“ጠላት” የነበሩ ሴቶች ዳግም ዕውቅና ማግኘት የሴቶቹ ሹመት ሕዝባዊ ፋይዳ

0
730

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከመጡ ወዲህ በታየው የለውጥ ሒደት ውስጥ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ ሴቶችን የማስቀመጥ ጅምሩ ጉልሕ ድርሻ ካላቸው ለውጦች አንዱ ነው። ይህንን በማስመልከት ቤተልሔም ነጋሽ ፋይዳውን ይነግሩናል።

 

 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የዛሬ ሰባት ወራት ገደማ ወደ ሥልጣን ሲመጡ፣ ያንን ተከትሎ የመጀመሪያውን አነቃቂና ተስፋ ሰጪ የተባለ ንግግራቸውን ፓርላማው ፊት ሲያደርጉ፣ በሴቶች መብቶች ዙሪያ ያገባናል ለምንል ትንሽ የተስፋ ጭላንጭል ታይቶን ነበር። ይኸውም መጪው ጊዜ ለኢትዮጵያ ሴቶች ትንሽም ቢሆን የተሻለ ይሆናል የሚል ነበር። እንደ እኔ ቢያንስ ያለፉትን ዐሥርት ዓመታት የኢትዮጵያ ሴቶችን ጉዳይ ጉዳዬ ብሎ የተከታተለ ሰው እንደሚረዳው፣ ቢያንስ በመንግሥት ደረጃ ገዢው ኢሕአዴግ ‹የሴቶች ጥያቄ ተመልሷል› ብሎ ያምን ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ሽረው ከከፈሉት መስዋዕትነትና በአገሪቱ እያደረጉት ካሉት ከፍተኛ አስተዋፅዖበተቃራኒ የኢትዮጵያ ሴቶች ዕውቅና ተነፍገው መክረማቸውን ጠቀሱ።በግላቸው የባለቤታቸውንና የወላጅ እናታቸውን አስተዋጽኦ ተናግረው በይፋ አመሰገኑ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደሥልጣን ከመጡ በኋላ ቃል የገቡትን የለውጥ እርምጃ ተከትሎ በተለያዩ አካላት “ይህን ቢያደርጉ” ተብለው ከሚሰነዘሩ የፖሊሲና ተያያዥ ለውጥ ሐሳቦች መካከል የሴቶችን ጉዳይ የሚመለከቱ ሐሳቦችም ነበሩበት። በሴቶች መብት ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚሠሩ ተቋማት በጋራ ለጽ/ቤቱ ካስገቡት ይፋዊ ደብዳቤ ሌላ በግለሰብም ደረጃ የሚሰነዘሩ፣ ይህ ቢደረግ በሴቶች ሕይወት ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ ይመጣል የሚባሉ አስተያየትና ጥቆማዎችን በተለያዩ አጋጣሚዎች ስንሰማ ነበር።
የሴቶች እኩልነት ላይ በሚሠሩ ተቋማትና በግላቸውም አቀንቃኝ በሆኑት ሰዊት ኃይለስላሴ እና ቢልለኔ ሥዩም (በአሁኑ ሰዓት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪ ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት) የጻፉትና በተለያዩ ድረ-ገጾች ያጋሩት “ግልጽ ደብዳቤ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ” የሚለው የጥያቄዎች ስብስብ ምናልባትም በዚህ ዘርፍ ከቀረቡት ሐሳቦች መካከል በድረ ገፆች በመታተምና በተለይ አንደኛዋ ጸሐፊ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ በመዘዋወር ተጠቃሽ ነው። በደብዳቤው ላይ በግልጽ ከተቀመጡት ጥያቄዎች መካከል በካቢኔ የሴቶች ቁጥር ጨምሮ ሃምሳ-ሃምሳ የፆታ ተዋፅዖ እንዲኖር በተጨማሪም የወንዶች ግዛት ተደርገው ሚወሰዱት እንደ ንግድ፣ መከላከያ፣ ፋይናንስ እና ኢንዱስትሪ በሴቶች ቢያዙ የሚል ነበር።
ጥቅምት 6፣ 2011 ጠቅላይ ሚኒስትሩ 20 አባላት ያሉት አዲሱን ካቢኔያቸውን ሲያስተዋውቁ የሆነው ግን ከተስፋውና ከጥያቄው ጋር ቢሔድም በፍፁም ያልተጠበቀ ነበር። በመጨረሻ የኢትዮጵያ ሴቶች ጊዜ መጣ እስኪባል ደስታ ሆኖ ነበር።
በሳምንቱ የቀድሞዋ አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ፣ ቀጥላ ታዋቂዋ የሴቶች መብት ተሟጋችና ሴቶች ላይ አድልዎ ያደረጉ በርካታ ሕጎች እንዲቀየሩ ምክንት የሆነው የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር መሥራች መዓዛ አሸናፊ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆና ስትሾም እንደ ካቢኔው የፆታ ተዋፅዖ መመጣጠን ዜና ሁሉ አገራችን በዓለም በአዎንታዊ መልኩ ሥሟ ተነሳ።
ለዘመናት ትርጉም ያለው የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ መብት እንዲረጋገጥ ቅስቀሳ ሲያደርጉ የነበሩ፣ የሴቶች ውክልና ሊረጋገጥ ይገባል ብለው ባገኙት መድረክ ሲሟገቱ የከረሙ ጥረታቸው ፍሬ አፈራ።
ለእኔ በተለይ በሴቶች መብቶች ዙሪያ ድምፃችንን ለምናሰማና በዚህ ጥላሥር ለተሰባሰብን ድሉን የበለጠ ጣፋጭ የሚያደርገው የሴቶችን መብቶች ጥየቃ መንግሥትን አላግባብ ተዳፈራችሁ ተብለው ድርጅታቸው የተዘጋው እነ መዓዛ አሸናፊ ይገባችኋል ተብለው ለቁልፍ ሥራ መታጨታቸው ነው። አሸባሪ ተብለው በእስር ቤት መከራ ከማየት እስከመሰደድ የደረሱት እነ ብርቱካን ሚደቅሳ መብታቸውን የነሳቸው ተቋም ኃላፊ ሆነው መሾማቸው ነው። በብዙ የሴቶች መብት መሸራረፍ ዘልማድ ሆኖ እንዲቀጥል ፈላጊዎች እንደ ፅንፈኛ የሚታየውን ፌሚኒዝም በይፋ የሚያቀነቅኑ ሌሎች እንደ ፕሬስ ሴክሪታሪዋ ያሉ ፖለቲከኛ ያልሆኑ ዋነኛ የሴት መብት ተሟጋቾች በመንግሥት ከፍተኛ ቦታዎች መግባታቸው ነው።
ያሁኑን ውጤት ጣፋጭ የሚያደርገው በመንግሥት ሳይቀር የነበረውን አሠራር በመገዳደራቸው ድርጅቶቻቸው እስኪዘጉ ‹ጠላት› ተደርገው የተቆጠሩ ዕውቅና ሲሰጣቸው ብቻ ሳይሆን ‹ታውቃላችሁ፣ ትችላላችሁ፣ ኑ ምሩ!› ሲባሉ ማየቱ ነው። ለዚህም ነው ይህ እውን እንዲሆን በአገራችን የመጀመሪያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ቡድን (ሴቶች) የከፍተኛውን ሥልጣን ግማሹን እንዲይዙ ላደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ብቻ ሳይሆን እንደ መዓዛ ያሉ ከእሷ ጋር የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበርን የመሠረቱ፣ ያለምንም ማወላወል የተጋፈጡ ለቆሙለት ዓላማ “ትዳር አፋቺ” እና ሌላ ሥያሜ ተለጥፎባቸው ቢጠሉም ወደኋላ ያላሉ፣ በብዙ ሺዎች ለሚቆጠሩ ሴቶች መከታ የሆኑ በፍርድ ቤት በነፃ እየቆሙ አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሔዱ ያደረጉ ዛሬ ለመጣው ለውጥ ለከፈሉት ዋጋ የምናመሰግናቸው።

የሹመቱ ፋይዳ
የሴቶች ወደ ሥልጣን መውጣት ለምን ያስፈልጋል የሚለውን ተመልክቼ ጽሁፌን ልቋጭ። ግሎሪያ ስቴነም ባለፈው ሰሞን የአሜሪካ ‹የሚድ ተርም› ምርጫን አስመልክቶ በርካታ ሴቶች በእጩነት ስለመቅረባቸው ስትጠየቅ ለሲኤንኤንዋ ክርስቲያን አማንፑር እንደተናገረችው ‹የመጀመሪያው በዲሞክራሲ መርሖ መሠረት ሥልጣን ላይ የሚወጡት ሰዎች በፆታም፣ በዘርም፣ በሃይማኖትም በአመለካከትም አጠቃላዩን ሕዝብ የሚመስሉ መሆን አለባቸው› ብላለች።
በስፋት ተቀባይነት ካገኙ የዲሞክራሲ ፅንሰ ሐሳቦች መካከል አንዱ የፖለቲካ እኩልነት ሲሆን ሁሉም ዜጎች እኩል የፖለቲካ ተሳትፎ መብት አላቸው የሚለው ሐሳብ የዲሞክራሲ ዋና መሠረት ነው። ይህ የዜጎች እኩል ተሳትፎ መረጋገጥ የሚለው ብቻ በቂ ላለመሆኑ ግን ከጥቂቶች በስተቀር በብዙ የዓለም አገራት የሴቶች ውክልና አናሳ መሆን ምስክር ነው። ለዚህም ነው የአውሮፓ አገራትን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ባሉ ፓርላማዎች ጥናት ያደረጉ ምሁራን ከእኩል ውክልና (Equal representation) ይልቅ ገላጭ ውክልና(Descriptive Representation)ተገቢ የዲሞክራሲ ማረጋገጫ መንገድ መሆን አለበት ሲሉ የሚከራከሩት።ገላጭ ውክልና ማለት በፓርላማና በሌላውም የፖለቲካ ሥልጣን ላይ የሚሆነው አካል የሕዝቡን ብዝኃነት ያካተተ ሲሆን ማለት ነው።
ሕዝቡ በትክክል ተወከልኩ የሚለው እያንዳንዱ እሱን የሚመስል ሰው በፓርላማም በቀበሌም በሚኒስትር ደረጃም ሥልጣን ይዞ ማየት ሲችል፣ ድምፁ በሚመስሉትና ኑሮን እሱ በሚያየውና በሚያልፍበት መንገድ ያለፉ ሰዎችን ማየት ሲችል ነው። ይህ በምላሹ ፖለቲካ የተወሰኑ ሰዎች ፍላጎት ወይም ርስት ሳይሆን ብቃትና ዕውቀት ያላቸው ሰዎች በፍላጎት ተነሳስተው የሚገቡበት እንዲሆን ያበረታታል።፡
ከሁሉም በላይ የሴቶች ወደከፍተኛው የሥልጣን እርከን መምጣት ዋጋ የሚኖረው ደግሞ በተለይ ለሴት ሕፃናት ነው። እነሱን የሚመስሉ ሴቶችን በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሲመለከቱ ወደፊት በፖለቲካ ለመሳተፍ፣ እነኛን ቦታዎች ለመያዝ የማለም ዕድል ይኖራቸዋል።
ከዚህ ሌላ ሴቶች ለፓርላማውም ይሁን ከታች ጀምሮ እስከላይኛው የሥልጣን እርከን ሲመጡ ይዘው የሚመጡት የተለየ እይታ አለ። ሴቶች ከዕለት ተዕለት ኑሮ ፣ ወደ ፖለቲካ ከመግባት አንስቶ ሥልጣን ላይ እስከመውጣት ባለው ሂደት የሚያልፏቸው ተግዳሮቶች ከወንዶች የተለዩ ናቸው። ይህን ነገሮችን በተለየ መነፅር የመመልከት ይህንና የተለየ የህይወት ልምዳቸውን ለአመራር ዘይቤያቸው ሲጠቀሙ አመራሩና ሂደቱ የተሟላ እይታና ልምድ የሚጠቀም እንዲሆን ይረዳል።
በተጨማሪም ፖለቲከኞች የወከሉትን ብቻ ሳይሆን የወጡበትን ማኅበረሰብ ችግር የመፍታት አዝማሚያ አላቸው። ሴት ባለሥልጣናት ሲበዙ ፖሊሲዎች ሲወጡ የሴቶች ድምፅ እንዲካተት ያደርጋሉ የሚል ነው እሳቤው።
ደግሞም የፕሬዚዳንትነትም ሆነ የግማሽ ካቢኔው እንዲሁም አሁንም በሌሎች ቦታዎች እስከ ቀበሌ ድረስ ይቀጥላል ብለን በምናምነው ሹመት የሚካተቱ ሴቶች በችሮታ የተሰጣቸው ሳይሆን በመብታቸውም፣ በትግላቸው ያገኙትም ጭምር ነው።
በመጨረሻም“አሁንማ መከላከያ ሚኒስቴር ሆናችሁ፤ ከዚህ በላይ ምን ትፈልጋላችሁ?” የሚል አስተያየት ለሚሰነዝሩ የሚከተለውን መልስ መስጠት አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ ለሴቶች መብቶችን የሚያጎናፅፉ መልካም የሕግ ማዕቀፎች ቢኖሩም፣ በሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት እየጨመረ መጥቷል። ታዳጊ ሕፃናትና ወጣት ሴቶች ሊጠብቋቸው፣ ከለላ ሊያደርጉላቸው በሚገባ የቅርብ በሚሏቸው ሰዎች ሳይቀር ይደፈራሉ። ትምህርት ቤቶች ለሴቶች አመቺ አይደሉም። ሴቶች ዕለት ተዕለት ኑሯቸውአሁንም በሥጋት የተሞላ ነው። ለብዙ ሴቶች በሠላም ወጥቶ መግባት አሁንም ምኞት ነው። በሥራ ቦታዎች ሴቶች አሁንም ሴት በመሆናቸው ብቻ አድልዎና በደል ይፈፀምባቸዋል። ዛሬም “ፈልጌሻለሁ” ያለ ወንድ እንቢ በማለታቸው አሲድ የሚደፋባቸው ሴቶች አሉ። የድህነት ከባድ ጫና ዋነኛ ተሸካሚ ሴቶች ናቸው።
ተስፋችን ይህ ይቀየራል የሚል ነው። የሴቶች ቁጥር በዛ ብሎ በውሳኔ ሰጪነት ላይ መሳተፍ ትርጉም ኖሮት፣ በየዘርፉ ሴቶች ያሉበትን ሁኔታ አይቶ ሆን ብሎ ያንን ለመቀየር የሚሠራ መንግሥት እንዲኖረን ያደርጋል የሚል ነው።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here