ኦነግ ሸኔ በሰሜን ሸዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ሕዝቡን በማሳመጽ ላይ ነው ሲል ዞኑ ገለፀ

0
1641

በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ወረዳ ከመስከረም 24/2012 ጀምሮ ተከስቶ ለነበረው ግጭት መነሾ የሸኔ ታጣቂ ቡድን በሰሜን ሸዋ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚያደርገው እንቅስቃሴ ውጤት መሆኑን የዞኑ የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊ ካሳሁን እንቢአለ ለአዲስ ማለዳ አስታወቁ።

የቀድሞው የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባር የቆር ክንፍ የነበረው እና ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀሰው የሸኔ ታጠቂ ቡድን በኦሮሚያ ልዩ ዞን ውስጥ በመግባት ‹‹አማራ ሃይማኖትህን ሊያስቀይርህ እና ሊወርህ ነው›› በሚል ለሕዝቡ በሚያሰራጫቸው መረጃዎች የተነሳ በዞኑ ሰላም እንዳይኖር ምክንያት መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት የጸጥታ ኃላፊው፣ በዚህ ሳቢያ ከቅዳሜ መስከረም 24/2012 ጀምሮ በተከታታይ አምስት ቀናት በተካሔዱት ግጭቶች የአምስት ሰዎች ሕይወት ማለፉንና 8 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

‹‹የክልሉን ሰላም ለመንሳት በሚደረገው እንቅስቃሴ በየአካባቢው አጀንዳ በመቀበል የሚንቀሳቀስ ኃይል አለ›› ያሉት ካሳሁን፣ ‹‹ሸዋ ላይም በእነዚህ ኃይሎች ነው ችግሩ እየተፈጠረ ያለው›› ብለዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ ተፈራ ወንድምአገኝ በበኩላቸው፣ የሸኔ ታጣቂ ኃይሎችን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን እና መታወቂያና ሌሎችም ማስረጃዎች መገኘታቸውን በማስረዳት የምርመራው ውጤት ሲጠናቀቅ ዝርዝር መረጃውን ይፋ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

መስከረም 24/2012 በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ከተማ የአማራ ልዩ ኃይል በሚንቀሳቀስበት አካባቢ አንድ የታጠቀ ግለሰብ ሳይፈቀድለት ወደ ወታደሮቹ ሲቀርብ ለመቆም ፈቃደኛ ባለመሆኑና ተኩስ በመክፈቱ በተወሰደ እርምጃ መገደሉንና ያን ተከትሎ ከተለያዩ የከተማዋ አቅጣጫዎች የኦነግ ሠራዊት አባላት ተኩስ መክፈታቸውን የሰሜን ሽዋ ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ በሰጠው መግለጫ ገልጿል።

የዞኑ የኮሚዩኒኬሽን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሠራዊት እንደሌለው ብዙ ጊዜ ቢናገርም እውነታው ግን ከዛ የተለየ መሆኑን ያወሳል። ‹‹ኦነግ አጣዬ ምን ሊሠራ እንደመጣ ግራ የሚያጋባ ነው›› ያሉት ካሳሁን፣ ይህንን አስመልክቶ አሁን መናገር ጊዜው አለመሆኑንና በቀጣይ የክልሉንም ሆነ የዞኑን ሰላም ለመጠበቅ በተደራጀ መልኩ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰው በአሁኑ ሰዓትም የክልሉ ልዩ ኃይል፣ መከላከያ ሠራዊትና ፌዴራል በጋራ እየሠሩ መሆኑን አውስተዋል።

የሰሜን ሸዋ ዞን የሕዝብ ደኅንነትና የሰላም ግንባታ መምሪያ ኃላፊ ካሳሁን እምቢአለ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ከትላንት ጀምሮ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ከባለፉት ቀናት አንጻር መሻሻሎች አሉ።

አራት ቀናትን ባስቆጠረው ግጭት ከአጣዬ ከተማ በተጨማሪ በዙሪያው በሚገኙ ሌሎች ቀበሌዎችም የተኩስ ልውውጡ ተዛምቶ የነበረ ሲሆን እስከትላንትና ድረስ አምስት ሰዎች ሲሞቱ ስምንት ሰዎች ደግሞ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ መቁሰላቸውን የዞኑ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። የዓይን እማኞች ግን የሟቾቹን ቁጥር 8 ሲያደርሱት የቆሰሉትን ሰዎች ደግሞ 13 ያደርሷቸዋል።

ባለፈው ዓመት በከተማዋ ተመሳሳይ ግጭት ተፈጥሮ የሰው ሕይወት አልፏል፣ ንብረት ወድሟል፣ አብያተ ክርስትያናት ተቃጥለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here