በታሪክ ውስጥ ብቻ አንኑር፤ ከታሪክ እንማር፤ ታሪክ እንሥራ!

0
477

ታሪክ የትላንቱን ከዛሬ ለማነጻጸሪያነት፣ ለነገም መንደርደሪያ ሆኖ ወደ ፊት የታሻለ እንድንሠራና እንድናይ የሚያደርግ የኋላ ማስታወሻ ትዝታ ነው ማለት ይቻላል።
የአንድ አገር ታሪክ አገሪቱ እና ሕዝቦቿ ያለፉበትን መንገድ፣ ውጣውረድ፣ መጥፎ እና ጥሩ አጋጣሚዎችን ወደ ኋላ ሔዶ የሚያስታውስ ነው። የኢትዮጵያ የረጅም ዓመታት ታሪክ የትላንት ማንነታችንን ከነጉድፋችን ያሳያል፤ በበጎዎቹ እንከብራለን፤ በመጥፎዎቹ እንማራለን።

ታሪክ የኩራታችን ምንጭ፣ የማንነታችን ብያኔ ይሰጠናል። በትላንትና ውስጥ ምን እንመስል እንደነበር ያሳየናል። በእርግጥ ኢትዮጵያ የብዙ ዘመን ታሪክ ባለቤት እንደሆነች በታሪክ ድርሳናት ተከትቦ ይገኛል። ይሁንና ታሪካችን በሙሉ ተጽፏል ማለት አይደለም፤ ከምናውቀው የማናውቀው፣ ከተነገረው ያልተነገረው እንደሚበልጥ ይታወቃል።

የታሪክ ድርሳናትን ማን ጻፋቸው? ለምን ጻፏቸው? የሚሉት ሁሉ መፈተሸና መታየት አለበት። በመሆኑም የአንድንም አገር ምሉዕ ታሪክ ተጽፏል ለማለት አያስደፍርም፤ የኢትዮጵያም ታሪክ እንዲሁ ነው።

ታሪክ ከሚጻፍበት ዓላማና ዕይታ አንጻር በእቅድም ይሁን ያለ እቅድ፣ ታስቦበትም ይሁን ሳይታሰብበት ታሪክ ሲጻፍ አንዳንዱን የታሪክ ክፍል በማጉላት፣ ሌላውን ደግሞ በማሳነስ ወይም በመግደፍ ስለሚጻፍ ምሉዕ በኩለሄ የሆነ ታሪክ ይኖራል ማለት አይቻልም።

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገራት ከተጻፈው ይልቅ በቃል የሚነገረው የሚበዛበት፣ የተጻፈውም ቢሆን የላይኛውን የኅብረተሰብ ክፍል በተለይ ነገሥታቱን፣ መኳንንቱንና ሌሎች የከፍተኛው መደብ አካላት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን እነዚሁ ከፍተኛ የኅብረተሰብ መደብ የራሱን ታሪክ እንደሚያጽፍ ይታወቃል።

በተለይ የነገሥታት ታሪኮች የተመዘገቡባቸው ዜና መዋዕል ለዚህ አብነቶች ሆነው መጠቀስ ይችላሉ። እነዚህ መዛግብቶች ሙሉ በሙሉ እውነትን አይከትቡም ባይባልም ለነገሥታቱ ያደሉ፣ የሚያሞግሱ እንዲሆኑ ተደርገው የተጻፉ መሆናቸው የመስኩ ምሁራን በጥናቶቻቸው አመላክተዋል።

ሌላው በጽሑፍ ተመዝግበው ከሚገኙ ታሪካችን ባልተናነሰ ወይም የሚበልጠው ከትውልድ ትውልድ በአፍአዊ ትረካ የሚተላለፈው ይበዛል። አፍአዊ ትርክቶች ደግሞ ስለነበሩና ስለተከናወኑት ብቻ ሳይሆን ስላልነበሩና ስላልተደረጉ ጉዳዮች ትኩረት የሚያደርጉም አሉ። ፈጠራ የሚታከልባቸው፣ ግነት የሚጫናቸው አለበለዚያም በዛው ልክ አሳንሰው የሚመለከቱ ሊሆኑ ይችላሉ።

በእርግጥ አፍአዊ ታሪክና በጽሑፍ የተከተቡት ሁሌም አይመሳሰሉም ማለት እንዳልሆነ ግን ልብ ሊባል ይገባል። እንዲሁም በጽሑፍ የተከተቡትን ያህል እንኳን ባይሆን በአፈታሪክ ውስጥ እውነት አይኖርም ማለትም አይደለም።

ይህ በመሆኑም በጽሑፍ የተላለፉትም ሆኑ አፈታሪኮች በሕዝቦች ላይ የደረሰን በደል፣ ጭቆና ሊያጎሉም፣ ሊያሳንሱም ይችላሉ። በመሆኑም ኹለቱም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ መጠቀም ያስፈልጋቸዋል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።

ሌላው ገዢ መደብ የነበሩ ክፍሎች ሆነ ብለው እንደ አንድ የመግዣ መሣሪያ ታሪክን ሲጠቀሙበት ኖረዋል። ያለፈውን ታሪክ ለማነጻጸሪያነትና ለመማሪያነት ከመጠቀም ይልቅ የገዢና ተገዢ፣ የበዳይና ተበዳይ፣ የጠባብና ትምክህተኛ፣ ነፍጠኛ እና በነፍጥ ሲገዛ የነበረ በሚሉና በሌሎች ተንኳሽ፣ ለቂም በቀል የሚያነሳሱ፣ ተጠራጣሪ የሚያደርጉ ትርክቶችን በመጠቀም ሥልጣናቸውን አደላድለው ለማስቀጠል የሚጠቀሙበት ዘዴ መሆኑን ለመረዳት የሩቅ ዘመን ታሪክ መጥቀስ አያስፈልግም።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ በደማቅ ሁኔታ የተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የኦሮሚያ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሽመልስ አብዲሳ “የአሮሞ ሕዝብ እዚህ ነበር የተሰበረው፤ እዚህ ነበር መዋረድ የጀመረው፤ እዚህ ነበር ቅስሙ የተሰበረው። …የዛን ዘመን ታጋዮች የነፍጠኛ ስርዓት እዚህ ነበር የሰበራቸው። ዛሬ የሰበረንን ሰብረን፣ ከመሠረቱ ነቅለን ኦሮሞ የተዋረደበት ቦታ ተከብሮ ይገኛል” (ትርጉም በአብርሃም ዓለሙ (ዶ/ር)) የሚል ንግግር ማሰማታቸው የሰሞኑ መነጋገሪያ ርዕስ ከመሆኑ ባሻገር ብዙዎችን አስቆጥቷል፤ ከግራ ከቀኝ የመልስ ምት ቃላት አሰንዝሯል፤ በግንባሩ ውስጥ ባሉ ድርጅቶች ውስጥም ጥርጣሬን ፈጥሯል። በሳምንቱ አጋማሽ ላይም ስህተት መሠራቱን በገደምዳሜው የሚጠቁምና ለዛም የሚያመቻምች የሚመስል መግለጫ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ እንዲሰጥ ተገድዷል።

በመጀመሪያ ኢሬቻ ባሕላዊ ዳራ ያለው ሕዝባዊ በዓል መሆኑ ለፖለቲካ ትርፍ መጠቀሚያነት ማዋል ተገቢነት ያለው አይደለም ስትል አዲስ ማለዳ ታምናለች። እንደ ሕዝባዊ በዓልነቱ አባ ገዳዎች ወይንም ሽማግሌዎች መልዕክታቸውን በማስተላለፍ ክዋኔው ፍጹም ስርዓቱንና ወጉን በጠበቀ ሁኔታ ብቻ መከበር ነበረበት።

ሌላው እና እጅግ በጣም አስገራሚው በኦዴፓ እና አዴፓ ፊታውራሪነት እየተመራና እየተካሔደ ያለውን አገራዊ ለውጥ እንዴት ከፍተኛ የሆነ ሥልጣን ያለው ብሎም ለውጡን ካመጡት መካከል የሚገኝ ቁንጮ ባለሥልጣን ራሱን በገመድ ለመጥለፍ ይሔዳል የሚለው አስገራሚው ጉዳይ ነው።

የርዕሰ መስተዳደሩ ንግግር በሞቅታ የተፈጠረ የአፍ ወለምታ ከሆነ ሳይውሉ ሳያድሩ ራሳቸው ማረሚያ በሰጡ ነበር፤ ይሁንና አልሆነም። የተረኛነት ስሜት መፈጠሩ ግን አልቀረም። ይህ ድርጊት ግን ታሪክን እውነተኛ ይሁን አይሁን ዝርዝር ውስጥ ሳይገባ፣ እንዴት መጠቀም እንደሚችል እንደ ማሳያ ተደርጎ ሊታይ ይችላል።

በእርግጥ ሽመልስ በዚህ ረገድ ብቸኛው ናቸው ማለት አይቻልም። ይሁንና ሕዝብ ፊት ሲቀርብ የሚደረግ ንግግር ምን ያህል ጥንቃቄ መደረግ እንደሚገባው ጥሩ ማስተማሪ ሆኖ አልፏል።

ሌላው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማጠንጠኛ በአብዛኛው ታሪክ መሆኑ ይገርማል። ታሪክ አልፏል፣ አጠንጥኖ መመለስ ወይም ደግሞ እንዳልተፈጠረ አድርጎ ማሰብ አይቻልም፤ አይገባምም።

በእርግጥ በየትኛውም አገር ታሪክ ውስጥ የሚያኮራ እንዳለ ሁሉ የሚያሳፍርም ገጽታ ይኖረዋል። ይሁንና በጎውም ሆነ በመጥፎው ታሪክ ሆኖ አልፏል።
በመሆኑም ታሪክ ለመማሪያነት ማወቁ ጥሩ ነው። ታሪክ የኋላን አካሔድ አሁን ካለው ኹነት ጋር ለማነጻጸሪያነት መጠቀሙ ጥሩ ነው፤ በጎውን ለማስቀጠል ከመጥፎው ለመማር። ይሁንና በታሪክ ውስጥ ብቻ መኖር ፋይዳው ባዶ ኩራት ወይም ቁጭት ብቻ ይሆኗል።

በመሆኑም በታሪክ ውስጥ ብቻ አንኑር። በጎውን እናጉላ፤ ከመጥፎው እንማር። ይህንንም ለማድረግ ታሪክን እንወቅ። ከሁሉም በላይ ግን የቀደሙት ታሪክ ሠርተው ያቆይዋትን አገር ለተከታይ ትውልድ ከነ ክብሯ ማስረከቡ ትውልዳዊ ኀላፊነት ነው።

ለአብነት ለመጥቀስ የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለጥቁሮች ምሳሌ የሆነ ኩራታችን ነው። የሰው ዘር እኩልነት የተረጋገጠበት አንጸባራቂ ድል መሆኑን ማስታወስ ግድ ይላል። ስለሆነም አድዋ በጎ ታሪክ በመሆኑ ድሉን ማጉላት ይገባናል። አንድ ተጨማሪ አብነት ለመጥቀስ ሐሙስ፣ መስከረም 29 የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) መሪዎች በተገኙበት በከፍተኛ ድምቀት በይፋ የተመርቆ የተከፈተው የ“አንድነት ፓርክ” በበጎው ይሁን በመጥፎው የኢትዮጵያ አገረ መንግሥታት የሔዱበትን ከአንድ ክፍለ ዘመን በላይ የዘለቀውን ታሪካችንን ማሳያ መስታወት ሊሆነን ይችላል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሊደገሙ የማይገባቸውን በጎ ያልሆኑ የታሪካችን ጠባሳዎች ደግሞ እንማርባቸው ዘንድ ለሕዝብ ክፍት መደረጉ ታሪክ የመሥራት አንዱ አካል ተደርጎ ይወሰዳል። በታሪክ ውስጥ ብቻ ሳንኖር ታሪክን ለመማሪያነት የምናቀርብበት አንደኛው መንገድ ይኼው ስለሆነ።

ባለፈ ታሪክ ለመኩራትም ሆነ ለመማር ግን ታሪካችንን ጠንቅቀን ማወቅ ይጠበቅብናል። ማንነታችንን ከሚበይኑት መካከል ብዙ ነገሮች መካከል ታሪክ ጉልሁን ቦታ መያዙ የማይቀር በመሆኑ።

በርግጥ በጎ ያልሆነ የታሪካችንን አካል ቁስሉ እንዲያጠግግ፣ በደሉም እንዲሽር መፍትሔው ከእርቀ ሰላም ኮሚሽን እንጠብቃለን። በእርግጥ ኮሚሽኑ አሁን ላይ ምን እየሠራ እንደሆነ የሚታወቅ ነገር የለም።

በመጨረሻም አዲስ ማለዳ በታሪክ ውስጥ ብቻ አንኑር፣ ታሪካችንን እንወቅ፣ ከምንም በላይ ግን ታሪክ እንስራ ስትል ጥሪዋን ታቀርባለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 49 ጥቅምት 1 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here