እኛም ኮራን!

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

የሴቶች እኩልነት ሲባል ነገሩ የተፈጥሮ እኩልነት ተደርጎ መታየት እንደሌለበት እሙን ነው። ሴትና ወንድ ፈጽሞ እኩል ሊሆኑ አይችሉም። እንደዛ ከሆነ ሴት ወንድን በመውለድ ትበልጠዋለች፤ ወንድም አባት የመሆን ድርሻ በመያዝ ይበልጣታል ማለት ነው። አንዳቸው የሌላቸውን ድርሻ ሊወክሉ ቢችሉም ፍጹም ሆነው ግን ሊከውኑ የሚችሉት በተፈጥሮ የታደሉትን የየራሳቸውን ድርሻ ነው።

ስለዚህ እኩልነት ሲባል፤ እኩል መብትን የተመለከተ ነው። ይህም እንደ ሰው ኹለቱም ሊያገኙት የሚገባና የሚታደሉት መብት ነው። የቀረውን ደግሞ በስምምነት ቅድሚያ የሚሰጣጡበት ይሆናል። ከዛ ባሻገር ግን በተፈጥሮ ሴቶችና ወንዶች የተለያዩ ናቸው። ይህም አካላዊ ብቻ ሳይሆን ሥነ ልቦናዊ ውቅርም የሚጨምር መሆኑ አያጠራጥርም።

ብዙ ጊዜ ታድያ ከዚህ መረዳት ባልመነጨ መልኩ የሚከራከሩ ሰዎች አትሌቲክስን በምሳሌ ያነሳሉ። ‹ሴቶች በአትሌቲክሱ የሚሮጡበት የሩጫ ሰዓት ከወንዶቹ አንጻር ይጨምራል። ይህ የሆነው ወንዶች ስለሚበልጡና የተሻለ አቅም ስላላቸው ነው።›› የሚል ነው ማሳያ ተደርጎ የሚቀርበው።

አዎን! ሴቶችና ወንዶች የተለያዩ ናቸው። በእርግጥ በብዙ ልምምድ አካልን ለማንኛውም እንቅስቃሴ መገንባት እንደሚቻል እሙን ነው። ከዛ ውጪ ግን እንዲህ ያለው ማሳያ በትክክል ሴቶችና ወንዶች መካከል ያለውን ተፈጥሮአዊ ልዩነት ለማስረዳት መጠቀስ የሚችል ነው።

ይህን አሁን ለማንሳት ምክንያት የሆነኝ፤ ኢትዮጵያ በ18ኛው የዓለም ሻምፕዮና በኹለተኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጣትን ሜዳልያ በብዛት ያመጡት ሴቶች መሆናቸው ነው። እነዚህ ሴት አትሌቶቻችን ኮራንባቸው እንጂ ከወንዶች የተሻለ ነጥብ አላመጡም አላልናቸውም። ምክንያቱም ሥራቸውን በአግባብ ሠርተው ምርጡን ውጤት ያስገኙት እነሱ ናቸው። ቀላል ውድድር ሆኖ አይደለም፤ እነርሱም ግን ለውድድሩ ቀላል ሆነው ስላልተገኙና ስለተባበሩም ነው አሸናፊ ሆነው እኛንም አሸናፊ ያስባሉን።

ይህ አንድ ቁምነገር ይነግረናል። ይህም ልናሸንፍ የምንችልበት የየራሳችን ሩጫና ውድድር እንዳለን ነው። አትሌቲክሱ ላይ ማንም ሰው ሴቶችን ከወንዶች አያነጻጽርም። ውጤት ሲያመጡም ውጤት ያመጣውን ያደንቃል፤ የደከመውን ደግሞ ይወቅሳል። ወቀሳውም ጾታ ተኮር ሳይሆን ሥራ ተኮር ነው፤ ለምን በቡድን አልሠሩም፣ ለምን አልተባበሩም ወዘተ የሚል ነው።

ሩጫሽ የምንድን ነው? ልጆች የማሳደግ? ቤተሰብ የመንከባከብ? የምትሠሪበት ተቋምን የዓመት እቅድ የማሳካት? ሕልምሽን የመኖር? ምኞትሽን የማሳካት? እውቀትሽን የማሳደግ? ሩጪ። አትሌቶቻችን ለልምምድ ዳገት ቁልቁለቱን ሌሊት እየተነሱ ሲሮጡ የሚያያቸው ብዙ አይደለም። እነሱም የሚያሳዩት ወርቃቸውን ነው። ከበረታሽ ወርቁ ጋር ትደርሺያለሽ። ያም ከወንዶች አንጻር የሚመዘን አይደለም፤ የአንቺ ድል፤ የአንቺ ወርቅ ነው።

ውድ አትሌቶቻችንን ስለሰጡን ፈገግታና ስላደሱልን ተስፋ እናመሠግናለን!

መቅደስ ቹቹ


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች