የማንነት ጥያቄ እንደ ሰብኣዊ መብት

0
386

የአሜሪካ ሕገ መንግሥት በመጀመሪያ የመምረጥ እና የመመረጥ መብት የሰጠው ሀብት ንብረት ላላቸው ነጭ ወንዶች ብቻ ነበር። የማንነት ጥያቄዎች እየበረቱ እና እየጎለበቱ በሔዱ ቁጥር ሁሉም ነጭ ወንዶች የመምረጥ እና መመረጥ መብቶችን ተጎናፅፈዋል። ከዚያ በኋላ በትግል ሴቶች እና ጥቁሮችም እንዲሁ የመምረጥ እና የመመረጥ መብቶችን እንዲያገኙ እንዲሁም በማናቸውም ሁኔታ ሰብኣዊ ክብራቸው እንዳይጓደል እና ቢያንስ በሕግ ፊት እኩል እንዲታዩ ማድረግ ችለዋል።
ዴሞክራሲ እንከን አልባ አይደለም። በብዙኃን ይሁንታ የሚመራ፣ የሕዳጣን መብት ግን የማይገሰስበት ስርዓት ነው። ይሁን እንጂ የብዙኃን ይሁንታም ይሁን የሕዳጣን መብት ተብሎ የሚታመነው በየጊዜው እና በየቦታው በመለያየቱ ምክንያት ዴሞክራሲ እያደገ የሚሔድ እንጂ የመጨረሻው ምርጡ ስርዓተ መንግሥት እንዳይሆን አድርጎታል። በመሆኑም ኃያላን እና ብዙኃን በድምፅ ብልጫ የሚመሠርቱት ስርዓት የአናሳ ቡድኖችን መብት የሚጨፈልቅበት ጊዜ ቀላል አይደለም። የማንነት ጥያቄዎች የሰብኣዊ መብቶች ጥያቄዎች የተደረጉት በዚህ ምክንያት ነው። ሰብኣዊ መብቶች በብዙኃን አመራር ውስጥ ይከበራሉ እንጂ በፍፁም አይገሰሱም።
የዓለም ዐቀፉ የሰብኣዊ መብቶች ድንጋጌ እና የአፍሪካ ሰብኣዊ እና ሕዝባዊ መብቶች ቻርተር (ሁለቱም በአንቀፅ 2) ያስቀመጡት ድንጋጌ “በዘር፣ በዘውግ ቡድን፣ በቆዳ ቀለም፣ በፆታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም አስተያየት፣ በብሔር ወይም ማኅበራዊ ምንጭ፣ በሃብት፣ በውልደት ወይም ሌላ ምክንያት” ምንም አድሎ ሳይደረግባቸው ሁሉም ሰዎች ሰብኣዊ መብቶቻቸው እና ክብሮቻቸው ይጠበቁላቸዋል ይላሉ። በሁለቱ ድንጋጌዎች መካከል ያለው ልዩነት የአፍሪካው ቻርተር የዘውግ ቡድን የሚለውን መጨመሩ ብቻ ነው። በመሠረቱ የአፍሪካ ቻርተር በተባበሩት መንግሥታቱ ድንጋጌ ውስጥ የማይታወቁ የሕዝቦች መብቶች የሚላቸው እነዚህን የዘውግ ቡድኖች የወል መብቶች ነው።
የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ተመሳሳይ ድንጋጌ አለው። በአንቀጽ 25 ውስጥ “የእኩልነት መብት” በሚል የሰፈረው ድንጋጌ፣ በማንነት ልዩነት ማድረግን ይከለክላል። ከዚህም በተጨማሪ የሴቶች መብት (አንቀፅ 35) እና የሕፃናት መብት (አንቀፅ 36) በማለት የተለያዩ የማንነት ጥያቄዎችን በተለየ ትኩረት ለማየት ይሞክራል።
በኢትዮጵያ የክልላዊ መንግሥታት ሕገ መንግሥቶች ውስጥ የማንነት ጥያቄዎች ቅሬታ የሚያስነሱት የክልሎቹ “መሥራቾች” ተብለው የተለዩ አካላት ወይም የዘውግ ቡድኖች በመኖራቸው፣ እንዲሁም ከነዚህ ውጪ ያሉት ነዋሪዎች መብቶቻቸው የሚሸራረፉባቸው በመሆኑ ምክንያት የማንነት ጥያቄዎች የግጭት መንስዔ እየሆኑ ነው። ይሁን እንጂ የማንነት ጥያቄዎች የሰብኣዊ መብቶች ጥያቄ እንደመሆናቸው የትኛውም ክልሎች ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ዜጎች “መሥራች” ወይም “መጤ” የሚል ክፍፍል ሳያደርጉ እኩል መብት በማጎናፀፍ ቅሬታዎቹን በዴሞክራሲያዊ መንገድ መፍታት ያሻል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here