መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየመድኃኒቶች በሕገ ወጥ መንገድ ከሆስፒታል መውጣት እየተባባሰ ነው ተባለ

የመድኃኒቶች በሕገ ወጥ መንገድ ከሆስፒታል መውጣት እየተባባሰ ነው ተባለ

አዲስ ማለዳ ከተለያዩ መረጃ ምንጮች እንዳገኘችው፣ በሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የሚሠሩ ባለሙያዎች በተለይ ውድ የሚባሉ መድኃኒቶችን ውጭ ላሉ የግል መድኃኒት ቤቶች እያወጡ የሚሸጡ ሲሆን፣ ይህም ተግባር እየተባባሰ መጥቷል ተብሏል።

በአንዳንድ ሆስፒታሎችም የካንሰር ታማሚዎች መድኃኒት ከግል መድኃኒት ቤት እንዲገዙ እንደሚላኩና በየዙሩ እስከ 5 ሺሕ ብር ድረስ ለወጪ ስለሚዳረጉ ለማቋረጥ እየተገደዱ እንደሆነ ነው የተገለጸው።

በዚህም በግል ፋርማሲዎች መገኘት የሌለባቸውን መድኃኒቶች ጨምሮ ሌሎችም ከመንግሥት ጤና ተቋማት እየወጡ በውድ ዋጋ እየተሸጡ እንደሆነና ታማሚዎችም መድኃኒቶችን ማግኘት እየከበዳቸው መሆኑ ላይ ቅሬታ ቀርቧል።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት፣ በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ አድርጎ መድኃኒት እንደሚያቀርብ ጠቅሶ፣ ይሁን እንጂ በሕገወጥ መንገድ ከጤና ተቋማት አውጥቶ የመሸጥ ችግር በብዙ ቦታዎች መኖሩን ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነትና የኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አወል ሀሰን፣ ብዙ ገንዘብ አውጥተን የሚቀርበው መድኃኒት በማግስቱ የለም መባሉ የእኔም ጥያቄ ነው ሲሉ ገልጸዋል። አክለውም ከቅርንጫፍ ሠራተኞች ጋር ስንወያይም ‹‹ባዶ በርሜል መሙላት ነው የሆነብን፣ በየጊዜው እንሰጣቸዋለን፣ መድኃኒቱ የለም ይባላል፣ የት ነው የሚገባው›› የሚል ጥያቄ በምሬት ያነሳሉ ነው ያሉት።

ለአብነትም የካንሰር መድኃኒቶች ውድና ብዙ ቦታ የማይገኙ (በስድስት ሆስፒታሎች ብቻ ይሰጣል) መሆኑን አንስተው፣ በግለሰብ ደረጃ የማይመጡና የማይሰጡ በመሆናቸው ከእኛ ወጥቶ እነሱ ጋር መገኘቱ ሕገወጥና ሌብነት ነው ብለዋል።

ተጠቃሚዎች ከግል መድኃኒት ቤቶች ሲገዙም ይህ መድኃኒት ለግል ይሰጣል ብለው መጠየቅ አለባቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ከፍተኛ በጀት ወጥቶበት የተገዛ መድኃኒት ሰዎች እየሞቱ ለራስ መበልጸጊያ ማድረግ ከወንጀልም በላይ ነው ሲሉ አሳስበዋል።

ስለሆነም ይህን የመቆጣጠር ሥልጣን በአዋጅ የተሰጠው የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን መሆኑን አውስተው፣ እኛም የጤና ተቋማቱ ኃላፊዎች ጋር በየሳምንቱ እየተገናኘን ስላላቸው የመድኃኒት መጠንና እኛ ጋር ስላለው ክምችት እንነጋገራለን ነው ያሉት። አክለውም የጤና ተቋማት ከእኛ የወሰዱትን መድኃኒት በትክክል ስለማድረሳቸው ማረጋገጫ ያቀርባሉ ብለዋል።

ይሁን እንጂ ከዚህ አልፎ በሕገወጥ መንገድ በሚወጣበት ጊዜ እርምጃ የተወሰደባቸው አካላት በብዛት አለመኖር ችግሩን እንዳባባሰው አመላክተዋል።

አገልግሎቱ 80 በመቶ የአገሪቱን የሕክምና ግብዓቶች ፍጆታ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ቀሪውን ደግሞ የግል አስመጪዎች ፈቃድና የውጭ ምንዛሬ አግኝተው እንደሚሸፍኑም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ባለፉት ዘጠኝ ወራት 38 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሆን የሕክምና ግብዓት ግዥ መፈጸሙ ተገልጿል።

በዚህም ትልልቅ ዘመናዊ ማሽኖችን ጨምሮ መደበኛ መድኃኒቶችን እንዲሁም በዓይነትና በእርዳታ ለጤና ተቋማት በነጻ የሚሰጡ የወባ፣ የቲቢ፣ የክትባትና ሌሎች መድኃኒቶችን ጨምሮ ግዥ መከናወኑ ነው የተመላከተው።

ከዚህ ውስጥ 25 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የሚያወጡት ለማኅበረሰቡ ተሰራጭተዋል ተብሏል። የመድኃኒት ግብዓት ግዥው እየጨመረ በመምጣቱም አምና በዓመቱ መጨረሻ የተገዛው በዚህ ዓመት በዘጠኝ ወር የተገዛውን የሚያህል መሆኑም ተገልጿል።

ከተገዛው የሕክምና ግብዓት 90 በመቶ ያህሉ ከውጭ ሲሆን፣ ቀሪው አነስተኛ መጠን ግዥ የተከናወነው ከአገር ውስጥ አቅራቢዎች ነው ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 195 ሐምሌ 23 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች