ፋኖ… ፋኖ…ፋኖ…!

0
1917

ከሕወሓት ጋር ይደረጋል የተባለው ድርድር የተቀመጠለት ቅድመ ሁኔታ፣ ሰላም ይመጣል ብለው ተስፋ የሚያደርጉትን ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገባ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ ምንአልባት ሕወሐት እንደሚዝተው ጦርነት ከከፈተ፣ የጦር ሜዳና መረማመጃ የሚያደርገው የአማራና የአፋርን ምድር መሆኑ ይታወቃል። እናም በአማራ ክልል ፋኖዎች ላይ የሚካሄድ የማሰርና የማሳደድ ዘመቻ ቀርቶ የማሠልጠን ሥራ ሊሠራ ነበር የሚገባው የሚሉት ግዛቸው አበበ፤ ከባለፈው ሳምንት የቀጠለ ሐሳባቸውን እንዲህ አጋርተዋል።

ከባለፈው ሳምንት የቀጠለ

‹ዱቄት ሆኗል፣ ለመሰብሰብ በማይቻልበት ሁኔታ ተበትኗል!› የተባለው ሕወሐት ወደ ትግራይ ገዥነቱ ተመልሷል። ሕወሐት የክልሉን ፖሊስና የትግራይ መከላከያ የሚለውን ኃይል እያደራጀ ነው። ሕወሐት ዱቄት ሆኗል የተባለው ከማን ጋር እንደራደር፣ ሕወሐት ለድርድር የሚበቃ ቁመና የሌለው ሆኖ ወድሟል ለማለት ተፈልጎ ነበር። አሁን ደግሞ ከሕወሐት ጋር ስለመደራደር ዜናዎች የሚሰሙበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።

የእንደራደር ጥሪ የቀረበለት ሕወሐት ቅድመ ሁኔታዎችን በመደርደር እያንገራገረና አስፈላጊ ከሆነ በጦርነት መፍትሄ ለማግኘት የሚያስችል ሙሉ አቅም እንዳለው በመዛት ላይ ነው። ይህን መሰል ነገር ባለበት በዚህ ወቅት በአማራ ክልል ‘ሕገ-ወጥ ታጣቂዎችን የማሳዳድ ዘመቻ ማካሄድ’ በሚል ሽፋን ፋኖዎች እየተጠቁ ነው የሚል እሮሮ በመላ አማራ ምድር በዝቶ መሰማቱ ግራ አጋቢና አሳሳቢ ነገር ነው። ከየትኛውም ኃይል ጥቃት ሰንዝሬአለሁ የሚል ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም፤ ሰኔ ወር 2014 ሕወሐት በአማራ እና በኤርትራ ላይ ጦርነት ከፍቶ የነበረ መሆኑ ተሰምቷል።

በሌላ በኩል ሕወሐት የኤርትራ ጦር በድንበር አካባቢ የሚገኙ የትግራይ ከተሞችን በከባድ መሣሪያ መደብደቡን ተናግሯል። ሕወሐት በኤርትራና በአማራ ኃይሎች የተያዘብኝ መሬት እስካልተመለሰልኝ ጦርነት መክፈቴ አይቀሬ ነው ሲል መሰማቱ በሌላ በኩል ደግሞ ከወደ አማራ ክልል በሕወሐት እጅ የገባው የራያና የጠለምት ምድር መመለስ ይገባዋል፣ ሕወሐት ወልቃይት ጸገዴን መልሶ ለመያዝ መቋመጡን አላቋረጠም የሚል አቤቱታ መሰማቱ፣ የኤርትራ መንግሥትም በዓለም ዐቀፉ ፍርድ ቤት የተበየነልኝን ባድመንና አካባቢውን ለሕወሐት አሳልፌ አልሰጥም ስለሚል የሰሜን ኢትዮጵያ የጦርነት ደመና ያልተገፈፈ መሆኑ፣ ሰላም የሚባለው ተፈላጊ ነገር በጭላንጭል ደረጃም ቢሆን የማይታይ መሆኑን መገመት አያዳግትም።

ጥቅምት 2012 ጦርነት መፈንዳቱን ተከትሎ በኹለቱም ወገኖች ጦርነቱ ሕዝብ በሕዝብ ላይ የዘመተበት ግብግብ እንደሆነ ተደርጎ በሰፊው ፕሮፓጋንዳ ተሠርቷል። ጦርነቱ በትግራይ ምድር ሲስፋፋም ሕወሐቶች ሕዝቡን ጥለው ራሳቸውን ለማዳን በትግራይ ቆላማ ቦታዎች ሲሽለኮሎኩ ቆይተዋል። ጦርነቱ ወደ አማራና አፋር ክልል ሲስፋፋ ደግሞ ብልጽግናዎች ሕዝቡን ትተው ራሳቸውን ለማዳን ወደ መሀል አገር ፈርጥጠዋል። እነዚህና የመሳሰሉት አጋጣሚዎች መፈጠራቸው ኹለቱም ወገኖች ሕዝብን ከሕዝብ አደገኛ ማናቆር ውስጥ በመዶል ራሳቸውን ከእልቂቱ ማዶ ደብቀው ለመኖር ማሰባቸውን የሚያጋልጥ ጉዳይ ነው።

ሕወሐት ወደ ቆላ ተምቤን በረሀዎችና ወደ ተከዜ ሸለቆ ሲፈረጥጥ ሕዝቡን መሣሪያ ያለው በመሣሪያ፤ የጦር መሣሪያ የሌለው በአካፋ፣ በዶማ፣ በመጥረቢያና በቢላዋ ሳይቀር መፋለሙን እንዲቀጥል አበክረው ቀስቅሰዋል። እንዲሁ ጦርነቱ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ሲዛመትም ብልጽግናዎች ሕዝቡ ባገኘው የጦር መሣሪያና በቤቱ ውስጥ በሚገኝ ስለታም ቁሳቁስ ሕወሐቶችን እየተፋለመ ከተማውን፣ መንደሩንና ቤቱን እንዲጠብቅ ግዳጅ መሰል ትዕዛዝ ይሰጡ እንደነበረ የሚታወስ ነው።

ሕወሐቶችም ሆኑ ብልጽግናዎች ራሳቸውን ለማዳን እየፈረጠጡ ሕዝብ ታንክ፣ መድፍ፣ ዲሽቃ እና መትረየስ ጭምር ታጥቆ የሚመጣውን ኃይል እንዲጋፈጥ ማዘዛቸው ወይም ጥሪ ማድረጋቸው ብዙ ትርጉም ያለውና ሁሉም ሰው ቆም ብሎ በቅጡ ሊመረምረው የሚገባ አደገኛ ነገር መሆኑ ፈጽሞ ሊዘነጋ አይገባውም።

ስለ መደራደር ጭምጭምታ በሚባል ደረጃ የሚሰማ ነገር አለ። ቢሆንም ሕወሐት የአፍሪካ ኅብረት ወኪል ሆነው አዲስ አበባና መቀሌ ሲመላለሱ የከረሙትን የቀድሞውን የናይጄሪያውን መሪ የኦባሳንጆን ዐይን ከዚህ በኋላ ለማየት አልፈልግም ብሏል፡፡ ለድርድሩ ቅድመ ሁኔታዎች ያላቸውንም ወደ ሰባት የሚሆኑ ነጥቦች አስቀምጧል። ከመደራደሪያ ነጥቦቹ ውስጥ ትግራይ ውስጥ ለተፈጸመ ግፍ ተጠያቂ የሆኑ የብልጽግና ሹምምንትም ሆኑ ሌሎች ኃይሎችን ለፍርድ ይቅረቡ የሚል አቋም የያዘ ሲሆን፣ በ1984 ወደ ትግራይ ያጠቃለላቸውን የወሎና የጎንደር መሬቶች ወደነበሩበት (ወደ ትግራይ) ከተመለሱ ብቻ ድርድሩን እንደሚቀበለው አሳውቋል። ይህም ሁሉ ድርድሩ ሳይጀመር እንዲፈርስ ፈልጓል የሚል ግምገማ ለማስቀመጥ የሚያስገድድ ሆኗል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሚሰጡ ወገኖች በአንድ በኩል ሕወሐት የልብ ልብ እንደተሰማውና ‘ሶፍት ዌራቸውን ያወለቅሁባቸው ሮቦቶቼ’ እያለ የሚያጣጥላቸውን ብልጽግናዎችን ማፍረክረኩና ማደናገሩ እየተሳካለት መሆኑን እርግጠኛ ሆኗል ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ከዓመት በላይ የሆነ ጊዜ በወሰደው ጦርነት ያለቀው የትግራይ ወጣትና ጎልማሳ ብዙ ነውና ሕወሐት ለቤተሰቦቻቸው መርዶ የሚነግርበት ሰላማዊ ጊዜ እስከ ዘላለሙ እንዳይመጣ ስለሚፈልግ ሁሌም በጦርነት ውስጥ መኖርን መርጧል ሲሉ ይደመጣሉ።

ራሱን ከደሙ ንጹሕና ከተጠያቂነት ነጻ አድርጎ ሌላውን ወገን ብቻ ተጠያቂ የሚያደርገው ሕወሐት በሰሜን ዕዝ ላይ እንዲሁም በወሎና በአማራ ክልሎች ያደረሰውን ሰቆቃ የረሳ መምሰሉ የሚገርም ነው። የፌዴራሉ መንግሥትም በተመሳሳይ እነዚህን በደሎች ችላ ባይ መሆኑ ወይም ለተጎጂዎቹ ፍትሕ ማፈላለጉን የረሳ መምሰሉ ለትዝብት የሚዳርገውና ‘ድርድሩ ስለ አገርና ስለ ሕዝብ ሲባል የሚካሄድ ነው ወይስ ለብልጽግና ቡድን የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም?’ ብሎ ጥያቄ ለማንሳት የሚገፋፋ ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ ሕወሐት እንደሚዝተው ጦርነት ከከፈተ፣ የጦር ሜዳና መረማመጃ የሚያደርገው የአማራና የአፋርን ምድር መሆኑ እየታወቀ፤ በአማራ ክልል ይህን መሰል ሰፊ ቅሬታን የሚያጭር የማሰርና የማሳደድ ዘመቻ እያካሄደ ነው። ይህን ማድረጉ ዘመቻው የሚመራውና የሚካሄደው ጦርነት ሲነሳ ሕዝብን፣ ወረዳቸውንና ዞናቸውን ጥለው ለመሸሽ ቀዳሚ በሚሆኑት የብአዴን-ብልጽግና ሰዎች መሪነት መሆኑ ‘ዘመቻው የሚካሄደው ማንን ለመጥቀም እና ማንን ለመጉዳት ነው?’ የሚል ጥያቄን ለማንሳት የግድ የሚል ነው። ፋኖዎችን ከማሳደድ፣ ፋኖዎች እንዲበተኑ ከማድረግ ይልቅ በልማት ሥራ ላይ አሰማርቶና ወታደራዊ ሥልጠና እየሰጡ መጭውን ጊዜ መጠበቅ አይሻልም ወይ ብሎ መጠየቅም ተገቢ ነው።

ጦርነቱና ዝርክርክነት የሞላበት አመራር ያስከተለው ሞት፣ ስንክልናና ውድመት በቅጡ ሳይሰላ በአማራ ክልል ውስጥ የእርስ በርስ መናቆር ሊያስከትል የሚችል ነገር እየተከሰተ ነው። የአማራ ፋኖ ከአማራ ልዩ ኃይልና ከአማራ ፖሊስ ጋር መጋጨቱም ሆነ በፋኖዎችና በብአዴን-ብልጽግና አባላት መካከል በአንዳንድ አካባቢዎች መበቃቀልና ደም መቃባት መከሰቱ ውሎ አድሮ ለአማራ ውድመትና ውርደት መንገድ ከመጥረግ በስተቀር ሌላ ትርጉም ያለው ነገር አይደለምና በአማራው በኩል ያሉ ሁሉም ወገኖች ቆም ብለው ቢያስቡ መልካም ነው።

ፋኖዎችን በማደራጀትና አንድ ወጥ አመራር ስር ሆነው በሥልት እንዲንቀሰቀሱ በማድረግ በአማራ ሕዝብ ላይ የተጋረጠውን የሕልውና አደጋ ለመመከት መዘጋጀት ሲገባ በብልጽግናዎች በኩል የማን አለብኝነት ቀረርቶዎች ያለ ልክ በጩኸት መስተጋባታቸውና በሌላው ወገን ደግሞ ፋኖዎች ተገደሉ፣ ፋኖዎች ታሰሩ፣ ፋኖዎች ተሰወሩ ወዘተ… የሚሉ እሮሮዎች ያለ ማቋረጥ መሰማታቸው የአማራን ሕዝብ ግራ በማጋባት ላይ ይገኛል። በእርግጥ ለችግሩ ሁሉ የብአዴን ብልጽግናዎችን ብቸኛ ተጠያቂዎች ማድረግ ተገቢ አይደለም። በክልሉ ውስጥ ረዘም ላለ ጊዜ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ፣ የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻል እንደሚባለው ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የለየለት ውንብድናና ዝርፊያ የሚፈጽሙ አጥፊ ኃይሎችም አሉ።

ስለ ትጥቅና ስለ ታጣቂዎች ሲነሳ አንድ ሊካድ የማይገባው ሐቅ አለ። በ2010 ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ የአማራ ብሔርተኝነትን ማራመድ በሚል ሽፋን በአውራጃዊ ጠባብነት ውስጥ ተቀርቅረው በክልሉ ሕዝብ ላይ ችግር የሚፈጥሩ ግለሰቦች ጥቂት አይደሉም። ይህን መሰሉ ብስለት የጎደለውና ለዘመኑ የማይመጥን አስተሳሰብ በአማራ ክልል ወስጥ የነገሠው አብን የሚባለው ቡድን መፈጠሩን ተከትሎ ነው። ‘አማራ የጥቃት ሰለባ የሆነው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ’ ስለሚል ነው በሚል ሽፋን ኢትዮጵያዊነትን የሚያንኳስሱ ግለሰቦች የተባዙት አብን የተባለው ቡድን ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ነው።

በክልሉ ውስጥ አብን የተባለው ቡድን እነ በረከት ስሞዖን የጠፈጠፉት የሕወሐት ተላላኪ ቡድን ነው የሚል ሐሜት በሰፊው ሲናፈስ የነበረውም ለዚህ ነው። አብን መወለዱን ተከትሎ በአማራ ክልል ውስጥ በብዙ ወረዳዎችና ከተሞች ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች ለመንቀሳቀስና ለመሰብሰብ ሲሞክሩ በጥባጭ የሆኑ የመንጋ አመጾች መካሄዳቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። እነዚህን መሰል ለዴሞክራሲ ጸር የሆኑ የመንጋ አመጾች በደብረ ታቦርና በደብረ ማርቆስ ጀምረው ወደ ባሕርዳርና ጎንደር ከተማ ተስፋፍተው በየጊዜው ዜና ለመሆን በቅተው ነበር።

መንጋዎቹ ስብሰባዎችን ገና ከጅምሩ ከመከልከል ጀምሮ መካሄድ የጀመሩ ስብሰባዎችን በጩኸት በማወክ እስከ መበተን የደረሱ ሕገ-ወጥ የሆኑ ተግባራትን ፈጽመዋል። አልፎም በባሕርዳርና በአንዳንድ አካባቢዎች የጦር መሣሪያዎችን ይዘው በመውጣት ጸረ-ዴሞክራሲያዊነታቸውን ብቻ ሳይሆን ጸረ-ሕዝብነታቸውንም ዐሳይተዋል። ይህን የመንጋ እንቅስቃሴ ያስቆሙ ዘንድ ጥያቄ ይቀርብላቸው የነበሩ የክልሉ ከፍተኛ የጸጥታ ኃይል ኃላፊዎች የመንጋዎቹን ድርጊት እንደሚደግፉ የሚያሳብቁ መልሶችን ይሰጡ እንደነበረና ከአዲሰ አበባ ወደ አማራ ክልል በመሄድ ለመንቀሳቀስ የሚሞክሩ የፖለቲካ ቡድኖችን (ከባልደራስ በስተቀር) ፊት ይነሷቸው እንደነበረ ሊካድ የማይችል ሃቅ ነው።

በክልሉ እዚህና እዚያ ይታይ የነበረው ሁኔታ የክልሉን የጸጥታ ኃይል ከሚመሩ ባለሥልጣናት አንዳንዶቹ የመንጋውን እንቅስቃሴ ሊጠቀሙበት እንደሚፈልጉ ወይም እየተጠቀሙበት መሆኑን የሚያሳብቅ ነበረ። የባለሥልጣናቱ ሁኔታ የልብ ልብ እንዲሰማቸው ያደረጋቸው በመንጋ እንቅስቃሴዎች የሚሳተፉ ግለሰቦች የጦር መሣሪያዎችን ይዘው በከተሞች ውስጥ መንቀሳቀሱን የወጥ ማማሰያ ይዘው ከተሞች ውስጥ ኮሜዲ ፊልም የመሥራትን ያህል አቃልለው በማየታቸው ነገሩ ከቁጥጥር ውጪ ሆኖ ነበረ። ይህን መሰሉ ብስለት የጎደለውና በስሜት የመነዳት ጉዞ ሰኔ 2011 የታየውን የባለሥልጣናት መገዳደል ማስከተሉ የሚታወቅ ጉዳይ ነው።

ይህ የመገዳደል ዘመቻ በክልሉ ውስጥ ጎራ መክፈሉና ገና ፍጻሜ ላይ ያልደረሰ የአዳኝና ታዳኝ ጎራ እንዲኖር ማድረጉ የሚካድ አይደለም። ይህን መሰሉ ክፍፍል ባለበት ጊዜ ጦርነት መቀስቀሱና የአማራ ክልል ሕዝብ በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ስር ተሰልፎ እንዲዋጋ የሚያስገድድ ሁኔታ መፈጠሩ የእውነተኛ ፋኖነትን ትንሳኤ ዕውን አድርጓል። ከዛ ውጪ በሕገ-ወጥ መንጋዎች ውስጥ ተሰልፈው ሕገ ወጥ አካሄዶችን ሲከተሉ የነበሩ ግለሰቦችም በፋኖነት ሽፋን በሌላ ሕገ ወጥ አካሄድ ውስጥ እንዲጓዙ፣ ጥላቻና ቂመኝነታቸውንም ለማራመድ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠርላቸው፣ በተቻላቸው መጠን ሁሉ ፍትሕን እየረገጡ ራሳቸውን ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሯሯጡ በር ከፍቶላቸዋል። ከዚህ ሌላ ጠመንጃ ይዘው ከተሞች ውስጥ ስለተንቀሳቀሱ ብቻ ፋኖዎች ነን ብለው ቤታቸውንና ከተማቸውን መበጥበጥን ትግል ብለው የያዙ ግለሰቦችም ጥቂት አይደሉም። በዚህም ሆነ በዚያ ሰበቦችን እየደረደሩ አንዱ አማራ ሌላውን አማራ የሚያጠቃበት መርዘኛ መንፈስ ክልሉን እየበጠበጠው ነው።

ልብ ያለው ልብ ይበል። ሥልጣን ላይ ካለው መንግሥት ጋር ተወዳጅቶም ይሁን ባላንጣ ሆኖ የከተማ ውስጥ ታጣቂነት ውሎ አድሮ አደገኛ ችግርን የሚያስከትል መሆኑን ከኢሕአፓ እና ከመኢሶን የውድቀትና የእልቂት ታሪክ መማር ተገቢ ነው። ኢሕአፓ የደርግ ጠላት መኢሶን የደርግ ወዳጅ ሆነው የከተማ ውስጥ የጠመንጃ ፖለቲካ ለማራመድ ሲሞክሩ አካሄዳቸው ለየቅል ቢሆንም ውድቀታቸው ግን ተመሳሳይ ነው የነበረው። ኹለቱም የጥቂት ጠላቶቻቸውን ሕይወት አጥፍተው የብዙ አባሎቻቸውን እልቂት አስከትለው ‘ነበረ’ ሆነው ቀርተዋል።

በከተሞች ውስጥ በሞቀ ቤት እየበሉና እየጠጡ ወጣ ብለው ደግሞ ጠላቴ ያሉትን እየገደሉ መሰወርን ትግል ብለው ይዘውት የነበሩት ኢሕአፓና መኢሶን የደርግ ጥይት ማብረጃዎች ሆነው ራሳቸውን ለእልቂት ሲዳርጉ፤ ከደርግ ሸሽቶ በረሀ የገባው ሕወሐት ግን ጊዜውን ጠብቆ ደርግን አሸንፎ ገዥ ለመሆን በቅቶ ነበር። ኢሕአፓና መኢሶን በተለይ ኢሕአፓ ምላስ አትሞትምና ከ1963 ጀምሮ ወደ 50 ለሚጠጉ ዓመታት ከእልቂት ተራፊ በሆኑ አባላቱ አማካኝነት ራሱን ትልቅ እያስመሰለ ቢያወራም ኢሕአፓ ተበልቶ የተጣለ እንኩቶ ሆኖ የቀረ ቡድን ነው።

በሚዲያዎች ላይ በተለይ በአርትስ ቲቪና በሸገር ኤፍ ኤም እየተጋበዙ ቀርበው፣ ተገቢውን ጥያቄ የሚጠይቃቸው ጋዜጠኛ ስላጡ ብቻ ኢሕአፓን በድል ላይ የሚረማመድ፣ አሸንፎና ዓላማውን አሳክቶ በመግዛት ላይ ያለ ቡድን የሚያስመስል፣ በትግሉ ወቅት የተሰዉት አባላቱ ሕይወት ፍሬ ያፈራ ወዘተ… እያስመሰሉ አብዝተው ያወራሉ። ቢሆንም ኢሕአፓ በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱን ደመ ከልብ አድርጎ የወደመ ቡድን መሆኑን ታሪክ በመመስከር ላይ ነው። ልብ ያለው ልብ ይበል።

ጠመንጃ የያዘ ሰው አንድም የጠራ ዓላማ ከሌለው፣ በተጨማሪም ጠንካራ ዲስፒሊንና ምክንያታዊነት ካልተላበሰ አጥፍቶ ጠፊ ከመሆን የዘለለ ውጤት አይኖረውም። ከወረዳዬ ወይም ከከተማዬ አልወጣም ባይ ግለሰቦች በየወረዳቸው ወይም በየከተማቸው ጎጆዎች ቀልሰው፣ ከየወረዳው ወይም ከየከተማው ሕዝብ በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ አሰባስበው በወለጋ ዞኖች አደገኛ ሕይወት በመግፋት ላይ ያሉና ቀጣዮቹ ሰለባዎች የመሆን ዕድላቸው ሰፊ የሆነ ምስኪኖችን አንድ በአንድ እያሳፈሩ፣ ራሳቸውን የሚችሉበት ሥራ እየሰጡ ቢታደጓቸው መልካም ነው። ከተማ ውስጥ ከጠመንጃ ይልቅ ዶማና አካፋ፣ ድስትና ሞሰብ ነው ሊጠቅም የሚችለው።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here