መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበነጋሪት ጋዜጣ የሚወጡ አዳዲስ ሕጎች የስርጭት ውስንነት እንዳለባቸው ተጠቆመ

በነጋሪት ጋዜጣ የሚወጡ አዳዲስ ሕጎች የስርጭት ውስንነት እንዳለባቸው ተጠቆመ

በነጋሪት ጋዜጣ የሚወጡ አዳዲስ ሕጎች የስርጭት ውስንነት እንዳለባቸው የሕግ ባለሙያዎች ገለጹ። በአገሪቱ በተለይም በፌዴራል ደረጃ የሚወጡ አዳዲስ ሕጎች፣ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡ በኋላ ለማኅበረሰቡ ብሎም ለሕግ ባለሙያዎች ሳይቀር በቀላሉ ተደራሽ እንዳልሆኑ ነው የተገለጸው።

ባለሙያዎቹ እንደገለጹት፣ የሚወጡ ሕጎች ተፈጻሚ በሚሆኑበት ማኅበረሰብ ዘንድ እንዲታወቁ እና ማኅበረሰቡም ከሕጉ አንጻር ሕይወቱን እንዲመራ ማድረግ ያስፈልጋል። ሰዎች ሕግን ባለማወቅ ከጥፋተኝነት ነጻ ስለማይሆኑም ሕጉን ወደ ማኅበረሰቡ ማሰራጨትና ማሳወቅ የመንግሥት ግዴታ መሆኑን አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሕግ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በኦሮሚያ ክልል እና በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቃ የሆኑት ገመቹ ጉተማ፣ የሕግ ባለሙያዎች ሳይቀር በነጋሪት ጋዜጣ የሚወጡ አዳዲስ ሕጎችን በግዥ እንደሚያገኙ ጠቅሰው፣ ‹‹በጋዜጣው የሚወጡ የፌዴራል ሕጎች አዲስ አበባ ውስጥ ሦስት ቦታ ብቻ እንደሚሸጡ
አውቃለሁ። የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር የት እንደሚሸጥ አላውቅም። የኦሮሚያ ክልልም ለመግዛት እንኳን አይገኝም›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ስለዚህም፣ በክልሎችና በፌዴራል ደረጃ የሚወጡ ሕጎች ዜጎች እንዲያውቋቸው የሚደረግበት መንገድ ችግር ያለበት ነው ብለዋል። ጉዳዩ እንደችግር ታይቶ መፍትሄ ሊሰጠው ይገባል ያሉት ጠበቃው፣ ‹‹ብዙ ወንጀሎች በማኅበረሰብ ልማድ በቀላሉ ይታወቃሉ። ነገር ግን የሰው ልጅ ግንኙነት የተቀራረበ በመሆኑና ነገሮች በመወሳሰባቸው አንዱ ማኅበረሰብ እንደወንጀል የማይቆጥረው ባህል ወደ ሌላኛው ማኅበረሰብ ገብቶ ወንጀል ሊሆን ይችላል። ማኅበረሰቡም ይህን ሳያውቅ ወንጀል እንዳይሠራ ማሳወቅ ያስፈልጋል።›› ነው ያሉት።

ሕጎችን ከነጋሪት ጋዜጣ ሌላ ከድረ ገጽ እንደሚያገኙ ጠቁመውም፣ ይህም ግን ከመንግሥት ኃላፊነት አንጻር በደንብ እየተሠራበት አይደለም ሲሉ ተናግረዋል። ይልቁንም በራሳቸው ወጪ ጋዜጣውን ገዝተው ወደ ‹‹PDF›› በመቀየር በነጻ የሚያሰራጩና ከመንግሥት በላይ ማኅበረሰቡን እያገለገሉ ያሉ  አካላት መኖራቸውን ነው የገለጹት።

ፍትህ ሚኒስቴርም የበፊት ሕጎችን ጨምሮ በድረ ገጽ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፣ በበኩሌ በደንብ ስለማይሠሩበት ይሁን በሌላ
ምክንያት በዚህ ለመጠቀም እቸገራለሁ ብለዋል። አክለውም፣ የሕግ ዓላማ ሰዎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው እንዲኖሩና የተረጋጋ
ማኅበረሰብ ለመፍጠር ነው ካሉ በኋላ፣ በነጋሪት ጋዜጣ የሚወጡ በውድ ዋጋ መሸጣቸው ሌላኛው ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።

ስለሆነም ለነጋሪት ጋዜጣ ተጨማሪ እሴት ግብር ማስከፈል የሕግ አግባብ አለው ወይ ሲሉ ጠይቀው፣ ቢኖረው እንኳን የጋዜጣውን
ተደራሽነት የባሰ ችግር ውስጥ አይከተውም ወይ ብለዋል። የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነትና የማኅበራዊ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዳንኤል ኃይሌ፣ በጋዜጣው ላይ የተነሳውን የስርጭት ችግር እንደማያውቁ ገልጸው፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወጡ አዳዲስ አዋጆች ብዙም ፈላጊ የሌላቸው ከሆነ ከ500 እስከ 1000 ይታተማሉ። ፈላጊ ካለ ደግሞ ከ20 ሺሕ እስከ 25 ሺሕ የሚታተሙ አሉ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
ስለዚህም፣ የህትመት መጠኑ ከፍላጎት ጋር

የተያያዘ መሆኑን ጠቁመው፣ የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ በአዲስ አበባ ሦስት ቦታ እንዲሁም በሀዋሳ አንድ የሽያጭ መደብር እንደሚገኝ
ተናግረዋል። ለክልሎችም የሽያጭ ወኪል በሆነው በሜጋ አሳታሚ ድርጅት በኩል እያገኙ መሆኑን አንስተው፣ በኹሉም ቦታ መሸጫ
ቦታ ለመክፈት ግን አዋጭ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

የታተሙ ሕጎችን እፈልጋለሁ የሚል ማንኛውም ሰው በግዥ የሚያገኝ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፣ የኢትዮጵያ ሕግ ከመጽሐፍ በስተቀር ማንኛውም ህትመት ተጨማሪ እሴት ግብር ያስከፍላል ስለሚልም ነጋሪት ጋዜጣም ተጨማሪ እሴት ግብር ይከፈልበታል ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች