መነሻ ገጽዜናወቅታዊበአስከፊው ድርቅ የሞት ጥላ ያንዣበበባቸው ነፍሶች

በአስከፊው ድርቅ የሞት ጥላ ያንዣበበባቸው ነፍሶች

በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት ዝናብ ባለማግኘታቸው በከፍተኛ ድርቅ የተጎዱ የአርብቶ አደር አካባቢዎች፣ እንስሶቻቸውን በድርቅ አጥተዋል። በስፋት በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም ብዙም ትኩረት ባልተሰጠው በደቡብ ክልል በተከሰተው ድርቅ እንስሶቻቸውን ያጡ ዜጎች፣ አሁን ላይ በድርቅ እንዳለቁት እንስሶቻቸው የሞት እጣ እንዳይደርሳቸው ስጋት እንዳላቸው እየገለጹ ነው።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች የተከሰተውን ድርቅ እና ያደረሰውን ጉዳት ተከትሎ በድርቁ በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብለው በተለያዩ አካላት በይፋ እውቅና የተሰጣቸው አካባቢዎች በመዘዋወር የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ክትትል በማድረግ ያዘጋጀውን ባለ 50 ገጽ ሪፖርት ባለፈው ሐምሌ 19/2014 ይፋ አድርጓል።

ኢሰመኮ በድርቅ የተጎዱ አካባቢ ተጎጂዎችን አነጋግሮ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ያነጋገራቸው የድርቅ ተጎጂዎች ለነፍሳቸው ያላቸውን ስጋት፣ “አጥንታችን እንደከብቶቻችን መሬት ላይ ተበትኖ እንዳይቀር እንፈራለን” በማለት እንደገለጹለት በሪፖርቱ ገልጿል። በድርቅ የተጎዱ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንደሚሉት፣ በኢትዮጵያ በአርብቶ አደሩ አካባቢ የተከሰተው ድርቅ ከ40 ዓመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ ድርቅ መሆኑን ነው።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ በተከሰተው ከፍተኛ ድርቅ ምክንያት የቤት እንስሳት እልቂት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሲሆን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ምግብና ውሃ ፍለጋ ቤታቸውን ለቀው እንዲፈናቀሉና ተረጂ እንዲሆኑ አድርጓል።

ኢሰመኮ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ክትትል የተደረገባቸውና ትኩረት የተሰጣቸው ቦታዎች በተደጋጋሚ በድርቅ የሚጠቁ አካባቢዎች ቢሆኑም፣ የተከሰተው ድርቅ ከዚህ በፊት ከነበሩት አደጋዎች በተለየ መልኩ የተራዘመ፣ ማለትም ከኹለት እስከ አራት የዝናብ ወቅቶች ያልዘነበበት እንዲሁም ሰፊ ቦታዎችን ያካለለ መሆኑን ተመልክቻለሁ ብሏል። በዚህም ማኅበረሰቡ እንደ ከዚህ ቀደሙ ወደ ተሻሉ ቦታዎች ተዘዋውሮ ከድርቁ ተጽዕኖ ለማምለጥ አለመቻሉን የገለጸው ኢሰመኮ፣ በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ ከእንስሳት እልቂት ለሰዎች ሕይወት አስጊ እየሆነ መምጣቱን ከተጎጂዎቹ ሰምቻሁ ብሏል።

በሕጻናት ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሠራው ዓለም ዐቀፉ ‹ሴቭ ዘ ችልድረን› በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል የተከሰተው ድርቅ የዱር እንስሳትን ሳይቀር ተፈጥሯዊ ያልሆነ ባህሪ እንዲያሳዩ ምክንያት መሆኑን ሰኔ 9/2014 ባወጣው መግለጫ ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው። ተቋሙ በወቅቱ ባወጣው መግለጫ በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ የዱር እንስሳት “ከተፈጥሮ ውጪ” ሕጻናትን እንዲተናኮሉ ምክንያት ሆኗል ብሏል።

“ጦጣዎች ከጫካ ወርደው እቃ የተሸከሙ ሕጻናትና ሴቶችን እያጠቁ ነው” የሚለው የሴቭ ዘ ችልድረን መግለጫ፣ ሰዎች የያዙትን ነገር ውሃ ነው ብለው በማሰብ ነጥቀው ለመጠጣት ወይም ዕቃ ለመውሰድ እንደሚሞክሩም ጠቅሷል።

የሕጻናት ቤተሰቦች ጦጣዎችን በዱላ ለመከላከል እየተገደዱ መሆኑን የሐረሪ ክልል፣ የሶማሌ ክልል እና የምሥራቅ ኦሮሚያ ክልሎችን ጨምሮ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ክልሎች የሴቭ ዘ ችልድረን አካባቢ ኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ አብዱራዛቅ አሕመድ ገልጸዋል። ከጦጣዎች በተጨማሪ ድኩላዎች ምግብ እና ውሃ ፍለጋ ባልተለመደ ሁኔታ ከሰዎች ቤት እየገቡ መሆኑንም ተናግረዋል።

የዱር እንስሳት ተፈጥሯዊ ባልሆነ ባህሪ ሰዎችን እንዲተናኮሉ እና ለአርብቶ አደሩ እንስሳት እልቂት ምክንያት የሆነው ድርቅ፣ በተለይ በቂ ውኃና ምግብ ባለመኖሩ ሰዎች ለተለያዩ የጤና እክሎች እንዲዳረጉ ምክንያት መሆኑን ኢሰመኮ ባደረገው ክትትል መመልከቱን በሪፖርቱ ጠቁሟል።

“በምግብ እጥረት ምክንያት ሰውነታቸው የከሳ፣ ሆዳቸውና እግራቸው ያበጠ በዚህም ታመው የተኙ ሰዎች አሉ።” የሚለው ኢሰመኮ የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማት በአካልም በኢኮኖሚም ተደራሽ አለመሆናቸውንም ባደረገው ክትትል ማረጋገጡን አስታውቋል።

የተከሰተው ድርቅ ጥንካሬ እና ቆይታ በ40 ዓመታት ታይቶ እንደማይታወቅ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቢሰማም፣ ለድርቁ የተሰጠው ምላሽ በቂ አለመሆኑን ዓለም ዐቀፍ የተራድኦ ድርጅቶችና ኢሰመኮ ያወጧቸው መረጃዎች ያመላክታሉ።

ኢሰመኮ ድርቅ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ክትትል አድርጎ ይፋ ባደረገው ሪፖርት መሠረት የጤና አገልግሎቶችን ለራሳቸው ማግኘት ለማይችሉ የድርቁ ተጎጂዎች የጤና ግልጋሎቶችን ተደራሽ ከማድረግ ረገድ የተሠሩ ሥራዎች ውስን ናቸው። በዚህ ምክንያት ተጋላጭ የኅብረተሰቡ ክፍሎች በተለይም አረጋዊያን እና ሕፃናት ሕይወታቸው አደጋ ላይ ወድቋል ተብሏል።

በድርቅ ምክንያት ተፈናቅለው በተፈናቃይ ካምፖች ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ተግባራት አለመከናወኑ እና የተፈናቃዮችን ጤና አደጋ ውስጥ ሊከት የሚችል እንደ ወረርሽኝ የመሰለ በሽታ ተጋላጭነት ነበር። ይህም የድርቅ ተጎጂዎችን የጤና መብት ከማረጋገጥ አንጻር ክፍተት እንዳለ የኢሰመኮ የምልከታ ሪፖርት ያመላክታል።

የኢሰመኮ የክትትል ሪፖርት በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ድርቁ ስለተከሰተበት አውድ እና አጀማመር፣ ለድርቅ ስጋት፣ ቅነሳ፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ እና ዝግጁነት የተሰጠውን ትኩረት እንዲሁም ድርቁ ያስከተላቸው ጉዳቶች እና የተሰጡ ምላሾች ከሰብአዊ መብቶች አንጻር የዳሰሰ ነው። በዚህም በኦሮሚያም ሆነ በሶማሌ ክልል በቅድመ ማስጠንቀቅ እና በዝግጁነት ረገድ የተሰበሰቡት መረጃዎች አግባብነት ባላቸው የብሔራዊ የአደጋ ክስተት ስጋት ሥራ አመራር ፖሊሲና ስትራቴጂ እንዲሁም በአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 363/2008 በተካተቱ ድንጋጌዎች መሠረት የድርቁን አደጋ ቅነሳ፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ዝግጅት እንዲሁም የማሳወቅ ሥራዎች በይፋ አለመሠራታቸው ለድርቁ አደጋ ምላሽ የዘገየ መሆኑን ኢሰመኮ ባደረኩት ክትትል ተገንዝቤያለሁ ብሏል።

