መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናመንግሥት ከተሽከርካሪ ፍቃድ ማደሻ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እያጣ ነው

መንግሥት ከተሽከርካሪ ፍቃድ ማደሻ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እያጣ ነው

የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀምና በማጭበርበር መንግሥት ከዓመታዊ የተሽከርካሪ ፍቃድ ማደሻ ማግኘት ያለበትን ገቢ እያሳጡት መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክተር አስራት አሰሌ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፍቃድ ማደሻ ወይም የቦሎ ክፍያን በባንክ በኩል በመክፈል ክፍያ የፈፀሙበትን ደረሰኝ ለኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በማቅረብ ወደ አሽከርካሪና ተሽከርካሪ ቀርበው ሕጋዊነቱን ማረጋጋጥ ያለባቸው ቢሆንም፣ ሕጉን የሚጥሱ አሽከርካሪዎች አሉ ብለዋል።

ይህም የአሽከርካሪ ባለንብረቶች ሐሰተኛ ሰነድ በመጠቀምና በማጭበርበር ሕጋዊ በመምሰል ለመስተናገድ የሚፈልጉበት ሁኔታ እንዳለ እና በዚህም አስተዳደሩ ማግኘት ያለበትን ገቢ እያገኘ እንዳልሆነ ነው የተናገሩት።

ዳይሬክተሩ አክለውም፣ በአሽከርካሪ ባለንብረቶች አስተዳደሩ ምን ያክል ገቢ እንዳጣ የኦዲት ሥራ እየተሠራ የሚገኝ ሲሆን፣ ወንጀል የፈፀሙ አካላትንም በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ በመረጃ የተደገፈና ቁጥራዊ መረጃዎችን የማጣራት ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል።

አስተዳደሩ ምን ያህል ገንዘብ በአጭበርባሪዎች እንዳጣ እና ለሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ ያቀረባቸውንም አካላት ጉዳይ በቀጣይ ያሳውቃል ተብሏል።

ተቋሙ በ2014 በጀት ዓመት ካጋጠሙት ችግሮች መካከል ሌላው የተጠቀሰው፣ በክብደት ላይ የተመሠረተ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ ገቢ በተሰበሰበው መጠን ወደ መንገድ ፈንድ አካውንት አለመግባት ችግር ነው። በክብደት ላይ የተመሠረተ ዓመታዊ የተሽከርካሪ ፍቃድ ማደሻ በፎርጅድ ደረሰኝ መሰብሰብም ሌላው በዓመቱ ያጋጠመ እክል መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ይህንንም ለመቅረፍ ምስጢራዊ የስቲከርና ሠርተፍኬት ህትመት በብርሀንና ሠላም ማተሚያ ድርጅት ታትሞ ወደሥራ እንዲገባ መደረጉ ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በ2014 በጀት ዓመት ከነዳጅ፣ ከተሽከርካሪ ዘይት እና ከሌሎች ከተጣሉ ታሪፎች ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱንም ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል። በባለፉት አስራ ኹለት ወራት ከተለያዩ ዘርፎች ለመንገድ ጥገና እና ለሌሎች ሥራዎች የሚውል ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧልም ተብሏል።

በዚህም በ2014 በጀት ዓመት በነዳጅ ላይ ከተጣለ ታሪፍ 2 ቢሊዮን 998 ሚሊዮን በላይ ብር፣ ከተሽከርካሪ ዘይት እና ቅባት 4 ሚሊዮን 820 ሺሕ ብር፣ ከመንገድ ጠቀሜታ ክፍያ 3 ሚሊዮን 730 ሺሕ ብር እና በክብደት ላይ ከተመሠረተ ከተሽከርካሪ ፈቃድ ማደሻ 252 ሺሕ ብር በላይ የተሰበሰበ ሲሆን፣ በድምሩ 3 ቢሊዮን 259 ሚሊዮን በላይ ብር መሰብሰቡን ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ሊሰበሰብ ታቅዶ የነበረው 3 ቢሊዮን 471 ሚሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፣ ከአፈፃፀም አንጻር ሲታይ  94 በመቶ ነው ማሳካት የተቻለው ተብሏል።

የኮቪድ 19 እና በኢትዮጵያ የነበሩ ግጭቶች ለተያዘው እቅድ ሙሉ ለሙሉ አለመሳካት በምክንያትነት እንደሚጠቀስም ተነግሯል።

ኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተሰበሰበውን ገቢ ለመንገድ ጥገና ለማዋል ያሰበ ሲሆን፣ 1 ቢሊዮን 593 ሚሊዮን 500 ሺሕ ብር በክልል ለሚገኙ የመንገድ ኤጀንሲዎች፤ ቀሪው ብር ደግሞ ለአዲስ አበባ ከተማ መንገድ ኤጀንሲ መሰጠቱን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

ዳይሬክተሩ አያይዘውም፣ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በሌላ በኩል በየዓመቱ ለመንገድ ኤጄንሲዎች የሚመደብላቸውን በጀት ለታለመለት ዓላማ እያዋሉ መሆኑን በተመለከተ የክትትልና ድጋፍ ሥራ ይደርጋል ብለዋል።

ኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ ከመንገድ ኤጀንሲዎች የሚላኩ ጥያቄዎችን እና ሪፖርቶችን የገመገመ ሲሆን፣ በታዩ ክፍተቶች ላይ ግብረ መልስ የመስጠት ሥራ ተሠርቷል ብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች