የአትክልትና ፍራፍሬ ዋጋ በ7 ወር ውስጥ የሰባት እጥፍ ጭማሪ ማሳየቱ በጥናት ተረጋገጠ

0
780

ከጥር 1/ 2011 እስከ መስከረም 2012 ባለው ጊዜ ውስጥ በአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶች ላይ ሰባት እጥፍ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ያካሔደው ጥናት አረጋገጠ። ጭማሪው ምንም አይነት እሴት ሳይጨመር በፍትኀዊ አሰራር ጉድለት ምክንያት ብቻ በተለይ በከተሞች የተፈጠረ በመሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገው ሚኒስቴሩ ገልጿል።

በቂ ምርት እንዲያቀርቡ ትስስር የተፈጠረላቸው የንግድ ተቋማትና የሸማች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ፍትኀዊ አሠራርን ተከትለው አገልግሎት እየሰጡ አለመሆኑን ያመላከተው ጥናቱ፣ በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚታየው የዋጋ ጭማሪ የተከሰተው በንግድ ሥርዓቱ ላይ እንቅፋት የሚፈጥሩ ተቋማት በመበራከታቸው ምክንያት እንደሆነም አመላክቷል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ኀላፊ የሆኑት ወንድሙ ፍላቴ እንደሚሉት፣ የንግድ ሒደቱ በሕገ ወጥ ደላሎች የተተበተበ በመሆኑ ማኅበረሰቡ የሚፈልገውን ነገር በቀላሉ እንዳያገኝ አድርጎታል። የምርት አቅርቦት የሌለ አስመስለው የሚደብቁና በመነጋገር ያሻቸውን የዋጋ ተመን እያወጡ ሕጋዊ ባልሆኑ ነጋዴዎችና ደላሎች እየተፈፀመ ያለው ድርጊት የዋጋ ንረቱ ዋነኛው መንስኤዎች ሆነው መለየታቸውንም ይናገራሉ።

የኑሮ ውድነቱ ጊዜያዊና ዘለቄታዊ መፍትሔ እንዲያገኝ ለማድረግ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የሚመራ ግብረ ኃይል መቋቋሙም ተገልጿል፤ ግብረ ኃይሉ ከሁሉም ክልሎች አጋር አካላት መንግሥታዊ መዋቅሮች የተውጣጣ እንደሆነም ተጠቁሟል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችና በአዲስ አበባ አስተዳደር በ105 ሺሕ 693 ተቋማት ላይ በተደረገ ምርመራ የ74 ሺሕ 404 የንግድ ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰዱንም አስታውቋል። ሕገ ወጥ ደላሎችን ከገበያ ለማስወጣት፣ ምርቶች በቀጥታ ከአርሶ አደሩ ወደ ሸማቹ የሚደርሱበትን መንገድ መፍጠርና የኮንትሮባንድ ንግድን ለመከላከል እየተሠራ መሆኑንም ወንድሙ ተናግረዋል።

በየወሩ 40 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት፣ 624 ሺሕ ኩንታል ስኳርና 600 ሺሕ ኩንታል የዳቦ ዱቄት በመንግሥት ድጎማ በጀት ከውጭ ሀገራት ወደ ሀገር ውስጥ ይገባል።

የብሔራዊ ዋጋ አረጋጊ ኮሚቴ የተሰበሰቡ መረጃዎች ላይ ረቡዕ መስከረም 28/ 2012 ባካሔደው ስብሰባ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያቀርብባቸው “ኢትፍሩት” የተሰኙት ሱቆች የለውጥ ሥራ ቢደረግላቸው ችግሩን እንደሚፈቱ ታምኖ መመሪያ መሰጠቱን ወንድሙ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የፍጆታ ምርቶችን ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ገበያ ገዝቶ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ዋጋ የማረጋጋት ሥራ የሚሠራው ኮርፖሬሽኑ፣ በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች የኢትፍሩት ሱቆችን ማዘመን፣ ለሸማቹ ማህበረሰብ በቀላሉ ሊታዩና ለግብይትም ምቹ በሆነ መልኩ እንዲደራጁ መወሰኑንም ለማወቅ ተችሏል።

ይህንንም ለማስፈጸም ጨረታ በማውጣት በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል። የምርት አቅርቦትን ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የእርሻ ቦታዎችን በኪራይ በመያዝ ምርቶችን በራሱ ለማቅረብ ውል በመግባት እየሠራ እንደሆነ በኮርፖሬሽኑ የአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ከድር ለገሰ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ ዉስጥ ብቻ 63 የአትክልትና ፍራፍሬ የችርቻሮና የጅምላ ሱቆች ያሉት ሲሆን በአነስተኛ ትርፍ አገልግሎቱን ቢያቀርብም የተለያዩ ቅሬታዎች ይነሱበታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here