መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናበሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ844 ኪሎ ግራም በላይ የዝሆን ጥርስ ተይዟል ተባለ

በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋወር የነበረ ከ844 ኪሎ ግራም በላይ የዝሆን ጥርስ ተይዟል ተባለ

በ2014 በጀት ዓመት ከ844 ኪሎ ግራም የሚልቅ የዝሆን ጥርስ በሕገወጦች ሲዘዋወር መያዙን የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ባለሥልጣኑ እንዳስታወቀው ከ57 ኪሎ ግራም በላይ የከርከሮ ጥርስ፣ ከ79 ኪሎ ግራም የሚልቅ የጉማሬ ጥርስ እና ከአምስት ኪሎ ግራም የበለጠ የአውራሪስ ቀንድ ከሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ተይዟል።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን በላከው የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሪፖርት መሠረት፣ በሕገ ወጥ የዱር እንስሳት እና ውጤቶቻቸው ንግድና ዝውውር ከባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ በሕገወጦች የተገደሉ አራት ዝሆኖች እና ክብደቱ ከ29 ኪሎ ግራም በላይ የሚመዝን ሰባት ጥርስ ተይዞ ወደ ተቋሙ ገቢ መደረጉን አመላክቷል።

በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ ከጉምሩክ ኮሚሽን እና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በተደረገ የኢተለጀንስ ኦፕሬሽን ኹለት የዝሆን ጥርስ በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፣ ተጠርጣሪው ማምለጡም ነው የተገለጸው።

እንዲሁም፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ኦሞ ብሔራዊ ፓርክ፣ ጂንካ ከተማና አካባቢው በተደረገ ኦፕሬሽን ሦስት የዝሆን ጥርስ እና ኹለት የከርከሮ ጥርስ የተያዘ ሲሆን፣ በዚሁ ጉዳይ አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ይገኛል ተብሏል።

በኦሮሚያ ክልልም እንዲሁ ሰፊ ሕገወጥ የዱር እንስሳት ውጤቶች ዝውውር የተካሄደ ሲሆን፣ በቦረና ዞን ጠቅላላ ክብደቱ ከ34 ኪሎ ግራም በላይ የሆነ የአውራሪስ ቀንድ፣ አራት የዝሆን ጥርስ እና ኹለት የነብር ቆዳ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተመላክቷል።

ከእነዚህም ሕገወጥ አዘዋዋሪዎች፣ ሦስት የአውራሪስ ቀንድ ይዞ ከተገኘው ግለሰብ ውጪ የተቀሩት በቁጥጥር ስር አልዋሉም ነው የተባለው።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም እንዲሁ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ ኤርፖርት ከዴሞክራቲክ ኮንጎ በኢትዮጵያ በኩል ወደ ሊባኖስ ሲጓዝ የነበረ ተላላፊ መንገደኛ 60 ኪሎ ግራም የሚመዝኑ ከዝሆን ጥርስ የተሠሩ ጌጣጌጦችን ይዞ ለማለፍ ሲሞክር መያዙንም እንዲሁ ለማወቅ ተችሏል።

በተለያዩ ቦታዎችም አቦሸማኔ፣ ጦጣ፣ ጭላዳ ዝንጀሮና የአንበሳ ደቦልን የመሳሰሉ የዱር እንስሳት ከሕገወጥ አዳኞችና አዘዋዋሪዎች በሕይወት ሳሉ ተይዘው ወደ ተፈጥሮ ቦታቸው እንዲመለሱ መደረጉ ተመላክቷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በዱር እንስሳትና መኖሪያ አካባቢዎች ላይ የሚፈጸሙ በርካታ ሕገወጥ ድርጊቶች መኖራቸውም በሪፖርቱ ተገልጿል።

ለአብነትም በአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ፣ በተለያዩ ቦታዎች የከሰል ማክሰል ሥራ በስፋት የታየ ሲሆን፣ የዱር እንስሳትን ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ለምግብነት የማደን ተግባር እንደሚከናወንም ነው የተጠቆመው።

በጋምቤላ ብሔራዊ ፓርክም በተለይ የዝሆን ሕገወጥ አደን አሁንም እንዳለና ከአንበሳ ጋር የሚፈጠር ግጭት ለሕገወጥ አደኑ ምክንያት ሆኖ እንደቀጠለና በአካባቢው ባለው የፀጥታ ችግር ምክንያት ሕገወጥ ተግባሩን መቆጣጠር አዳጋች መሆኑ ተጠቅሷል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእንጦጦ ተራራ ውስጥ የነብር አደን መኖሩም እንደ ችግር የተጠቀሰ ሲሆን ፤ በሕገ ወጥ መንገድ የዱር እንስሳትን በሕይወት ይዞ ለቤት ውስጥ አገልግሎት ማዋል ብሎም በሕግ አስፈጻሚና በፍትህ አካላት ዘንድ የግንዛቤ ማነስ እንዳለ ነው የተገለጸው።

በጥቅሉም በኹሉም የዱር እንስሳት መኖሪያ አካባቢዎች፣ ከልቅ ግጦሽ፣ ከደን ጭፍጨፋ፣ ከሕገወጥ አደን እንዲሁም ከግንዛቤ ማነስ ጋር የተገናኙ በርከት ያሉ ችግሮች እንዳሉ ነው ለማወቅ የተቻለው።

በሌላ በኩል ከአገር ውስጥ እና የውጪ ጎብኚዎች 70 ሚሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 67 ሚለዮን ብር በላይ ገቢ ተገኝቷል ነው የተባለው።

ገቢው  ከባለፉት ዓመታት ገቢ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ሲሆን፣ ይህም የሆነው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ በጣም ዝቅተኛ ገቢ በመሰብሰቡ እንዲሁም በፓርኩ ውስጥ ሊከናወኑ ታቅደው የነበሩ ኹለት የአየር ላይ የፊልም ቀረፃዎች በመሰረዛቸው መሆኑ ተመላክቷል።

- ይከተሉን -Social Media

በውጭ ጎብኚዎች በብዛት የሚጎበኙት የነጭ ሳር፣ አብያታ ሻላ ሀይቆች፣ አዋሽ፣ ማጎና የባሌ ተራራዎች ብሔራዊ ፓርኮች የቱሪስት ቁጥርም በጣም አነስተኛ በመሆኑ ነው ተብሏል።


ቅጽ 4 ቁጥር 196 ሐምሌ 30 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች