መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናብዙዎችን ያጭበረበረው የፊያስ 777 አካውንት ታግዶ ምርመራ እየተካሄደ ነው

ብዙዎችን ያጭበረበረው የፊያስ 777 አካውንት ታግዶ ምርመራ እየተካሄደ ነው

ብዙዎችን ያጭበረበረው ፊያስ 777 አካውንት ታግዶ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት የፋይናንስ ወንጀሎች ትንተና ኃላፊ ዮናስ ማሞ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በፒራሚድ የንግድ ሥራ ላይ የተሰማራው ፊያስ 777 ድርጅት ከ26 ሺሕ በላይ የውጭ አገር እና ኢትዮጵያዊያን ሰዎች የተሳተፉበት ሲሆን፣ ብዙ ሰዎች ላይ የማጭበርበር ወንጀል መፈፀሙን ጠቁመዋል።

ይህ ፊያስ 777 የተሰኘው ድርጅት እንደ ፋይናንስ ተቋም ተመዝግቦ እና እውቅና ተሰጥቶት እየተንቀሳቀሰ ያልነበረ ተቋም መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል።

አክለውም ድርጅቱ እውቅና ካለማግኘቱ ባሻገር ፒራሚድ ንግድ በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የተከለከለ እና ወንጀል ነው ብለዋል።

ነገር ግን ድርጅቱ የተቀመጠውን ሕግ በመጣስ በሕገ ወጥ ሥራ ላይ ተሳትፎ በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ማለትም በቴሌግራም፣ በፌስቡክ፣ በዋትሳፕ ጓደኞችን እና ግሩፖችን ፈጥሮ ብዙዎችን እንዳጭበረበረ እና አሁን ላይ አካውንቱ ታግዶ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

በፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በኩል እስካሁን ባለው ድርጅቱ ምን ያህል ገንዘብ ከግለሰቦች እንዳጭበረበረ እየተጣራ ሲሆን፣ እስካሁን ባለው ምን ያህል ግለሰቦች የወንጀሉ ተሳታፊ እንደነበሩ በፌዴራል ፖሊስ በኩል የማጣራት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ተብሏል።

ኃላፊው አክለውም አሁንም ቢሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት ሥም እየቀያየሩ በዚሁ በፒራሚድ የንግድ ሥራ ላይ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ተሰማርተው ኅብረተሰቡን ለማጭበርበር የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች እንዳሉ ያነሱ ሲሆን፣ ሰዎች ከዚህ ሕገ ወጥ አሠራርና መጭበርበር ራሳቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

በርካቶችን ያጭበረበረው ፊያስ 777 ደርጅት ምን ያህል ዜጎችን እንዳጭበረበረ፣ ያጭበረበረውን የገንዘብ ተመን የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ መረጃውን አጠናክሮ ከጨረሰ በኋላ እንደሚያሳውቅ ተገልጿል።

በተጨማሪ የፋይናንስ ደኅንነት አገልግሎት በኩል ድርጅቱ ያጭበረበራቸው ገንዘቦች፣ የወንጀሉ አፈፃፀም በማጣራት ለፌዴራል ፖሊስ እንደሚያሳውቅ ተነግሯል።

በተጨማሪ ቲያንስ 777 ድርጅት ውስጥ ተሳታፊ ሆነው ኅብረተሰቡን ሲያጭበረብሩ የነበሩ ግለሰቦች ጉዳይ እንዲሁ ወንጀላቸው በፌዴራል ፖሊስ ስር እየተጣራ እንደሚገኝ እና ሙሉ መረጃው ከተረጋገጠ በኋላ ይፋ እንደሚደረግ ተጠቁማል።

ኢትዮጵያ ውስጥ እሠራለሁ ብሎ ወንጀል ሲያስፋፋ የነበረው ፊያስ 777 አጭበርባሪ የተሰኘው ድርጅት በኢንግሊዝ አገር ተጨማሪ ካምፓኒ እንዳለውም ተወስቷል።

በተጨማሪ ድርጅቱ በኢትዮጵያ በቴሌግራም፣ በፌስቡክ፣ በኢንስታግራም፣ በዩቱብ እና በሌሎች በማኅበራዊ  ሚዲያዎች ላይ እውቅና እንዲያገኝ ከመሥራት ባሻገር በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እውቅና ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር የሚፈፅማቸው ስምምነቶችም አሉ ተብሏል።

በተጨማሪ ድርጅቱ አሁንም የሚፈጽማቸው ወንጀሎች እንዳሉ እና የሚጭበረበሩ ግለሰቦችም ቁጥር በጊዜ ጊዜ እየጨመረ ነው ተብሏል።

በፊያስ 777 የተጭበረበሩ ግለሰቦችም ያስገቡበትን አካውንት እና ወንጀል ፈፃሚ ግለሰቦችን ማንነት ለፌዴራል ፖሊስ በነፃ ስልክ መስመር 991 በመደወል ጥቆማ ሲያደርሱ የነበረ ሲሆን፣ በቀጣይም ኅብረተሰቡ ከዚህ ዓይነት መጭበርበር ወንጀል በመውጣት በወንጀሉ ላይ የሚሳተፉ አካላትን በመጠቆም ጭምር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠይቋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች