በ2014 በጀት ዓመት 3 ሺሕ በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ መሞታቸው ተነገረ

0
1014

በኢትዮጵያ በአንድ ዓመት 3 ሺሕ 971 ሰዎች በትራፊክ አደጋ መሞታቸውን የትራንስፖርትና የሎጂስቲክ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

የትራንስፖርትና የሎጂስቲክ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋም የሆነው የመንገድ ደኅንነትና መድኅን ፈንድ አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ እንደገለፀው፣ ከሐምሌ 1/2013 እስከ ሰኔ 30/2014 ድረስ በደረሰው የትራፊክ አደጋ 3 ሺሕ 971 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል ብሏል።

አገልግሎቱ አክሎም ከሞቱት ሰዎች ባለፈ 5 ሺሕ 586 ዜጎች ከባድ የአካል ጉዳት፣ 4 ሺሕ 739 የሚሆኑ ሰዎች ላይ ደግሞ ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው እና በአጠቃላይ ከ14 ሺሕ 200 በላይ በሚሆኑ ዜጎች ላይ የትራፊክ አደጋ እንደደረሰ ጠቁመዋል።

በሀብት ደረጃ በበጀት ዓመቱ በተከሰተው የትራፊክ አደጋ 13.5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱም ተነግሯል።

ባለፈው አንድ ዓመት በኢትዮጵያ በተከሰቱት የትራፊክ አደጋዎች ከሞቱት ውስጥ፣ በአዲስ አበባ ከተማ 438፣ በድሬዳዋ ከተማ 28፣ በአማራ ክልል 860፣ በኦሮሚያ 1568፣ በአፋር 32፣ በሶማሊያ 266፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ 27፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች 549፣ በጋምቤላ 12፣ በሐረር 30 እና በሲዳማ ክልል 151 ናቸው።

በትግራይ ክልል በአገሪቱ ባለው ወቅታ ሁኔታ ምክንያት የትራፊክ አደጋ መረጃ እንዳልተዘጋጀ እና ከዚያ ውጭ ያሉ ክልሎችን መሠረት አድርጎ የተጠናቀረ ሪፖርት መሆኑም ተወስቷል።

በ 2013 በጀት ዓመት ከ4 ሺሕ በላይ ሰዎች ለሞት እንዲሁም ከ20 ሺሕ በላይ ሰዎች ደግሞ ለከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት ተዳርገው እንደነበር ተነግሯል። ይህም በ2014 በጀት ዓመት በሞት እና በቀላል የአካል ጉዳት 4 ነጥብ 6 በመቶ ቀንሷል ነው የተባለው።

ከላይ ለተጠቀሱት የሞት፣ ከባድ እና ቀላል እንዲሁም የንብረት ጉዳት መድረስ ምክንያት በዋነኝነት የአሽከርካሪዎች ሥነ ምግባር ጉድለት፣ ቸልተኝነትና ብቃት ማነስ፤ የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ጉድለት፣ ወቅቱን የጠበቀ የቦሎ እድሳት አለማድረግ፣ የመንገድ ግንባታ ችግርና የእግረኞች የመንገድ አጠቃቀም ችግር ናቸው ተብሏል።

በ2014 በጀት ዓመት የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የተቻለው ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን ለይቶ የማሻሻያ ሥራ በመሥራት፣ የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ የመግጠም፣ የቁጥጥር እና ሌሎች ተጨማሪ ሥራዎች እየተሠሩ በመሆናቸው አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here