የፍቅር ጋርመንት ባለቤት የ15ሺሕ ተማሪዎችን ዩኒፎርም ባለማድረሳቸው በቁጥጥር ስር ዋሉ

0
668

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የደንብ ልብስ ለማሠራት ያወጣውን ጨረታ ካሸነፉት 18 ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የፍቅር ሌዘርና ጋርመንት ኢንዱስትሪ ሥራ አስኪያጅና ባለቤት፣ ከጥራት በታች የሆነ ጨርቅ ከውጪ አምጥተዋል በሚል የተፈጠረውን አለመግባባት ተከትሎ ከተማ አስተዳደሩ ውሉን በማቋረጥ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር ዋሉ።

‹‹ፍቅር ሌዘርና ጋርመንት ኢንዱስትሪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በጨረታው የቴክኒክ መስፈርት መሰረት ከተቀመጠው መመሪያ ውጪ ወደ ቻይና በመሔድ ካሽሚር የተባለ ጨርቅ ናሙና መላካቸው ሲታወቅ ከተማ አስተዳደሩ የመጀመሪያ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ቢጽፍላቸውም ማስተካከያ ባለማድረጋቸው ውሉን በማቋረጥ ገንዘቡን እንዲመልሱ ጠይቀናል›› ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤትና ካቢኔ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ዳዊት ምንዳዬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

‹‹ውላችን የነበረው ቲትረን 6000 በተባለ እና ሙሉ በሙሉ አገር ውስጥ በሚዘጋጅ ጨርቅ የደንብ ልብሱን እንዲሠሩ ከዲዛይነሮቹ የቀረበላቸውን መመሪያ ወደ ጎን በመተው ያነሰ ጥራት ያለውን ጨርቅ ለመጠቀም ሞክረዋል›› ብሏል።

የከተማ አስተዳደሩም ሥራ አስኪያጁን ለማግኘት ባለመቻሉ የማስጠንቀቂያ ማስታወቂያ ድርጅቱ ድረስ በመሔድ መለጠፉን የሚናገሩት ዳዊት፣ ከሥራው አንገብጋቢነት አንጻር ቶሎ ምላሽ ማግኘት ባለመቻላቸው ለፖሊስና ለዓቃቤ ሕግ ማሳወቃቸውን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ግለሰቡ መጥተው ለቅድሚያ ክፍያ የወሰዱትን 9 ሚሊዮን ብር ቢመልሱም ቅጣቱንና መሰል ጉዳዮችን አስመልክቶ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ኃላፊው አስታውቀዋል። ውሉን ያቋረጠው ከተማ አስተዳደሩ የደንብ ልብሱ ለሌሎቹ ተቋማት እንዲከፋፈል መደረጉንና ልብሶቹም አልቀው ለተማሪዎቹ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

በ2012 የትምህርት ዘመን ለመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች የተዘጋጀው የደንብ ልብስ እስከ ነሐሴ 25 ድረስ ተጠናቅቆ ለተማሪዎቹ እንደሚከፋፈል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቢያስታውቅም፣ ለተማሪዎቹ ሙሉ ለሙሉ ተከፋፍሎ ያለቀው መስከረም 28/2012 በመሆኑ በዘገዩት 15ሺሕ የደንብ ልብሶች ምክንያት ትምህርት ያልጀመሩ ተማሪዎች ሰኞ ጥቅምት 3/2012 እንደሚጀምሩ የከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ ፕሬስ ሴክሪታሪያት ፌቨን ተሾመ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የአዲስ አበበ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ የ2011 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ሐምሌ 25/ 2011 ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ለ2012 በጀት ዓመት 300 ሺሕ ተማሪዎችን በተማሪዎች ምገባ ከማካተት በተጨማሪም 7.2 ሚሊዮን ደብተርና የተማሪዎች ደንብ ልብስ በነፃ ለማቅረብ ዝግጅት መደረጉን ገልጸው ነበር።

ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ባገኘነው መረጃ መሠረት፣ የኹለተኛ ደረጃ የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ጨምሮ ሁሉም የመንግሥት ተማሪዎች የተማሪዎች ደንብ ልብስ በነፃ አግኝተዋል።

ከተለያየ የኑሮ ደረጃ የሚመጡ ተማሪዎችን በተመሳሳይ መልኩ ለማስተናገድ ሲባል ሁሉም ተማሪዎች በተማሪዎች ምገባ እንዲስተናገዱና ተመሳሳይ የደንብ ልብስ እንዲለብሱ የከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራና የተለያዩ ድርጅቶችም ዕርዳታ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here