መነሻ ገጽርዕስ አንቀፅየመንቀሳቀስ መብት ያለመድሎ ይከበር!

የመንቀሳቀስ መብት ያለመድሎ ይከበር!

የሰው ልጅ በተፈጥሮው የፈለገበት ተንቀሳቅሶ እንዲሠራ የሚያስገድደው ባህሪ ያለው ነው። እንደዛፍ በአንድ ቦታ ተወስኖ ለመኖር አስፈላጊው የሆኑ ግብዓቶች እንዲመጡለት ማድረግ የሚቻል አይደለም። ይህ የመንቀሳቀስ ተፈጥሯዊ መብት በዓለም ዐቀፍ ድንጋጌዎችም ሆነ በየአገራቱ በሚደነገጉ የሕግ ፅንሰ ሐሳቦች ውስጥ ሳይሸራረፍ እንዲተገበር የተቀመጠ ነው።

ተንቀሳቅሶ የመሥራትም ሆነ የመዘዋወር መብት በሕግ ከተቀመጠለት ገደብ ውጭ በምንም መልኩ መገደብ እንደሌለበት አዲስ ማለዳ ታምናለች። አንድ ሰው ሕግን ጥሶ አልያም ወንጀለኛ መሆኑ በፍርድ ቤት ተረጋግጦበት ከአንድ ውስን ቦታ ውጪ እንዳይንቀሳቀስ ከሚገደበው ውጪ ወደፈለገበት የመዘዋወር መብቱ ሊገደብ አይገባም። አንድ ግለሰብ በገዛ አገሩ ይቅርና ስደተኛ ሆኖ በገባበት አገር ጭምር ፈቃድ አግኝቶ መዘዋወርና መሥራት ይችላል።

ከሥራ በተጨማሪም ለጉብኝትም ሆነ ሕክምናን ማግኘትን ለመሳሰሉ ለማናቸውም ዓላማ መጓጓዝ መብቱ እንደሆነ ይታወቃል። በገዛ አገሩም ሆነ በሌላ አገር የሚኖር ሕጋዊ ሰው በዘሩም ወይም በትውልዱም ሆነ በሃይማኖቱ ተለይቶ እገዳ ሊጣልበት እንደማይገባ ሕግ ብቻ ሳይሆን ሕሊናም ያስገድዳል። ይህ የመንቀሳቀስ መብትን የሚያስገኘውን መርህ ግን ኹሉም በፍትሐዊ መንገድ ሲጠብቀው አይታይም። በአገራችን ኢትዮጵያም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ፅንሰ ሐሳቡ በጥቂት ባለሥልጣናት ይሁንታ ላይ ተንጠልጥሎ ይታያል።

ለገፅታ ግንባታ ሲባል የወሎ ረሀብተኞች አዲስ አበባ እንዳይገቡ በ66 እና 77 ድርቅ ወቅት ተከልክለዋል ተብሎ ከሚነገረው ስሞታ የባሰ አሁን እየተፈጸመ እንደሆነ የሰርክ ወሬ ሆኖ ለዜና እንኳን መብቃት አለመቻሉ የሚያሳዝን ነው። አዲስ ማለዳ በዜጎች ላይ የመንቀሳቀስ መብትን የሚገድብ አድሏዊ አሠራርን አጥብቃ ትቃወማለች።

የሞት አደጋን ሸሽተው ከታጣቂዎች አፈሙዝ ለመራቅ ብለው ከኖሩበት ቀዬ የሚንቀሳቀሱ መንገድ ላይ በመንግሥት አካላት እየታገዱ ወዳልፈለጉበት ቦታ መወሰዳቸው የተለመደ መሆኑ ማብቃት ይኖርበታል። አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ አካላት ብቻ ሳይሆኑ ጊዜ የሰጣቸው ጉልበተኞችም ለሰባት ዓመታት ያህል የዘጉትና ኅብረተሰቡ እንዳይንቀሳቀስ ያደረጉበት አካባቢ በርካታ ነው።

በደቡብ ክልል አማሮ ወረዳም ሆነ ወለጋ ዞንን በመሳሰሉ አካባቢዎች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ተንቀሳቅሰው እንዳይሠሩ ብቻ ሳይሆን፣ ከሞት ሸሽተው እንዳያመልጡ መንገድ ተዘግቶባቸው ቀስ በቀስ እንዲያልቁ ሲደረግ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡም ዝም ማለት አልነበረበትም።

አንድ ማንኛውም ዜጋ እንደባለሥልጣናቱ ለመንቀሳቀስ መንገድ ይዘጋለት ባይባልም፣ ከማንም እኩል ይህ የመዟዟር መብቱ ሊከበርለት ይገባል። መንግሥት ይህንን መብቱን ማስከበር ከተሳነው በጊዜ አሳውቆ ኅብረተሰቡ በትብብር መብቱን እንዲያስከብር አልያም አማራጭ እንዲፈልግ መደረግ እንዳለበት አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። በአሸባሪዎችም ሆነ በጉልበተኞች የሚዘጉ መንገዶችን ማስቀረት መንግሥት ቢሳነው እንኳን፣ ራሱ እንደነሱ ኬላ አበጅቶ ዜጎችን እየለየ ‹አንተ እለፍ! አንተኛው ተመለስ!› የማለት መብትን ማግኘት በፍፁም የለበትም።

አንድ ዜጋ በየትኛውም መንገድ ሌላ ዜጋ እንቅስቃሴን ሊከለክለው አይገባም። በተለይ ከአራት እና አምስት ዓመታት ወዲህ መንገድ እየዘጉ የፈለጉትን ማገድና የፈለጉትን በመልቀቅ የተጀመረው አሳፋሪ እርምጃ፣ ምንም ዓይነት ቅጣት ባለማስከተሉ አሁን ራሱ መንግሥት ተመሳሳይ ተግባር ውስጥ በግላጭ እንዲገባ ማድረጉ እሙን ነው። በተለይ ጦርነቱ ከተጫረ ወዲህ ከሰሜን ወደ መካከል አገር የሚደረጉ ጉዞዎች ተስተጓጉለው እንደነበር ለማንም ግልፅ ነው።

የአገርን ሰላም ለማስከበር ተብለው በየቦታው የሚደረጉ ፍተሻዎች በመርህ ደረጃ ትክክል አይደሉም ማለት ባይቻልም፣ እነሱን ተገን በማድረግ በየኬላው ፈታሾቹ የማይፈልጉትን ሠንደቅ ዓላማ የመሳሰለ ዓርማና ልብስን እየነጠቁ ማውደም ተገቢ አለመሆኑ ሊታመንበት እንደሚገባ አዲስ ማለዳ ስትናገር ቆይታለች።

ይህ በግዑዝ አካል የጀመረ ክልከላና እገታ፣ አሁን በሰው ላይ በግልፅ ያለምንም ምክንያት እየተፈጸመ ይገኛል። በተለይ ከወሎ አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት የሚመጡ መንገደኞች ሰንዳፋን በመሳሰሉ የኦሮሚያ ክልል ከተሞች እንዲቆሙ፣ እንዲመለሱና እንዲጉላሉ እየተደረገ መሆኑ ይነገራል። መታወቂያቸው እየታየ ከአማራ ክልል የመጡና የክልሉን መታወቂያ የያዙ እንዳያልፉ በጅምላ የሚደረግ ክልከላ ላልተፈለገ ጥላቻ ከመዳረጉ ባሻገር፣ በማኅበራዊ ትስስሩ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ቀላል የሚባል አይደለም።

ተመሳሳይ የክልል መታወቂያ ይዘው ኦሮምኛ የሚናገሩ ብቻ እየተለዩ እንዲያልፉ መፈቀዱ እጅግ ሊታፈርበት የሚገባ ተግባር ነው። ይህን ዓይነት መድሏዊ አሠራር መንግሥት በጽሑፍ ወስኖ ለበታቾቹ እንደማያስተላልፍ ግልጽ ቢሆንም፣ እንዲህ ዓይነት መንግሥትን ሊያፈርሱ የሚችሉ ስሞታዎች በሚሰሙበት ወቅት መንግሥት ለራሱ ሲል መቀጣጫ እርምጃ ካልወሰደና ለሌላው መማሪያ ካላደረገው መዘዙ ከባድ እንደሚሆን ግልጽ ነው። አዲስ ማለዳ በተለይ በደብረ ብርሃን አቅጣጫ ከጊዜ ወደጊዜ እየተፈፀሙ የመጡትን የመንቀሳቀስ መብትን የሚገድቡ ተግባራትን በፅኑ ታወግዛለች።

የሕክምና ቀጠሮ ኖሯቸው እንዳይገቡ መከልከል ብቻ ሳይሆን፣ ያለምንም ምክንያት የአንድ ክልል ነዋሪዎችን ብቻ ለይቶ አትገቡም ማለቱ አፓርታይዳዊ አሠራር መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። የነጭና የጥቁር መንገድ ተብሎ በቅኝ ግዛት ዘመን በሌሎች አገራት እንደሚፈፀመው፣ አልያም የፍልስጤምና የእስራኤላዊ መተላለፊያና መኖሪያ ቦታዎች ተብለው አሁንም ድረስ እንደተከለከሉት እኛም አገር ይህን መሰል አስተሳሰቦች ሊቀሩ ይገባል። የኔ ብቻ የሚባል የተለየ መሬት በቁማችን ብቻ ሳይሆን አስከሬናችንም ማግኘት ስለማይኖርበት ይህን የማያባራ እልቂት ሊያመጣ የሚችል ጅምር እንቅስቃሴ በእንጭጩ ማስቀረት ይገባል። አዲስ አበባ የኹሉም ኢትዮጵያዊ ብቻ ሳትሆን የመላው ሰው ልጆች ከተማ መሆኗን አምነን፣ አንዱ ጎሳ ከልካይ ወይም ባለቤት መምሰሉ ሊያበቃ ይገባል ስትል አዲስ ማለዳ አጽንዖት ሰጥታ ታሳስባለች።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች