የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ መሠረታዊ የምጣኔ ሀብት አስተሳሰቦች (ክፍል ሁለት)

0
1379

ዓለማየሁ ገዳ በክፍል አንድ ጽሑፋቸው የነጋድራስ ገብረሕይወት ባይከዳኝ “መንግሥት እና ሕዝብ አስተዳደር” የተሰኘ መጽሐፍ ላይ ተመሥርተው፣ የገብረሕይወት ምጣኔ ሀብታዊ ኀቲት ግንባር ቀደም መሆኑን እንዲሁም የጀመርናዊው ሔንሪ ቻርለስ ኬሪ ትንታኔ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው አስነብበውን ነበር። በዚህ ክፍል ደግሞ ገብረሕይወት ውስጣዊ የምጣኔ ሀብት ተግዳሮቶች አድርገው ያሰፈሯቸውን ያትታሉ።

(ክፍል ሁለት)

 

ውስጣዊ የልማት መሠናክሎች
በነጋድራስ አስተሳሰብ ጦርነትን ያህል የልማት መሰናክል የለም። ጦርነት ልማትን በመገደብ ከተፈጥሮ ቁጣም ሆነ ካልተመጣጠነ የውጪ ንግድ ጉዳት ያይላል። ለነጋድራስ የአገራችንን ዕድገትን ጠፍንጎ የያዘው ይህ መሠናክል ነው። ለነጋድራስ የግጭት ወይም ጦርነት መነሻው የአንዳንድ ግለሠቦች ሳይደክሙ የሰውን ላብ የመሻት ፍላጎት ነው። ያገራችን ገበሬ ደግሞ ተበታትኖ መስፈሩ ለነዚህ ዘራፊዎች ምቹ ተዘራፊ አድርጎታል። የዚህ ዓይነቱ አካሔድ ድምር ውጤት ጥቂት ሰዎች ባመረቱት ብዙ ሥራ ፈት ዘራፊዎች ተመጋቢ ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ ሀብት የመፍጠርን አቅም፣ በተለይ በእርሻው ክፍል ኢኮኖሚ፣ በእጅጉ ስለሚያቀጭጭ የልማት ማነቆ ይሆናል። ለእርሻ ይውል የነበረው የሰው ኃይልም ወደ ሽፍታነቱና ዘራፊነቱ ሲያደላ የልማት ተስፋን የበለጠ ያደበዝዘዋል። (ጦርነት-ነክ ጥናቶች ገብረሕይወት እንዳደረጉት የጦርነት አሉታዊ ገፅታ ላይ ብቻ አያተኩሩም። እንዳውም ጦርነት ዕድገትን ሊያመጣ እንደሚችል ይሞግታሉ። ገብረሕይወት ይህንን የጦርነት ሌላ ገጽታ ያልተነተኑት ትንታኔያቸዉ ጉዳቱ ባየለበት በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ስለተመሠረተ ሳይሆን አይቀርም።)
ነጋድራስ ይህችን ጦርነት ነክ ገለጻቸውን በዛው አልገቱትም። ይልቅም ይህ ግጭትና የግጭት መንስዔን በዛን ጊዜ ቋንቋ ‘ነገዶች’ (በዛሬ ቋንቋ ብሔረሰቦች) መሐል ምን መልክ እንደሚይዝ ተንትነውታል። ይህንንም ሲገልጹ ዘረፋና ቅሚያ በእያንዳንዱ ነገድ ውስጥ እንዳለ፣ አንዳንዴ አንድ ነገድ ባንዱ ላይ እንዲነሣ በተለያየ መንገድ የነገዱ ተጠሪ ነን ባዮች እንደሚቀሰቅሱ፣ ጦርነት ሲነሳ ሁለቱ ነገዶች እንደሚተላለቁ፤ የነገድ መሪዎች ነን ባዮች ግን ወደ ጦርነት ቦታ ድርሽ እንደማይሉ፤ በአፋቸው ለነገዳቸው በማሰብ ጠበቃ የቆሙ እንደሚመስሉ በተግባር ግን ለግል ጥቅማቸው እንጂ ለነገዱ ደንታ እንደሌላቸውና ድብቅ ዓላማቸው መዝረፍ እንደሆነ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ፍንትው አድርገው አሳይተውናል። ይህ በነገዶች መሐል የሚነሳ ግጭት መደባዊ መልክ እንዳለው ገብረሕይወት በጥናታቸው ላይ ያስረገጡት ጉዳይ ነው፤ እንዲህም ይላሉ፡-
“የእያንዳንዱ ቆሮ [የነገዱ ተጠሪ ነን ባዮች] አሳብ መቼም ለመቀማት ነው። ነገር ግን ይህንን እውነተኛውን ሐሳባቸውን ሸፍነው ሥም ብቻ በመፈለግ የተነሱ ያስመስሉታል። …ቆሮዎቹ ግን በመጀመሪያ ለመጋደል አይፈላለጉም ነበር። …ገባሮቻቸውን እያስተራረዱ ቆሮዎቹ እርስ በራሳቸው በፍቅር ለመላላክ አይመለሱም።” (ገጽ 32)
ይህ የገብረሕይወት የጦርነት መንስዔ ኀቲት ባለፉት 10 ዓመታት (እ.ኤ.አ ከ1999 ጀምሮ) ግጭቶችን ለመተንተን ኢኮኖሚስቶች በተለይ ደግሞ የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ፖውል ኮሊየር እና አብረዋቸዉ የሚጽፉ ብዙ የምርምር አጋሮቻቸው በመስኩ የዘረጉትን “ስግብግብነትና የፍትሕ እጦት (greed and grievance) እንደ ግጭት መንስዔዎች” የሚባለውን የግጭቶችና የርስ በርስ ጦርነቶች ሞዴል ገብረሕይወት ከ90 ዓመታት በፊት ተንትነውት ነበር ማለት ይቻላል።
በገብረሕይወት ናሙና ውስጥ የዚህ ውጤት በጦርነቱ ምክንያት ገበሬው በብዙ ድካም ካለማው መሬት ተፈናቅሎ በመቆየቱ የለማው መሬት ተበላሽቶ እንደገና “ሀ” ብሎ መሬቱን ማልማት ሲጀምር ምን ያህል ልማትን ወደ ኋላ እንደሚመልስ ማስረዳታቸው ላይ ነው። የጦርነቱ አዙሪት በተደገመ ቁጥር የኋልዮሽ የልማት ጉዞው ሕዝቡን በዛው ልክ በድህነት አዙሪት ውስጥ ተደፍቆ እንዲቀር እንደሚያደረግ ነጋድራስ በአንክሮ ገልጸውታል።
“ያንዱን ትንሽ አገር ሌላው እየጠቀለለው ይሔዳል። በጊዜ ብዛትም ትልልቅ ነገሥታት ይወጣሉ። በውስጣቸውም በግድያና በዘረፋ የበለጠውን እያዩ ራስ፣ ደጃዝማች፣ [ጠቅላይ ሚኒስቴር፣ ጄኔራል] እያሉ ይሾማሉ። የነገሡበትንም አገር ለእነርሱ ያካፍላሉ፣ የቀረው ሁሉ የነዚህን ማዕረግ እያየ ሥምና ሹመት አገኛለሁ እያለ በሕዝቡ ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ሰው በግድያና በዘረፋ እንዲመሰገን ያጥራል። ጦርነቱም ከድሮ የባሰ ይሆናል።… ጦርነቱን የሚያነሱ ነገሥታቱና አለቆቹ ሁሉ ልባቸው ሀብት እንደፈለገ አይገልጹም። ነገር ግን ሥም ለመፈለግና ለማግኘት ወይም ሃይማኖቶችን ለማስፋፋት ወይም የተጠቃውን ለመርዳት አስመስለው ይነሳሉ። የጦርነቱ ሁሉ ፍፃሜና ምኞት ግን መዝረፍና ማስገበር ነው። ይህንንም ስንል ዕውቀታቸው የሰፋ ነገሥታትም ቢሆኑ መዝረፍን አይተዉም። አዘራረፋቸው ግን የዕውቀት አዘራረፍ ነው።” (ከገጽ 33 እስከ 34)
ይህ እንግዲህ ለነጋድራስ አንዱና ዋንኛው ‹ውስጣዊ› የልማት መሠናክል ነው። የመሠናክሉ ምንጭ ጦርነት ሲሆን፣ የጦርነቱ ሰለባ የሚሆነው የእርሻ ዕድገት ነው። በጦርነቱ የሚያልቀው የሕዝብ ብዛት ከባሥልጣኖች የሥልጣን አለመረጋጋት ጋር ተደማምሮ ልማትን እንደሚያሽመደምደው ነጋድራስ ገልጸውታል። የዚህ ጦርነታዊ ሒደት አስከፊ ተቋማዊ አንድምታው ዘረፋውና ዝናው ጦርነቱን ማትጊያ እመሆኑ ላይ መሆኑም ልብ ይሏል። ነጋድራስ የጦርነቱ ውጤት በትናንሽና በትላልቅ ንጉሦች መሐል እንደገና ተጭሮ አገሪቱን ሲያምስ እንደነበረ በግልጽ አስቀምጠውታል። እንዲያውም ነገሩ በዚህ ከቀጠለ የእርሻ ልማታችን ከሥሩ ጠፍቶ፣ የአየር ንብረታችንና የመሬት ለምነት ተናግቶ የልጅ ልጆቻችን ወደ ውጪ አገር እንደሚሰደዱ ተንብየዋል። የአሜሪካን ዲቪና አረብ አገር ለመሔድ ያለውን ሰልፍ ልብ ይሏል። አማኑኤል የተባለ ታመሪዬ ይህንን ደርዝ ይዞ የ2ኛ ዲግሪውን መመረቂያ ጽሑፍ በአ.አ.ዩ. አራት ኪሎ ግቢ/ደብር በዚህ ጉዳይ ላይ ጽፎበታል።
ነጋድራስ ውስጣዊ የልማት መሰናክሎች ከሚሉት ከላይ ከተጠቀሰው ሐሳብ ጋር አያይዘው መዋዕለ-ነዋይ (ኢንቨስትመንት) እና የተማረ ወይም የሠለጠነ የሰው ኃይል ለልማት ወሳኝ እንደሆነ ለማሳየት ጥረዋል። በተጨማሪም የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ቢሆንም የከተማው ክፍለ ኢኮኖሚ ካላደገ ግብርናው ብቻውን ሊያድግ እንደማይችል በጠራ ቋንቋቸው አሳይተዋል። ለነጋድራስ የከተማው ኢኮኖሚ ለገጠሩ የገበያ ምንጭ ብቻ ሳይሆን የሠለጠነ የሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ዕድገት መሠረትም ነው። ጠቅለል ባለ መልኩ ሲታይ የገብረሕይወት ናሙና ሦስት ክፍለ-ኢኮኖሚዎችን ያጠቃላለ ነው ማለት ይቻላል፤ ሆኖም ግን ናሙናቸው ያተኮረው በእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ነው። ከእርሻ ውጪ ያለው ኢኮኖሚ በሁለት አቅጣጫዎች እርሻው ላይ ተፅዕኖ እንደሚያደርግ አብራርተዋል። አንደኛው መንገድ ቴክኖሎጂ በማቅረብ ምርታማነትን መጨመሩ ሲሆን ሁለተኛው መንገድ ለእርሻ ክፍለ ኢኮኖሚው ገበያ መፍጠሩ ነው። መንግሥታችን ይህንን ሐሳብ ከ20 ዓመት በፊት አይቶት ቢሆን ምንኛ ጥሩ ነበር።
የገብረሕይወት ናሙና ሌላ ለየት የሚያደርገው ነገር ስትራክቸራሊስት የሚባሉትን ኢኮኖሚስቶችን በመቅደም የተዛባ የገቢ ስርጭት በአጠቃላይ (በማክሮ) ኢኮኖሚው ላይ ያለውን ተፅዕኖ በአንክሮ በመግለጽም ጭምር ነው። ይህንንም አንዲህ ብለው ገልጸውታል።
በሥራ ያልሠለጠኑ ሕዝቦች ያልተሠራ እቃ ካገራቸዉ አውጥተው ሸጠው ትርፍ ብር ቢያገኙ ለጊዜው ነው እንጂ አያዘልቃቸውም። መሬታቸው በጊዜ አርጅቶ እህል መስጠቱን ሲያቋርጥ፣ የሚሸጡት ነገር ሲጠፋ፣ የልብስ መግዣና ምግብ አጥተው እናገኛለን ሲሉ ወደ ሌላ አገር ይሰደዳሉ።… የሚነግዱበትም ነጋዴዎች ያገሩ ሰዎች ቢሆኑ ያው ነው። ባለ መሬቱ እየደኸየ ነጋዴው ግን እየተጠቀመ ይሔዳል። ማለት ያገሩ ሀብት በጊዜ ብዛት በጥቂቶች ሰዎች እጅ ይጠቀለላል። እነዚህም ጥቂቶች ሰዎች የተወለዱበት አገር ብዙ ፍሬ እነደማይሰጥ ሲያዩ የሰበሰቡትን ብርና ወርቅ ይዘው በደኅና ወደሚኖሩበት አገር ይሔዳሉ። ብዙ ሀብት ያከማቸ ሰው በሔደበት አገር ይመቸዋልና ያገር መውደድን ነገር ከጉዳይ አይቆጥረውም።
“የሚበላውን እና የሚለብሰውን ያጣ ድሀ የተወለደበትን አገር የሚወድበትን ምክንያት ያጣልና ያገሩ መንግሥት ቢበረታ ወይም ቢጠፋ ግድ የለውም፤ ስለዚህም መንግሥት የሚጠቀምበት ያገሩ ሀብት በጥቂቶች ሰዎች እጅ ሲሰበሰብ አይደለም፤ በመላው ሕዝቡ እጅ ሲከፋፍለው ነው እንጂ። የሀብታሞች አኗኗር እና የሠራተኛው ድኃ አኗኗር ዓይነቱ እንበለ መጠን የሚራራቅበት አገር መንግሥቱ ከጥፋት አፋፍ እንደደረሰ ያስረዳል። የኢትዮጵያንም ሕዝብ ሁኔታ ብንመለከት እንደዚሁ ያለ ጥፋት እንዳይደርስ ያስፈራል። ባንድ ፊት ነግደው የሚያድሩት የውጭ አገር ሰዎች እና ለሐዝቡ አንዳች ጥቅም ሳያድሩ ድካሙን የሚቀሙ አንዳንድ ሹማምንት ደኅና ቤት እየሠሩ፣ እያጌጡ የተመቸ ኑሮ ሲኖሩ እናያለን። ባንድ ፊትም የዕለት ምግብና ያንድ ዓመት ልብስ እናገኛለን ሲሉ ብዙ ሺሕ ድሆች ወባና ችጋር ፈጅቷቸው ከድሬዳዋ አንስቶ እስከ አዲስ አበባ ድረስ፣ ከምድር ባቡር ጎን ልፈው ተቀብረዋል። ግማሾቹም የተቀበሩበት መቃብር ጠሊቅ ስላልሆነ ዱሮ አጥንታቸው ወቶ ከምድር ባቡር መንገድ ግራና ቀኝ ተበትኗል።” (ገጽ 118-119)
“…ያማረ የግንብ ቤትና ትንንሽ ጎጆ አጠገብ ላጠገብ ተሠርተው እናያለን። ባንዱ ቤት ውስጥ ትልቁ ጌታ ሕዝቡ ደክሞ ያፈራውን ገንዘብ በከንቱ ሲያባክን፣ በጎጆው ውስጥ የሚኖረው ድሀ የሚበላውና የሚለብሰው የሚራበውም አጥቶ በረሃብና በብርድ ተጨብጦ በኩበት ጢስና በእድፍ ውስጥ ይጨማለቃል።” (ገጽ 120)
በዚህ ትንትና ገብረሕይወት አንደ ዕውቁ የፖላንድ ምሁር ሚካኤል ካልስኪ የኢኮኖሚ ተዋናዮችን የሚመለከቷቸው በመደባዊ ይዘታቸው ነው። እነዚህ ተዋናዮችም በተቋማት ላይ ያላቸውን ተፅዕኖ፣ ተቋማትም እንዲሁ በኢኮኖሚው ላይ ያላቸውን አንድምታ በውሉ አጢነውታል። በመጨረሻም የነጋድራስ ውስጣዊ የልማት ችግር ያልኩትን ሳጠቃልል፣ እሳቸው ያነሷቸውን ሁለት መሠረታዊ ሐሳቦች እንደገና በመጠቆም ነው፤ እነሱም:- አንደኛ፣ የሀብት ክፍፍል በቅጡ አለመመጣጠን በአገር ልማትና አገር ሉዓላዊነት ላይ የሚያመጣውን አሉታዊ ተፅዕኖ፤ ሁለተኛኛ ኢኮኖሚያዊ ትንተናቸው መደባዊ መሆኑና የልማት ተቋማት ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ መሆናችን ማሳሰባቸውን ነው።
እኚህ አስተሳሰቦቹ በመዋቅራዊ ችግሮች ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ ኀቲት (Structural economics) እና የድኅረ-ኬንስ ኢኮኖሚያዊ ኀቲት (Post-Keynesian economics) የሚባሉትን የዛሬ ኢኮኖሚስ ትምህርት ፈርጆቹ ፋና ወጊ መሆናቸውን ቁልጭ አርገው የሚያሳዩ ናቸው። ይህ ትንታኔያቸውም የመንግሥት የገንዘብና የቀረጥ-ነክ ፖሊሲ ምን መሆን እንዳለበት አጥጋቢ በሆነ መልኩ ለማስረዳት መንገድ ከፍቶላቸዋል።
(ክፍል ሦስት ይቀጥላል)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here