እኩልነት ለፍትሐዊነት !

ሴቶች ከወንዶች እኩል ናቸው ሲባሉ በሁሉም ነገር የሚመስላቸው አሉ። በተፈጥሮ የመለያየታቸውን ያህል እኩል እድል የሚያገኙበት ሁኔታም እንዳለ ግልጽ ነው።

ለዚህ ተፈጥሯዊ ልዩነትና ተመሳሳይነት መገለጫ የሚሆኑ የተለያዩ ድርጊቶች አሉ። ሴት ልጅ በሁሉም የሥራ ዘርፍ እንደወንድ ተሳትፋ ውጤታማ የምትሆንባቸው በርካታ የስራ ዘርፎች ቢኖሩም፣ በባህልም ሆነ በሃይማኖት የማይፈቀድላት ቦታዎች አሉ።

ለምሳሌ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶም ሆነ በእስልምና ሴቶች የሃይማኖት እናት መሆን አይቻላቸውም። ካህን ሆነው ማገልገል የማይችሉበት የራሱ የሆነ ምክንያት ቢኖረውም ፣በቡዲዝምም ሆነ በሂንዱይዝም ተመሳሳይ የፆታ ልዩነቶች መኖራቸው ይታወቃል።

በዓለማዊው አስተሳሰብ ምንም እኩል ናቸው ቢባልም፣ እነሱ ላይ በታሪክ የነበረውን መድሎ ለማካካስ የተለየ መስፈርት ሲወጣላቸውም ይሰማል። ይህ በተዘዋዋሪ የበታችነታቸውን እንዲያምኑ ያደርጋል ብለው የሚቃወሙ ቢኖሩም፣ ጊዜያዊ በመሆኑ ችግር አያስከትልም ሲሉ ምላሽ ይሰጣሉ።

ሴት ከወንድ እኩል አትሆንም የሚለው አስተሳሰብ ይበልጥ የሚንፀባረቀው በስፖርቱ ዓለም ሲሆን፣ በተለያዩ ውድድሮች ሴትና ወንድ እንደችሎታቸው ተብሎ በአንድ ውድድር እኩል ሲሳተፉ አይታይም። በሩጫም ሆነ በቦክስ አልያም በእግር ኳስ የተለያየ ጎራ ተዘጋጅቶ የሴቶችና የወንዶች ውድድር እየተባለ ለየብቻ መደረጉ ልዩነቱን ያመለክታል ብለው የሚሞግቱ አሉ።

ወንድ በተፈጥሮ ለጉልበት የተፈጠረ ነው ብለው የሚሞግቱ ሴት በተፈጥሮ እንደተለገሰችው በመውለድ ብቃት እንደመወዳደር ይቆጠራል ብለው ንፅፅሩን የሚተቹ በርካቶች ናቸው። እንዲህ አይነቱ አካላዊ መለያየት የሚያመጣው ልዩነት እንጂ፣ በሥነ ባህሪ ደረጃ ሴት ሩህሩህ ናት አልያም የበለጠ ጨካኝ ናት የሚሉ ሙግቶችንም ሲያስከትል ይሰማል።

በሌላ በኩል፣ በአካላዊ ብቃት ረገድ አማካይ ወንድ ከአማካይዋ ሴት ይበልጣል ብለው የሚሟገቱትን ያህል፣ ምንም ዓይነት የአካል ብቃት በማያስፈልጋቸው የቃላት ጨዋታን በመሳሰሉ የአስተሳሰብ ብቃትን በሚጠይቁ ውድድሮች ለየብቻ መስፈርት አለመደረጉን የሚያነሱ አሉ።

በሂሳብና  ፊዚክስ ትምህርት፣ እንዲሁም የመኪና እሽቅድምድምን በመሳሰሉት ውድድሮች በብዛት ወንዶች ማሸነፋቸው ይታወቃል። ለየብቻ የሴትና የወንድ ተብሎ ሽልማትና ውድድር መደረጉ የሚያመለክተው ቁምነገር አለም ይባላል። ለምሳሌ፣ ቼዝን ከወሰድን የወንድ ጨዋታ ተደርጎ ስለሚወሰድ ሴትና ወንድ እርስ በርስ እንዲጋጠሙ አይደረግም። አልፎ አልፎ በቅልቅል ውድድር ቢደረግም፣ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ግን የየጾታው አሸናፊዎች ይገለፃሉ እንጂ የኹሉም ተብሎ አይታወቅም።

የጥያቄና መልስ ውድድሮች ፆታን መሰረት አድርገው አይካሄዱም የሚሉ የልዩነት መስኮቹ ጠባብና ከሰውነት ብቃት ጋር የተገናኙ ናቸው ብለው ያምናሉ። ይህ ቢሆንም ግን፣ ከአብዛኛው ወንድ የሚበልጡ ጠንካራ ሴቶች መኖራቸው የሚካድ አይደለም።

ኹለቱን ፆታዎች በሁሉም ነገር ማወዳደር የአንድ ሳንቲምን ኹለት ገፅታዎች ከማበላለጥ አይሻልም። አንደኛው ከሌላው ተነጥለው የማይኖሩና የሠራቸው እንዳስጌጣቸው የተለያዩ ውበት ያላቸው መሆናቸውን መረዳት ግድ ይላል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች