መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን የሚቀርፍ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው

በግል ትምህርት ቤቶች ክፍያ ላይ የሚነሱ ጥያቄዎችን የሚቀርፍ መመሪያ እየተዘጋጀ ነው

በግል ትምህርት ቤቶች ላይ የሚነሱ የክፍያ ጥያቄዎችን የሚቀርፍ የማሻሻያ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ። በትምህርት ሚኒስቴር አጠቃላይ የትምህርት ክፍል የክትትልና ግምገማ ባለሙያ በላይ አወቀ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከዚህ በፊት በነበረው ሕግ መሠረት በግል ትምህርት ቤቶችና በወላጆች መካከል በተደረገ ስምምነት የተማሪ ክፍያ እንደሚፈጸም እና አሁን ላይ ይህን አሠራር ለማሻሻል የሚያግዝ መመሪያ እየተዘጋጀ ይገኛል ብለዋል።

አንድ የግል ትምህርት ቤት የተማሪ የትምህርት ቤት ክፍያ ጭማሬ ወይም ቅነሳ ለማድረግ በሚገደድበት ወቅት የትምህርት ዘመኑ ከማለቁ ከሦስት ወራት በፊት ቀደም ብሎ ለወላጆች እና ለትምህርት ቤቱ ኮሚቴዎች አሳውቆ ትምህርት ቤቱ ከሚያቀርበው ምክንያታዊ መረጃዎች ላይ ተደግፎ በወላጆች እንዲሁም በትምህርት ቤቱ ኮሚቴ በተደረገ ሰፊ ውይይት የትምህርት ቤት ክፍያው እንዲወሰን የሚያደርግ መመሪያ ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎን አጠቃላይ የግል ትምህርት ቤቶች ከአደረጃጀታቸው ጀምሮ ስርዓተ ትምርታቸው ጀምሮ ምን እንደሚመስል እና ዓለም ዐቀፍ የሆኑትን በትኩረት የመለየት፣ ለማኅበረሰብ የተቋቋሙትን የመለየት፣ ለትርፍ የተቋቋሙትን የመለየት፣  የሰው ኃይላቸውን የመለየት፣ የመሠረተ ልማታቸው እና ሌሎችንም ጨምሮ ምን እንደሚመስሉ የመለየት እና መልስ ሊሰጥ የሚችል የማሻሻያ መመሪያ መሆኑንም ባለሙያው ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

ባለሙያው አክለውም፣ አሁን ላይ ትምህርት ሚኒስቴር የሚሻሻለውን መመሪያ እያዘጋጀ የሚገኝ ሲሆን፣ መመሪያው ከተጠናቀቀ በኋላ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ይደረግበታል ብለዋል። መመሪያው ውይይት ወይም ምክክር ተደርጎበት የሚሻሻሉ ሐሳቦች ካሉ የሚሻሻልበት እድል ሊኖር ስለሚችል፣ መመሪያው ተጠናቆ መቼ ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል መጥቀስ እንደማይቻል ተነግሯል።

በተጨማሪ የማሻሻያ መመሪያው ተዘጋጅቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ለፍትህ ሚኒስቴር ቀርቦ ቁጥር ተሰጥቶት ከፀደቀ በኋላ መመሪያው ተግባራዊ
እንደሚሆን እና ለሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ይገለፃል ተብሏል። ትምህርት ሚኒስቴር በቀጣይ አውጥቶ ተግባራዊ የሚያደርገውን የወላጅና የግል
ትምህርት ቤቶችን የማሻሻያ መመሪያ የማይተገብሩት ላይ በሚቀመጠው ሕግ መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆኑም ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር አጠቃላይ የትምህርት ክፍል የክትትልና ግምገማ ባለሙያው አያይዘውም፣ በአዲስ አበባ ከተማ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ 29 የሚሆኑ የአንደኛና የኹለተኛ ደረጃ ዓለም ዐቀፍ ትምህርት ቤቶች አሉ። እነዚህ ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሯቸውም ሆነ አቅም ለሌላቸው ተማሪዎቻቸው ነፃ የትምህርት እድል የሚሰጡበት ሂደት ያለ ቢሆንም፣ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ግን የተቀመጠ አስገዳጅ ሕግ የለም ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ እነዚህ ዓለም ዐቀፍ ትምህርት ቤቶች ምን ያህል ተማሪዎችን የማስተማር አቅም እንዳላቸው ለጊዜው ለመጥቀስ እንደሚቸገሩ ያነሱት ባለሙያው ናቸው። በተጨማሪ ከላይ የተጠቀሱት ዓለም ዐቀፍ የትምህርት ተቋማት ሕግና ደንባቸው እንደሚለያይ እና እንደመስፈርታቸው መሠረት ለተማሪዎቻቸው ነፃ የትምህርት እድል እንደሚሰጡም ተገልጿል።

እነዚህ ትምህርት ቤቶች ለማኅበራዊ ኃላፊነት እንደመቋቋማቸው መጠን ነፃ የትምህርት እድሎችን በሚያመቻቹበት ወቅት ትምህርት ሚኒስቴር እውቅና የመስጠት ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑንም ባለሙያው ጠቁመዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች