መነሻ ገጽዜናየእለት ዜናኒያ ፋዉንዴሽን ለመጀመሪያ ጊዜ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ 12 ተማሪዎቹን አስመረቀ

ኒያ ፋዉንዴሽን ለመጀመሪያ ጊዜ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ 12 ተማሪዎቹን አስመረቀ

አርብ ሐምሌ 29 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኦቲዝም እና ተዛማጅ ችግሮች ያለባቸውን ሰዎች የመርዳትን አላማ አንግቦ፤ በባለ ራዕይዋ ዘሚ የኑስ አማካኝነት ከዛሬ 20 ዓመታት በፊት የተመሰረተው “ኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል” ለመጀመሪያ ጊዜ የኦቲዝም ጋር የሚኖሩ 12 ተማሪዎቹን በዛሬው ዕለት በብሄራዊ ቲአትር ቤት አስመርቋል።

ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ዜጎች መማር እንደሚችሉ፣ ወደ ሥራ መሰማራት እና ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ በተግባር ማረጋገጥን አላማው ያደረገው ኒያ ፋዉንዴሽን ጆይ ኦትዝም ማዕከል፤ 20ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ዛሬ ያስመረቃቸውን 12 ተማሪዎች በቀጥታ በማዕከሉ የሥራ ቅጥር እድል የተመቻቸላቸው መሆኑንም ገልጿል።

በተማሪዎቹ የምርቃት ሥነ ሥርዓት ላይ የማዕከሉ ዳይሬክተር እሌኒ ዳምጠው እንደገለጹት፤ ኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል በኦቲዝም እና ተዛማጅ እክል ያለባቸውን ሰዎች በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እንዳይኖራቸው የሚያግዱ ችግሮችን ለመቅረፍ እየሰራ ይገኛል።

ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት 80 የኦቲዝም እና ተዛማጅ ችግሮች ላለባቸው ህፃናት እና ወጣቶች ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

አክለውም፤ በአዲስ አበባ ሲ ኤም ሲ አካባቢ ከመንግስት በተገኘው 5 ሺሕ ካሬሜትር ቦታ ላይ ሊገነባ የታሰበው በአፍሪካ ብቸኛውና ኹሉን ያሟላው የኦቲዝም የልህቀት ማዕከል ሲጠናቀቅ፤ ተጨማሪ 500 የሚሆኑ የኦቲዝም እና ተዛማጅ እክል ያለባቸውን ዜጎች መቀበል፣ በሺሕዎች ለሚቆጠሩ ቤተሰቦች የምክር እና ድጋፍ አገልግሎት መስጠት፤ እንዲሁም ትልቅ የምርምር እና ልህቀት ማዕከል ማቋቋም እንደሚያስችልም አስረድተዋል።

የፋውንዴሽኑ የቦርድ ሰብሳቢ ሰሀራ ሀሰን በበኩላቸው፤ እንዲህ እንደዛሬው በማህበረሰብ ውስጥ ስለ ኦቲዝም ምንም አይነት ግንዛቤ ባልነበረበት ወቅት፤ ኒያ ፋውንዴሽን ጆይ ኦቲዝም ማዕከል መቋቋሙን ገልጸው፤ በአሁኑ ወቅት ለብዙሀን የኦቲዝም እና ተዛማጅ እክል ላለባቸው ዜጎች በመድረስ ትልቅ ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አክለውም፤ ኹሉም ኢትዮጵያዊ በዛሬው ዕለት የተመረቁትን ተማሪዎች በመቅጠርና ለሥራ ተስማሚ የሆነን ከባቢ በመፍጠር የበኩሉን ሀላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ኹሉም ኢትዮጵያዊ በ9616 አጭር የመልዕክት ፅሁፍ ላይ ok ብሎ በመላክ እንዲሁም፤ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሳር ቤት ቅርንጫፍ፣ በኒያ ፋውንዴሽን የአካውንት ቁጥር 1000066285808 ላይ ፋውንዴሽኑን በመደገፍ አገራዊ ሀላፊነቱን ይወጣ ዘንድ ፋውንዴሽኑ ጠይቋል።

ዘንድሮ በኢትዮጵያ ለ20ኛ ጊዜ፣ በአለም ዓቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ14ኛ ጊዜ፤ “ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ዜጎች በሥራ የመካተት እና የመሰማራት መብታቸው ይረጋገጥ፤ እድል እና ተግዳሮቶች ከወረርሽኝ ዘመን በሗላ” በሚል መሪ ቃል ባሳለፍነው መጋቢት ወር መከበሩ ይታወሳል።

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች