መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየጉራጌ ዞን ክላስተር ያለመቀበል አቋሙን ይዞ እስከ ዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚያቀና...

የጉራጌ ዞን ክላስተር ያለመቀበል አቋሙን ይዞ እስከ ዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚያቀና ተገለጸ

የጉራጌ ዞን ለዓመታት ሲያቀርበው የቆየውን የክልልነት ጥያቄ በተመለከተ፣ የብልጽግና መንግሥት በክላስተር እንዲደራጅ በቅርቡ ያወረደውን ትእዛዝ ተቃውሞ እስከ ዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት የሚያቀና መሆኑ ለአዲስ ማለዳ ተገለጸ። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሐምሌ 28/2014 ባደረገው ጉባኤ በክላስተርነት ከተደራጁት ሌሎች ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ጋር በነበረው ጉባኤ፣ የጉራጌ ዞን የክልልነት ጥያቄ ያልተካተተው መንግሥት ሕገ መንግሥቱን እየጣሰ ስለሆነ ነው ተብሏል።

መንግሥት ያወረደውን የክላስተር አደረጃጀት የጉራጌ ዞን እንዳልተቀበለ አቋሙን በመግለጽ፣ መብቱ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲከበርለት እስከ ዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት ሊያቀና መሆኑን የሕግ አማካሪና ጠበቃ ጀምብር አብዶ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል፡፡ የጉራጌ ዞን ህዳር 7/2011 በምክር ቤቱ ተሰብስቦ በክልልነት መደራጀት እንደሚፈልግ ያለምንም ተቃውሞ መወሰኑንና ሕገ መንግሥቱ በሚያዘው መሠረት ሕዝበ ውሳኔው እንዲፈጸም ለክልል ምክር ቤት ከደጋፊ ሰነዶች ጋር መላኩን ያስታወሱት ጀምበር፤ የክልልም ሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምላሽ በመስጠት
ፈንታ ዝምታን መርጧል ነው ያሉት።

በመሆኑም፣ የጉራጌ ዞን <በ2011 የወሰንኩት የክልልነት ጥያቄ ይፈጸምልኝ። በክላስተርነት ግን አልደራጅም።> የሚል ሕጋዊ አቋሙን ሊቀለብስ አይችልም ተብሏል። የሕግ አማካሪ እና ጠበቃው በሕገ መንግሥቱ  ክላስተሪንግ የሚል የሕግ መሠረትም ሆነ ጽንሰ ሐሳብ ስለሌለ፤ የጉራጌ ዞን ትዕዛዙን ሊቀበል አይችልም። የክልልነት ጥያቄው ግን ምላሽ ሊያገኝ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።

ክላስተሪንግ ‹‹ብልጽግና ከኋላ ኪሱ በመምዘዝ ያመጣው ነው›› ያሉት ጀምበር፤ የሕግ አካል እና ባለሙያ እንደመሆናችን መጠን እስካሁን አናውቀውም ብለዋል። ጀምበር ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ ስምንት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ስለመሆናቸው፣
እንዲሁም ንዑስ አንቀጽ ኹለት ደግሞ ይህን ሥልጣናቸውን የሚተገብሩት በተወካዮቻቸው አማካኝነት መሆኑን እንደሚደነግግ ጠቅሰዋል።

አያይዘውም የጉራጌ ክልል የሕገ መንግሥት መብቱን ተጠቅሞ የክልልነት ጥያቄው እንዲመለስለት በመጠበቅ ላይ ነው ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ይህንኑ መሠረት በማድረግ በተወካዮቹ በኩል ሙሉ ድምጽ አድርጎ በውሳኔው ላይ ሕዝበ ውሳኔ ይደረግልኝ የሚል አቋም እንዳለው ጀምብር ተናግረዋል።

በመሆኑም ጉራጌ ክላስተር አልቀበልም ማለቱ ጉዳዩ የሕግ መሠረት ስለሌለውና ምክር ቤቱ ተወያይቶ ሕዝቡ ክላስትር እሆናለሁ ብሎ ስላልወሰነ ነው ያሉት የሕግ አማካሪው፣ መንግሥት ክላስተር ተቀበሉ የሚለው በግድ ለመጫን ነው ሲሉ ገልጸዋል። ምንም ዓይነት ችግር ሳይፈጠር በወልቂጤ ከተማ የመከላከያ ኃይል ከበባና ወከባ መፈጠሩ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ሰሞኑን በከተማው ላይ በወጣው ኮማንድ ፖስት ጭራሽ
ጉራጌ ክልል ነው የሚል ቲሸርት መልበስ፤ ክላስተር አልፈልግም የሚል ወረቀት መያዝ እንደማይቻል መመሪያ እየተላለፈ ነው።

በወለጋ፤ በአማሮ ልዩ ወረዳ እና በጉጂ አዋሳኞች እንዲሁም በሌሎች የጥቃት ሰለባ በሆኑ አካባቢዎች የመከላከያ ኃይል በአሁኑ ወቅት ሊሰለፍባቸው ሲገባ ወደ ወልቄጤ ማምጣቱ በራሱ ከሕግ አንጻር አግባብነት የለውም ተብሏል። “ሥልጣን ላይ ያለው የብልፅግና መንግሥት ሕገ መንግሥቱን አስገድዶ እየደፈረ ነው” ሲሉ ነው የሕግ አማካሪና ጠበቃው ለአዲስ ማለዳ የገለፁት።

ጉራጌ ከዚህ በኋላ ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሄደ ለሦስተኛ ጊዜ ቅሬታውን ለማቅረብ ነው ያሉት ጀምበር፤ መብታቸው በሕገ መንግሥቱ መሀረት ካልተከበረላቸው እስከ ዓለም ዐቀፍ ፍርድ ቤት እንደሚያቀኑ ነው የተናገሩት። ገዢው መንግሥት ሕገ ወጥ አሠራር እየተከተለ ነው የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ የሕዝብን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ይገባዋል ሲሉ ጉዳዩን ከሕግ አንጻር አብራርተዋል። ምንም ቢፈጠር የጉራጌ ዞን የያዘው አቋም ሕገ መንግሥቱን መሠረት ያደረገ በመሆኑ፣ የክልልነት ጥያቄው ፍትሃዊ ምላሽ ተችሮት ክልል እስካልሆነ ድረስ ትግላችንን እንቀጥላለንም ብለዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads
- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች