ሚኒስትሮቹ የተገኙበት የሲዳማ ተወላጆች ስብሰባ በፖሊስ ተስተጓጎለ

0
808

አዲስ አበባ ለ5 ቀናት በኮማንድ ፖስት ስር ነበረች ተብሏል

በሳለፍነው ሳምንት እሁድ መስከረም 25/2012 በአዲስ አበባ ባህል ማዕከል በከተማዋ የሚገኙ የሲዳማ ዞን ተወላጆችን ለማወያየት የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ፣ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍፁም አሰፋ(ዶ/ር)፣ የሐዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ እንዲሁም የዞኑ አስተዳዳሪ የተገኙበት ስብሰባ ፈቃድ ሳታገኙ ተሰብስባችኋል በሚል ተበተነ።

ከአንድ ሺሕ በላይ ሰዎች ታድመውበታል የተባለው ይህ ጉባኤ፣ የሆረ ፊንፊኔ በዓል በተከበረበት ማግስት የተካሔደ ሲሆን ፖሊሶቹም ‹‹አዲስ አበባ ለአምስት ቀናት በኮማንድ ፖስት ስር ስለሆነች ማንኛውም ስብሰባ ፍቃድ ሳያገኝ መካሔድ አይችልም›› በሚል ስብሰባው ከተጀመረ በኋላ ወደ አዳራሹ መግባታቸውን የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደስታ ሊዳሞ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። የተሰበሰበውን ሰው ከአዳራሹ እንዲበተን ከተደረገ በኋላም የመጡት ፖሊሶች ከኀላፊዎቻቸው ጋር በስልክ ባደረጉት ልውውጥ ስብሰባው እንዲቀጥል በድጋሚ ፈቅደዋል።

‹‹የተከሰተው ቀላል አለመናበብ እንጂ ሌላ ነገር አይደለም። የተበተነው ተሰብሳቢም ከግቢው ብዙም ርቆ ሳይሔድ በድጋሚ ስብሰባው እንዲደረግ ስለተፈቀደ መልሰን ስብሰባውን አካሒደናል›› ሲሉ የፕላን ኮሚሽን ኮሚሽነሯ ፍፁም ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ደስታ በበኩላቸው አዳራሹን ለስብሰባ ከማስፈቀድ ባለፈ ለፖሊስ ስለ ስብሰባው አለማሳወቃቸውን ገልፀው፣ ‹‹ጥፋቱ የእኛ ነው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ቁጥሩ ቀላል የማይባል ፖሊስ ወደ አዳራሹ ገብቶ ነበር በሚል በስብሰባው ላይ ከታደሙ ሰዎች ለመጣው አስተያየትም ‹‹ወደ አዳራሽ የመጣው የፖሊስ ቁጥር ሳይሆን ዋናው ችግሩን የፈቱበት መንገድ ነው›› ሲሉ የዞን አስተዳዳሪው ተናግረዋል።

የስብሰባው ዋና አላማም በሲዳማ ዞን የሚነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ላይ ለመወያየት ያቀደ እንደነበር እና በተለይም የዞኑ ተወላጆች ዋነኛ ጥያቄ ነው ተብሎ በተነሳው የሕዝበ ውሳኔ ጉዳይ ላይ መሆኑን ደስታ ተናግረዋል።

‹‹የቤተሰብ ውይይት ተብሎ የሚወሰድ ውይይት በአዲስ አበባ የሚገኙ የዞናችን ተወላጆች በመጨው የሕዝበ ውሳኔ ላይ መሳተፍ ከፈለጉ ወደ ዞኑ በመምጣት መሳተፍ እንዲችሉ እና ያን ባያደርጉ እንኳን ባሉበት ሆነው ሒደቱን መከታተል እንደሚችሉ የተነጋጋርንበት ነው›› እንደ አስተዳዳሪው ገለፃ። ‹‹በተጨማሪም የዞናችን ተወላጅ የሆኑ ባለሃብቶች እንዲሁም በተለያየ የመንግሥት የሥራ ኀላፊነት ላይ ያሉ ግለሰቦች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች አንስተን የተወያየንበት እና በዞኑ ስለሚነሱ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ትኩረት ሰጥተን የተነጋገርበት መድረክ ነበር›› ብለዋል።

አከውለውም የክልሉ መንግሥት ለሕዝበ ውሳኔው ማስፈፀሚያ የሚውል 75 ሚሊዮን ብር ለምርጫ ቦርድ ገቢ ማድረጉን እና የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችም መገባደዳቸውን ተናግረዋል።

ፖሊሶቹ ስበሰባውን በመበተናቸው ይቅርታ ጠይቀው እንዲቀጥል ፈቅደው ለግማሽ ቀን የቆየውም ስብሰባ በሰላም መጠናቀቁን አዲስ ማለዳ በስብሰባው ተሳታፊ ከነበሩ ሰዎች የገኘችው መረጃ ይጠቁማል።

አዲስ ማለዳ በተለይ አዲስ አበባ ለአምስት ቀናት በኮማንድ ፖስት ስር ነበረች በሚለው መረጃ ላይ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ እና ወደ ፌደራል ፖሊስ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ስልክ በመደወል ጥያቄ አቅርባ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁለቱም በጉዳዩ ላይ መረጃ እንደሌላቸው የገለጹ ሲሆን የፌደራል ፖሊስ በበኩሉ ጉዳዪ በቀጥታ የሚመለከተው የአዲስ አበባ ፖሊስ ነው ሲል ገልጿል፡፡

ኮማንድ ፖስት ስለሚቋቋምባቸው ህጋዊ መሰረቶች ለአዲስ ማለዳ በሐምሌ 20 ቀን 2011 ዝርዝር ሞያዊ እይታቸውን ያካፈሉት የህግ ረዳት ፕሮፌሰር ማርሸት መሃመድ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅን ከኮማንድ ፖስት ጋር ማምታታት በተለያዩ ወገኖች አንደሚታይ እና ይህም ለዴሞክራሲያዊ መብቶች የራሱን አደጋ እንደሚጋርጥ ይናገራሉ፡፡

በተለይም የአንድ አካበቢ የፀጥታ መዋቅር በብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት ውሳኔ ወደ ኮማንድ ፖስቱ በሚወሰድበት ወቅት በግለሰብም ሆነ በቡድን መብቶች ላይ ስለሚጣሉ ገደቦች እና ስለተከለከሉ ተግባራት ሳይዘረዝር ማለፍ የተለመደ እየሆነ እንደመጣ ባለሞያው ያትታሉ፡፡

በአገሪቱ የኮማንድ ፖስት ቁጥጥር መተግበር የጀመረው ከ 2009 ጀምሮ ሲሆን ይህም በወቅቱ ታውጆ ከነበረው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ይህ ኮማንድ ፖስትም የአዋጁን አፈፃፀም ለመከታተል ታስቦ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ የነበረ ሲሆን በ2010 በታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ደግሞ በመከላከያ ሚኒስትሩ የተመራ ነበር፡፡

ባለፈው አንድ አመት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተነሱ ግጭቶች ወቅት የክልል መንግስታት በሚጠይቁት መሰረት የፀጥታው ምክር ቤት የተለያዩ ኮማንድ ፖስቶችን አቋቁሟል፡፡ እነዚህ ኮማንድ ፖስቶች ሲቋቋሙ እና ሲፈርሱ ጨምሮ ስለሚያከናውኗቸው ተግባራት ዝርዝር መረጃ የማይሰጡ ሲሆን እንደ አስቸኳይ ግዜ አዋጅም ዝርዝር ሪፖርት ባለማቅረባቸው ሲተቹ ቆይተዋል፡፡

በአዲስ አበባም ለአምስት ቀናት ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ነበር የሚለው መረጃ ለስራ ሃላፊዎቹ ይገለፅ እንጂ በመገናኛ ብዙሃንም ሆነ በፀጥታ መዋቅሩ ዘንድ የሚታወቅ አለመሆኑን አዲስ ማለዳ ያካሄደችው ዳሰሳ ያስረዳል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here