መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛከክተት ወደ ጸሎት

ከክተት ወደ ጸሎት

ከሠሞኑ መነጋገሪያ ከነበሩ ጉዳዮች መካከል መንግሥት ለጋራ ጸሎት እንዘጋጅ ያለበት ረዘም ያለ ጽሑፍ አንዱ ነበር። መግለጫ በተባለው በዚህ ጥሪ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ ለደቂቃ ፈጣሪን እንዲያመሰግኑ ጥያቄ ወይም ጥሪ ቀርቧል።

ከዚህ ቀደም ለሕዝብ አጠቃላይ የጦርነት የክተት ጥሪ ሲያቀርብ የኖረው መንግሥት፣ የዘመቻ አስተሳሰቡ ባይቀየርም አሁን አሰላለፉን ቀይሮ ኑ ተሰብሰቡና እንጸልይ ማለቱ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዕይታ ጠፉ፣ ታመሙና ለሕክምና ውጭ ሄዱ በሚባልበትና ደጋፊዎቻቸው ጭንቀት ላይ እንደሆኑ በሚነገርበት በዚህ ጊዜ፣ የጸሎት መርሐ ግብር ለሁሉም መጠራቱ ባይገርምም፣ እናመስግን መባሉ ብዙዎችን ግራ አጋብቷል።

አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ እየተመለከትን ማረን እያልን መጮኽ ሲገባን ላደረግክልን ሁሉ እናመሰግናለን ማለት ምን የሚሉት ሹፈት ነው በማለት ሂደቱን የገመገሙትም ነበሩ። ሕዝብ እያለቀ መንግሥትም የሚይዘው የሚጨብጠው ባጣበት በዚህ ጊዜ እንደቀደመው ጊዜ ምሕላ ሊባል ሲገባ፣ ምስጋና መሆኑ ተገቢ ነው ወይ ያሉም ነበሩ።

በደስታችሁ ጊዜ ትዝ ያላላችሁን ፈጣሪ አሁን ሲጨንቃችሁ ማስታወሱ ተገቢ ባይሆንም፣ ጭራሹኑ ከመቅረት ማርፈዱ ይሻላል ብለው ሐሳቡ ላይ አስተያየት የሰጡም አልጠፉም። ፈጣሪ መኖሩን የረሳን እስኪመስል እርስ በርሳችን የተጠፋፋነውን ይቅር ተባብለን ምሕረት ሳንጠይቅ ለፈጣሪ ምስጋና መሰባሰቡ ምን ፋይዳ አለው ያሉም ብዙዎች ናቸው።

በሌላ በኩል፣ መንግሥትና ሃይማኖት ተለያይተዋል እየተባለ በሚደሰኮርበት በዚህ ዘመን በመንግሥት እንዲህ ዓይነት ጥሪ መቅረቡ ዋና የሕግ ፅንሰ ሐሳብን የሚሽርና አጠቃላይ መርሆዎችን የሚጥስ ነው በሚል ትችት የሰነዘሩም ጥቂት አይደሉም። መንግሥት ቢጨንቀው እንኳን ለሃይማኖት ተቋማት ጥሪ አቅርቦ እነሱ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋሉ እንጂ የተገላቢጦሽ መሆን አልነበረበትም ያሉ ሂደቱን ተችተዋል።

የመንግሥትን ጥሪ ተከትሎ የሃይማኖት ተቋማቱ የጋራ ምክር ቤት ምላሽ መስጠቱም አግራሞትን የፈጠረባቸው በርካቶች ናቸው። ወዲያው በሚባል ሁኔታ ያለማንገራገር ሁሉም ለጸሎት መርሐ ግብር መስማማታቸው ተገልፆ ጥሪው ቀናትና ደቂቃ ተወስኖለት እንዲስተጋባ ተደርጓል።

ይህ ሁሉ ጥሪ ሲደረግ ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት የባሰ ችግር ውስጥ እንዳትገባ ፈጣሪ ረድቷታል የሚል አንድምታ በሕዝቡ ውስጥ እንዲሰርፅ የተፈለገ ሲሆን፣ ለምንስ እንዲህ ደረጃ ወርደን እንድንጠፋፋ ፈጣሪ ፈቀደ ብሎ መጠየቅም ግድ ያላል ያሉ አሉ።

ያም ተባለ ይህ፣ አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል በሀብቱ በጉልበቱ ወይ በዘመዱና በትጥቁ በሚመካበት በዚህ ጊዜ፣ መተማመን በፈጣሪ ነው በሚል እሳቤ ፊቱን ያለምንም ጥርጥር ወደፈጣሪው እንዲያዞርና ብቸኛ መመኪያው እንዲያደርገው የሚያደርገው ጥሪ ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ ብዙዎች ይስማሙበታል። ጥሪውን ማንም ያድርገው፣ ዓላማው እንደውስጣችን ስለሚለያይ ወደፈጣሪ መቅረቡ በራሱ የተሻለ መሆኑ በአብዛኛው ማኅበረሰብ ተቀባይነት ያገኘ ይመስላል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

- ይከተሉን -Social Media
Previous articleእኛም ኮራን!
Next article22 ቢሊዮን ብር
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች