አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትን በጥቃቅን እና አነስተኛ ንግድ ላይ የገደበው ሕግ ሊሻሻል ነው

0
833

የአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትን በጥቃቅን እና አነስተኛ የሥራ መስኮች ላይ ብቻ እንዲሰማሩ የገደበው ሕግ እንዲሻሻል እና በተጨማሪ ለሌሎች ምርታማ የሥራ መስኮች የሚውል ገንዘብን ማስተዳደር የሚያስችል መብት የሚሰጥ ማሻሻያ አዋጅ ተዘጋጅቶ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

በሥራ ላይ ያለው አዋጅ የብድርና ቁጠባ ተቋማት በከተማ በግብርና ሥራ እና በሌሎች ሥራዎች ላይ እንዲሁም በጥቃቅን እና አነስተኛ የሥራ መስኮች ለተሰማሩ እንዲያበድሩ እና በተለይም በድህነት ቅነሳና በሥራ እድል ፈጠራ ላይ እንዲሰማሩ የገደበ ነበረ።

በአዲሱ አዋጅ ማሻሻያ መሰረት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ለሌሎች ምርታማ የሥራ መስኮች እና ተግባራት የሚውል ገንዘብ ማስተዳደር እንደሚችሉ የሚገልፅ አንቀፅ አካትቷል። ከዚህም በተጨማሪ በዲጂታል ዘዴዎች የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት፤ ወኪል ባንኪንግ አገልግሎት እና ከወለድ ነፃ አነስተኛ የፋይናንስ ሥራ አገልግሎት እንዲሰጡ ረቂቁ ይፈቅዳል።

ከዚህም በተጨማሪ አሁን በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ከሚዘረዝራቸው ፈቃድ ሊያሰርዙ የሚችሉ ምክንያቶች ባሻገር ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን እና መርሆዎችን መሰረት በማድረግ ተጨማሪ ሦስት ምክንያቶች መካተታቸውን የሕጉ ማብራሪያ ያስረዳል። ገንዘብ አከል ንብረት እጥረት ሲያጋጥም፤ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋሙ ዕዳ መክፈል ወደማይችልበት ደረጃ ሲደርስ ወይም ሕግንና መመሪያን ለማክበር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋሙ ፈቃደኛ ያልሆነ እንደሆነ በተጨማሪ ፈቃዱን ሊያሰርዙ የሚችሉ ምክንያቶች ሆነው ተዘርዝረዋል።

በተጨማርም በሥራ ማንኛውም ትውልደ ኢትዮጵያዊ ወይም ሙሉ በሙሉ ሆነ በከፊል ከውጪ ሀገራት ዜጎች ባለቤትነት የተያዘ ድርጅት አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ለማቋቋም ቅርንጫፍ ለመክፈት ወይም የውጭ ሀገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ተቀፅላ በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ለመሥራት ፍቃድ የማይሰጥ ሲሆን በአዲሱ የአዋጅ ማሻሻያ የኢትዮጵያ ተወላጅ የሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች በአነስተኛ ፋይናንስ ዘርፍ በመሰማራት በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡ ፈቃድ እንዲያገኙ ለማድረግ ያስችላል።

ሕጉን ለማሻሻል ተቀዳሚ መነሻ የሆነው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሆኑ የውጭ ሀገር ዜጎች በፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ እንዳይሳተፉ የሚከለክለውን እገዳ ማንሳት ሲሆን ጎን ለጎን ግን በአዋጁ ላይ ለትግበራ አስቸጋሪ የሆኑትን በአጭር ጊዜ ሊሻሻሉ የሚችሉ አንቀጾች እና ንዑስ አንቀጾች ማሻሻል እንዲሁም ይነሱ ለነበሩ ቅሬታዎች ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ተብሏል።

በማሻሻያ አዋጁ ላይ የፋይናንስ ተቋማትን ትርጓሜ በተመለከተ በነባሩ አዋጅ ላይ ፋይናንስ ተቋማት ተብለው የተካተቱትን መድን ሰጪ ኩባንያዎች ባንክ እና አነስተኛ ተቋማት በተጭማሪ በብሔራዊ ባንክ ፈቃድ የሚሰጣቸው እና የካፒታል ዕቃ ፋይናንስ ኩባንያዎችን፤ የጠለፋ መድን ሰጭ ኩባንያ፣ ወደፊት ወደ ሥራ የሚገቡትን አነስተኛ መድን ሰጪ እና በዲጂታል ዘዴዎች የፋይናንስ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች እንዲያካትት ሆኖ ትርጓሜው እንዲስተካከል ተደርጓል።

በጉዳዩ ላይ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ተኪኤ ዓለሙ፣ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት በበርካታ የሀገራችን ክልሎች ለሚገኙ በጥቃቅን እና አነስተኛ የሥራ መስኮች ላይ ለተሰማሩ ዜጎች ብድር በመስጠት ኢኮኖሚውን ለመደገፍ እና ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋፅኦ አላቸው ያሉ ሲሆን በጥቃቅን እና አነስተኛ የሥራ መስኮች በተጨማሪ አትራፊ የሆኑ ሌሎች መስኮች አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጉ መልካም ጅማሮ ነው ብለዋል።

ትውልደ ኢትዮጵያውያን በአነስተኛ የፋይናንስ አገልግሎት ውስጥ ለመግባት የራሳቸውን ገንዘብ ኢንቨስት አድርገው መግባታቸው ለኢኮኖሚው እድገት አስተዋፅኦ አለው ያሉ ሲሆን፣ የውጭ ሀገር ተወላጆች በአነስተኛ የፋይናንስ አገልግሎት ለመሰማራት ፍላጎት ቢኖራቸውም በፍጥነት ወደ ሥራ ለመግባት የገንዘብ አቅም እና ሌሎች ጉዳዮች ፈተና ሊሆኑባቸው ይችላሉ ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ እንደ ሞባይል ባንኪንግ ባሉ ዲጂታል ዘዴዎች ሰዎች ገንዘብ እንዲያዘዋውሩ ማድረጋቸው አነስተኛ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጭዎች ወደ መደበኛው ባንክ አገልግሎት ለማደግ ለሚያደርጉት ጥረት አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በቀድሞ አዋጅ ውስጥ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ተበዳሪዎች የብድር መረጃ ልውውጥ ስርዓት ላይ የሚያስቀምጠው መመሪያ የሌለ ሲሆን ተደራራቢ ብድር እንዳይኖር ለማድረግ አነስተኛ የገንዘብ ተቋማት የብድር አመላለስ ስጋታቸውን ውጤታማ በሆነ መልኩ መከታተል እንዲችሉ እንደሚያድረግ በመታመኑ የተበዳሪዎች የብድር መረጃ ልውውጥ ስርዓት በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ተካቷል።

በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ ከ 30 በላይ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ከብሔራዊ ባንክ ፈቃድ በመውሰድ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here