦርነትን ይደግሳል። ድኅረ እውነትን ለመከላከል ፍቱን መድኀኒቱ ሳንሱር ሳይሆን ግልጽነት ነው፤ በዋነኝነት የመንግሥት ግልጽነት። ዜጎች እና ጋዜጠኞች ባለሥልጣናትን እና ፖለቲከኞችን በሚመለከት በቂ መረጃ ማግኘት የሚችሉበት ስርዓት ከተረጋገጠ ሐቅ ስሜትን የሚያሸንፍበት ዕድል ሊፈጠር ይችላል። ከሁሉም ከሁሉም በላይ ግን ዋናው ራስን ማዳን ነው፤ ሁሉም ሰዎች ራሳቸውን በድኅረ እውነት ትርክቶች እንዳይጠመዘዙ በየጊዜው መጠራጠር አለባቸው፤ “ስለምሰማው እና ስለምናገረው ነገር ምን ያህል እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?” ይህንን ጥያቄ መጠየቅ ካልቻልን በግጭት አፋፍ ላይ ያለችውን ኢትዮጵያ፣ ውድቀቷን ልናፋጥነው እና ነዋሪዎቿም እንደ ዜጋ ሰላም እና ፍትሕ ልናጣ እንችላለን የሚል ስጋት አለኝ።
“እርግጠኝነትን መሻት የሰው ልጅ ተፈጥሮ ነው፤ ምሁራዊ ባሕሪ ግን አይደለም” – በርትራንድ ራስል።

በፍቃዱ ኃይሉ የሰብኣዊ መብቶች ተሟጋች እና ጸሐፊ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው befeqe@yahoo.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here