የደሴና ኮምቦልቻ መንገድ በ13 ኪሎ ሜትር ሊያጥር መሆኑ ተነገረ

0
937
  • ኹለቱን ከተሞች በ7 ኪሎ ሜትር ለማገናኘት እየተሠራ መሆኑም ታውቋል

የደቡብ ወሎ ዞን መቀመጫ የሆነችውን የደሴ ከተማን ከኮምቦልቻ ከተማ ጋር የሚያገናኘውን እና በተለምዶ ሃረጎ ተብሎ የሚጠራውን ጠመዝማዛ እና 20 ኪሎ ሜትር መንገድ በዋሻ ውስጥ በሚዘረጋ 13 ኪሎ ሜትር የሚተካ መንገድ ለማሠራት ሥራ መጀመሩን የደሴ ከተማ አስተዳዳር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ደሴ ከተማ በተለምዶ አሬራ አካባቢ የሚገኘውን አዝዋ ገደል (ዶሮ መዝለያ) ዋሻ በመሥራት ኹለቱን ከተሞች ለማገናኘት የአዋሽ ኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት ‹‹ያፒ መርከዚ›› የተባለው ሥራ ተቋራጭ ሥራውን እንዲሠራ ተመርጦ ሥራ መጀመሩን የከተማ አስተዳደሩ ገልጿል።

ኮምቦልቻ ከተማ የአየር ማረፊያን ጨምሮ የተለዩ የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶች የሚገኙ ሲሆን በዚህም ቀንድ ከብት ንግድን ጨምሮ የተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች የሚደረግባት ከተማ መሆኗ ይታወቃል። ደረቅ ወደብ፣ በቅርቡ ተመርቆ ሥራ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀውን የኮምቦልቻ ሀራ ገበያ የባቡር ፕሮጀክት መዳረሻ የሆነችው ከተማዋ፣ ከጅቡቲ አፋር አድርጎ ወደ ኮምቦልቻ የሚደር የሚገኝበት ከተማ መሆኑ የመንገዱን ማጠር ምክንያት ተደርጎ ይወሰዳል።

የደሴ ከተማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ብርቱካን ሃብቴ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ በመንገድ መሰረተ ልማት ምክንያት ኮምቦልቻ፣ ደሴና ወልድያ መስመሮች ከርዝመታቸው ባለፈ በተደጋጋሚ ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ ነዋሪዎች ቅሬታ እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል። ክልሉ መንገዶቹን ዘመናዊ ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ በመግለፅ፤ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስና የመንገድ ችግሮችን ለመቅረፍ ከፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ጋር በጋራ የመሥራት እቅድ እንዳለ አመልክተዋል።

በከተማ አስተዳደሩ ለመሰራት እቅድ የተያዘለት የደሴ ኮምቦልቻ መንገድ በሕብረተሰቡ ከ7 ዓመት በፊት ጀምሮ ጥያቄ ሲቀርብበት እንደነበር ብርቱካን የገለጹ ሲሆን፣ በዚህ መንገድ ሳቢያም በከተማው ሕዝብና በአስተዳደሩ መካከል አለመግባባቶች እንደነበሩ አስታውቀዋል።

ባለሙያዎችና የክልሉ ኃላፊዎች ወደ አካባቢው በመሔድ ግምገማ አድርገው መመለሳቸውን የገለጹት ኃላፊዋ፣ ኹለት ወር የፈጀ ጥናት ተደርጎ የዋጋ ግምት እየወጣለት መሆኑንም ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ጉዳዩን ወደፊት ይፋ እንደሚያደርገው ያስታወቁት ኃላፊዋ፣ የዋጋ ግምት ወጥቶለት ሲያበቃና ሥራው ሊጀመር እንቅስቃሴ ውስጥ ሲገባ ግልጽ መረጃዎቹን እናሳውቃለን ብለዋል። የሥራው መጀመር በሀረጎ ጠመዝማዛ መንገድ ለተንገላታው የኹለቱ ከተሞች ነዋሪ ትልቅ የምስራች ነው ብለዋል።

አዲሱ መንገድ ከኮምቦልቻ ዩኒቨርስቲ አደባባይ ኮስፒ ተብሎ እስከሚጠራው አካባቢ ያለውን መንገድ የሚያካትት ሲሆን፣ በደሴ ከተማ በተለምዶ ከአራዳ እስከ ዶልፊን ያለውን አካባቢ መንገዶቹ እንደሚያቋርጡት ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት። አዲሱ እቅድ የሕዝቡን የዘመናት የትራንስፖርት ችግር ከመቅረፉም ባሻገር ለኹለቱ ከተሞች ፈጣን እድገት ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሏል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገረቻቸው የፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሳምሶን ወንድሙ፣ የመንገድ ሥራው በፌደራል መንገዶች ባለሥልጣን እንደማይሠራና በከተማ አስተዳደሩ እንደሚሠራ ገልጸው ከክልሉ ለሚነሱ ማናቸውም የድጋፍ ጥያቄዎች ከተቋማቸው ምላሽ እንደሚያገኝ ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here