በምሥራቅ አፍሪካ የተከሰተው ድርቅ በ40 ዓመታት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ሲሆን፣ ድርቁ በሶማሊያ እና ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የረሃብ ቀውስ አስከትሏል። በኢትዮጵያ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንዲሁም በሶማሌ ክልሎች ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሏል። 185 ሺሕ የሚጠጉ ሕጻናት ገዳይ በሆነ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ ነው ተብሎ እንደሚገመትም የተራድኦ ደርጅቱ ሴቭ ዘ ችልድረን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው። ድርቁ በከፋባቸው በሶማሊያ፣ በኬንያ እና በኢትዮጵያ አካባቢዎች አንድ ሰው በየ48 ሰከንዱ በረሃብ እየሞተ መሆኑ መገለጹም የሚታወስ ነው።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን ምንም እንኳን በደቡብ ክልል ኮንሶ አካባቢ የተከሰተውን ድርቅ እንደ ሶማሌና ኦሮሚያ ክልል ትኩረት እንዳልሰጠው ቢገለጽም፣ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች በድርቁ እንስሳት ቢያልቁም የሞተ ሰው የለም ብሏል። የኢሰመኮ የክትትል ሪፖርት እንደሚያመላክተው ደግሞ ሰውነታቸው አልቆና ከስተው በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙ ነፍሶች መኖራቸውን ነው።

- ይከተሉን -Social Media

ይህ አስከፊ የድርቅ አደጋ በሰዎች ሕይወት ላይ ያንዣበበውን ለሞት የሚጋብዝ ረሃብ ለማስቀረት በሚደረጉ የአደጋ ምላሽ ሥራዎች፣ ለድርቁ አደጋ ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑ የኅብረተሰቡ ክፍሎች ንቁ፣ ነፃና ትርጉም ያለው የተሳትፎ ዕድል እንደማያገኙ ኢሰመኮ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል።

በዚህም ሴቶች ቀጥተኛ እና በቂ የተሳትፎ ዕድል አለማግኘታቸው፣ የሚሰጡ ምላሾች ድርቁ በሴቶች ላይ ያደረሰውን ጫና ከግምት ያላስገባ እንዲሆን አድርጓል ተብሏል።

ድርቁ እና ለድርቁ ምላሽ በመስጠት ሂደት በሰብአዊ መብቶች አፈጻጸም ላይ የተከሰተውን አሉታዊ ተጽዕኖ እና ጥሰትን በተመለከተ ሪፖርቱ በተለይም በሕይወት፣ በምዝገባ፣ መረጃ፣ ተሳትፎ እና ተጠያቂነት፣ በመጠጥና በንጽሕና መጠበቂያ ውኃ የማግኘት መብት እና በምግብ መብት፣ በንብረትና መተዳደሪያ መብት፣ እንዲሁም በትምህርት፣ በጤና እና በባህል መብቶች ላይ ትኩረት አድርጓል። እንዲሁም የአገር ውስጥ ተፈናቃዮችን ጨምሮ ድርቁ ለመብቶች ጥሰት ተጋላጭ በሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች ላይ ያደረሰውን ጉዳትም ዳስሷል።

የውኃ መብትን በተመለከተ ለክትትሉ በተመረጡ ቦታዎች የድርቁ ተጽዕኖ መሰማት የጀመረው የመጠጥና የንጽሕና ውኃ ምንጮች መቀነስ እና መድረቅን ባስከተለ የውኃ እጥረት የተነሳ መሆኑን እና ለዚህ ሁኔታ የሚሰጠው ምላሽ እንደየአካባቢው የተለያየ ሲሆን፣ የመጨረሻው አማራጭ ግን ውኃን በተሽከርካሪ ማከፋፈል መሆኑን አስታውሷል። አያይዞም ክትትሉ በተደረገበት ወቅት ድርቁ በተከሰተባቸው አካባቢዎች በመሠረተ ልማት አለመኖር፣ በነዳጅ እጥረት፣ በውኃ ዋጋ መናር ወይም በውኃ አቅርቦት ውስንነት ምክንያት ውኃ የማያገኙ ሰዎች በርካታ መሆናቸውን ኢሰመኮ በሪፖርቱ አመላክቷል።

በድርቁ ጉዳት ሳቢያ በተለይ በቂ ውኃና ምግብ ባለመኖሩ ሰዎች ለተለያዩ የጤና እክሎች መዳረጋቸውን የሚገልጸው የኢሰመኮ ሪፖርት፣ በምግብ እጥረት ምክንያት ሰውነታቸው የከሳ፣ ሆዳቸውና እግራቸው ያበጠ በዚህም ታመው የተኙ ሰዎች መኖራቸውን ጠቁሟል። የጤና ግልጋሎቶችን ለራሳቸው ማግኘት ለማይችሉ የድርቁ ተጎጂዎች፣ የጤና ግልጋሎቶች ውስን በመሆናቸው ተጋላጭ የኅብረተሰቡ ክፍሎች በተለይም አረጋዊያን እና ሕፃናት ሕይወታቸው አደጋ ላይ መውደቁ አያጠራጥርም ሲል ኢሰመኮ አሳስቧል።

ደርቁ በሰዎች ላይ ካስከተላቸው ችግሮች መካከል መፈናቀል አንዱ ሲሆን፣ የተፈናቀሉ ዜጎች ከውኃና ከጤና አገልግሎት ማጣት በተጨማሪ የትምህርትና የመጠለያ ችግር እንደገጠማቸው ኢሰመኮ አረጋግጧል። በዚህም እጅግ በርካታ ተማሪዎች በድርቁ ምክንያት ትምህርታቸን ያቋረጡ ሲሆን፣ ይህም በትምህርት መብት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽዕኖ አድርሷል ተብሏል።

ዜጎች መጠለያ የማግኘት መብት ያላቸው ቢሆንም፣ በድርቁ ምክንያት ከነባር መኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ፣ ያለ በቂ መጠለያ እጅግ በጣም በርካታ ሰዎች መኖራቸው ሌላው ድርቁ በመኖሪያ ቤት ያደረሰው ተጽዕኖ መሆኑን ኢሰመኮ ጠቁሟል። ኢሰመኮ በክትትል ሪፖርቱ ላይ እንዳብራራው መጠለያን በተመለከተ የተደረገው ድጋፍ እጅግ በጣም ውስን መሆኑን ነው።

ኢሰመኮ ድርቁን ለመቋቋም በአፋጣኝ እና በሂደት ወይም በመካከለኛ ጊዜ ውስጥ ሊተገበሩ ይገባል በማለት የተለያዩ ምክረ ሐሳቦችን በመከፋፈል ያቀረበ ሲሆን፣ በተለይም የፌዴራል፣ የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች መንግሥታት በአፋጣኝ ሊተገብሯቸው ይገባል ካላቸው መካከል አንዱ በመረጃና በምዝገባ ሥርዓት የታገዘ፣ አሳታፊ የሆነ፣ የተጠያቂነት ሥርዓት የተዘረጋለት እንዲሁም ከፍላጎት ጋር የተመጣጠነ ምላሽ ማቅረብ፣ ማሰራጨት እና ክትትል ማድረግ የሚለው ነው።

- ይከተሉን -Social Media

በተጨማሪም ኮሚሽኑ መንግሥት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በድርቁ ሳቢያ ለተፈናቀሉ ድጋፍ ፈላጊዎች ባሉበት ቦታ እርዳታ እንዲያገኙ እንዲያደርግ፣ እርዳታ የሚገኝበትን ቦታ እና ሁኔታ እንዲያሳውቅ እና ያለ በቂ መረጃ ለሚፈናቀሉ ሰዎች አፋጣኝ እርዳታ ለማድረግ የሚያስችል የመጠባበቂያ እርዳታ ዝግጁ እንዲያደርግ ጠይቋል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆናቸውን የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ሴቭ ዘ ችልድረን የገለጸ ሲሆን፣ ወደ 30 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ወይም ሩብ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልገዋል ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች