ሴትነት በወንዶች ጭንቅላት

0
634

ከቤት ውጭ ባለ ሥራ የምንውል ሰዎች ከቤተሰብና ከጓደኛሞች ጋር ከምናሳልፈው ጊዜ መስሪያ ቤት የምናልፈው ጊዜ ይበልጣል። ከሥራ ባልደረባዎቻችን ጋር ብዙ ጊዜን ስለምናሳልፍም ጓደኝነት መፈጠሩ አይቀርም። በቢሮ ወሬ ብዙ ነገሮች ይነሳሉ። ለምሳሌ ስለአለቃ ባህሪ፣ ከቢሮ ውጪ ስላለ ኑሮ፣ ስለ ፖለቲካ እና ሌሎችም ጉዳዮች እያነሱ መጣል የተለመደ ነው፡፡ በሰራተኞች መሃል ያለ ወሬ የሥራ ውሎ ቶሎ እንዲያልፍ ማድረጉ ባይካድም በወሬ መካከል አንዳንዴ ያልተጠበቁ ነገሮችንም ልንሰማ እንችላለን።
ለምሳሌ በቅርቡ የተሾሙት ሚኒስትሮች ጉዳይ በብዙዎች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኗል። መቼም አዲስ ከተሾሙት ሚኒስትሮች መካከል ግማሾቹ ሴቶች ናቸው ብዬ አላሰለቻችሁም። እኔና ጓደኞቼ በሥራ ላይ ሆነን ስለ ሚኒስቴሮቹና ስለ አገሪቷ ሁኔታ ስናወራ ብዙ ጊዜ ከአንዳንድ ወንድ ባልደረቦቻችን የሚያጋጥመን ነገር መቼም ለጉድ ነው፡፡
ከሴት ተሿሚዎች መካከል የመከላከያ ሚኒስትሯን አይሻ መሃመድ ያክል አጨቃጫቂ ሆኖ ያገኘሁት የለም። አንዱ ይነሳና ‹‹አገሩን ተቆጣጠራቹት አይደል›› ይላል፤ ከዚያም ይሳቃል። ወዲያውኑ ግን ሁሏም ሴት የምታውቀው ወሬ ይጀመራል። አንዱ ‹‹ግን የመከላከያ ሚኒስትርን ሴት ማድረግ አይከብድም፤ ምን ታሰቦ ነው›› የሚል ጥያቄ አንስቶ ክርክሩ ጦፈ፡፡ አስገራሚው ግን ጥያቄ ውስጥ የገባው የሚንሰትሯ ልምድ ወይም ለቦታው ያላት ብቃት አይደለም። በሴትነቷ ብቻ ለቦታው አትበቃም ነው ነገሩ። ነገሩን ከመከፋትም በላይ ያደረገብን ግን ያውቃሉ ከምንላቸው መካከልም ተመሳሳይ አቋም መንፀባረቁ ነው፡፡ እኔም ሆንኩ ጓደኞቼም የተረዳነው ጉዳዩ በአመክንዮ የተደገፈ ክርክር ሳይሆን ድርቅና መሆኑን ነው፡፡
በእርግጥ ‹‹ሴት እንዴት እዚህ ቦታ ላይ›› የሚለው የአመለካከት ችግር በሚኒስትር ደረጃ በተሾሙት ብቻ የተወሰነ አለመሆኑ ግልጽ ነው። ማንኛዋም ሴት በተለምዶ የወንዶች ነው የሚባለውን ቦታ ደፍራ ስትይዝ የሚደርስባት ትችትና ሽርደዳ የሚገርም ነው። በሥራዋ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ መድረስ የፈለገች ሴት ግን የግድ ይህንን መሰናክል ማለፍ አለባት። ሴት በሥራዋ የቱንም ያህል ብታድግ በብዙ መልኩ ትተቻለች፡፡ በትምህርትና አቅሟ የተሰጣትን ቦታ ‹‹አይ እከሌ ቢሆን ኖሮ ይሻል ነበር›› በሚል ለሴት እንደማይገባ ለመሞገት የሚቸኩለው በዝቷል፡፡
በዚህ በለውጥ ዘመን ግን ይህን ዓይነት ቆሞ ቀር አስተሳሰብ አያሳዝንም? ሰው ሴት ስለሆነች ብቻ ብቃቷ ሳይታይና ልምዷና ችሎታዋ ሳይገመገም ለሴት የሚሆን ቦታ ብቻ ነው የሚሆናት ማለት አለብን? ለሚቀጥለው ትውልድ ምን እያስተማርን ነው? ሴት ልጅ ምንም አይነት ስራና ምንም አይነት ሹመት ብታገኝ ለዛ ቦታ የሚሆን ችሎታ እስካላት ድረስ ሰው ተቀብለዋት ምንም ዓይነት ፆታዊ ሃሜት ሳይደርስባት ከወንድ ታንሳለች ሳትባል መሥራት መቻል አለባት። ምነው? 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ያለን መስሎኝ ነበረ!

መና አስራት
menna.a@ethiopianbusinessreview.net

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here