መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበሰሜኑ ጦርነት ከተጎዱ የሞባይል ጣቢያዎች 70 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎት አይሰጡም

በሰሜኑ ጦርነት ከተጎዱ የሞባይል ጣቢያዎች 70 በመቶ የሚሆኑት አገልግሎት አይሰጡም

ኢትዮ ቴሌኮም በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች፤ በተለይም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ባጋጠመው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከተጎዱ የሞባይል ጣቢያዎች ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት እስከ አሁን አገልግሎት መስጠት አለመጀመራቸውን አስታውቋል።

ተቋሙ ይህን ያስታወቀው የ2014 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርቱን ባሳለፍነው ሐሙስ (ሐምሌ 21/2014) ይፋ ባደረገበት መድረክ ላይ ነው።

በመድረኩም የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፣ በ2014 የሥራ ዘመን በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በተለይም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት በአገሪቱ ካሉት ሰባት ሺሕ 622 የሞባይል ጣቢያዎች  ውስጥ፤ በ10 የክልል ከተሞች የሚገኙ 3 ሺሕ 473 የሞባይል ጣቢያዎች መጎዳታቸውንና በዚህም ምክንያት አገልግሎት መስጠት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።

በአሁን ወቅት ከእነዚህ ከ3 ሺሕ 473 የሞባይል ጣቢያዎች ውስጥ 30 በመቶ የሚሆኑት ተጠግነው አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንም የገለፁት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ነገር ግን 1 ሺሕ 144 የሚሆኑት የሞባይል ጣቢያዎች እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት ሥራ አለመጀመራቸውን አሳውቀዋል።

አገልግሎቱ የተቋረጠባቸው 1 ሺሕ 144 ጣቢያዎች መካከል 482ቱ ሰሜናዊ ሪጅን በሚባለው በትግራይና አጎራባች አካባቢዎች የሚገኙ ሲሆኑ፣ 265 የሚሆኑት ደግሞ ደቡብ ምዕራብ ተብሎ በተቋሙ በሚታወቀው የወለጋ ሪጅን የሚገኙ መሆናቸውን ኢትዮ ቴሌኮም ከሰጠው መረጃ ለመመልከት ይቻላል።

በተያያዘ ኢትዮ ቴሌኮም በ2013 በጀት ዓመት 56 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን፤ በ2014 የበጀት ዓመት ደግሞ 70 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ዕቅድ ይዞ ነበር። ቢሆንም ግን የእቅዱን 87 ነጥብ 6 በመቶ በማሳካት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 61 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ፍሬሕይወት ተናግረዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ብዙ ፈተናዎች እንደነበሩበት የተናገሩት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ‹‹ከገጠመን ችግር አንፃር ይህን ያህል ገቢ ማምጣታችን ቀላል አይደለም›› ሲሉም ተናግረዋል።

ለእቅዱም አለመሳካት ብዙ ምክንያቶች ሊነሱ እንደሚችሉ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ፣ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ባጋጠመው የፀጥታ ችግር ምክንያት የአገልግሎት መቋረጥ፣ በኔትዎርክ ሀብት ላይ የሚደርሱ አደጋዎች እንዲሁም የፋይበርና የመዳብ መስመሮች ስርቆትና መቆራረጥ፣ ቴሌኮም ማጭበርበር፣ የኮሮና ወረርሽኝ፣ በተቋም ንብረት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ የገበያ አለመረጋጋት እንዲሁም የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ በዋናነት የሚጠቀሱ ተግዳሮቶች እንደነበሩ ተናግረዋል። የኃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የነዳጅ እጥረት፣ እቃዎችን ለማስገባት የሚረዱ የኮንቴይነር እጥረቶች እንዲሁም የዶላር እጥረትና የዋጋ ግሽበት ለእቅዱ አለመሳካት በተጨማሪ ምክንያትነት ተቀምጠዋል።

በበጀት ዓመቱ ከተገኘው ገቢም 51 በመቶው በድምፅ አገልግሎት፣ 27 በመቶው በዳታ እና ኢንተርኔት አገልግሎት፣ 10 በመቶው ከዓለም ዐቀፍ ገቢ፣ 5 ነጥብ 7 በመቶው እሴትን በሚጨምሩ አገልግሎቶች እንዲሁም 6 ነጥብ 6 በመቶ የሚሆነው በሌሎች አገልግሎቶች የተገኘ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።

በተጨማሪም፤ የውጪ ምንዛሬ ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 146 ነጥብ 6 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር መገኘቱን ገልጸው፤ ይህም የእቅዱን 82 ነጥብ 3 በመቶ ያሳካ ነው ብለዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በዓለም ዙሪያ የቴሌኮሚኒኬሽን አገልግሎትን ከሚሰጡ 778 ተቋማት መካከል 26ተኛ እንደሆነ ያሳወቀ ሲሆን፣ በአፍሪካ አገልግሎቱን ከሚሰጡት 195ቱ ውስጥም ኹለተኛ ነው ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች