ዳሰሳ ዘ ማለዳ ማክሰኞ ጥቅምት 4/2012

0
655

1- የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ህዝበ ውሳኔው የሚከናወንበት ቀን በአንድ ሳምንት ተራዝሞ ህዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑን ምርጫ ቦርድ አስታውቋል። ቦርዱ ባወጣው መግለጫው፥ የደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ምክር ቤት ህዝበ ውሳኔው የሚካሄድባቸው ቀበሌዎችን ዝርዝር ለመስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲያቀርብ ተወስኖ የነበረ ቢሆንም እንዲሁም በተከታይ ከቦርዱ ማሳሰቢያ ቢላክም ህዝበውሳኔው የሚካሄድባቸው ቀበሌዎች ዝርዝር እስካሁን ድረስ አልቀረበም። (አዲስ  ማለዳ)

………………………………………………………

2- በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ(ዶ/ር) የተፃፈው “መደመር” መፅሃፍ ቅዳሜ ጥቅምት 8/2012 ይመረቃል።የመፅሃፉ ምረቃትም በተለያዩ 20 በሚሆኑ የአገሪቱ ክፍሎች በዋናነትም በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ጅማ፣ ባህር ዳር፣ ሀዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ ጋምቤላ፣ አሶሳ፣ ጅግጅጋ፣ ሰመራ እና ሀረር  በአንድ ቀን በሁሉም ቦታ ይመረቃል። በሶስት ቋንቋዎች የተጻፈዉ መፅሓፍ ዋጋው 300 ብር ሲሆን ገቢውም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ትምህርት ቤቶችን ለማስገንባት እንደሚዉል ተገልጿል። (ፋና ብሮድካስቲንግ)

………………………………………………………

3- የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የሸጎሌ የአውቶብስ ዴፖን ዛሬ ጥቅምት 4/2012 መርቀው በይፋ ስራ አስጀምረዋል። በሸጎሌ የአውቶቢስ ዴፖ ማዕከል አውቶብሶች በቴክኖሎጂ የተደገፈ የጋራዥ አገልግሎት ፣ የእጥበትና የነዳጅ አቅርቦትን በአንድ ማዕከል ማግኘት እንደሚችሉ ታዉቋል። ዴፖ 52 ሺ ካ.ሜ ላይ ያረፈ ሲሆን ከ250- 300 አውቶቢሶችን የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ (አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………

4–የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የአገሪቱን የጥራት መሠረተ-ልማት አገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የሚረዳ የአምስት ዓመት ፕሮጀክት በመንደፍ በትግበራ ላይ መሆኑን ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታውቋል። የዚህ ፕሮጀክት ዋና አላማ በአገሪቱ አሁን በሥራ ላይ ያሉትን አምራቾች የጥራት ማረጋገጫ አገልግሎት እንዲጠቀሙ ለማድረግና የዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሣደግ የሚያስችል የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት እንደሆነ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስታዉቋል።(አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………

5-አክዋ የተሰኘ የሳዑዲ ዓረቢያ ኩባንያ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተባበር የፀሐይ ሃይል ማመንጫዎችን በ300 ሚሊየን ዶላር ሊገነባ ነው። የኩባንያው ፕሬዚዳንት ፓዲ ፓድማናታን እና የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ፕሮጀክቱን ተግባራዊ ለማድረግ ስምምነት የፈፀሙ ሲሆን የጸሃይ ሃይል ማመንጫዎቹ የሚገነቡት በአፋርና በሶማሌ ክልሎች መሆኑ ታውቋል።ፕሮጀክቶቹ እያንዳንዳቸው 125 በአጠቃላይ 250 ሜጋ ዋት የፀሐይ ሃይል እንደሚያመነጩም ታውቋል። (አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………

6- አንድ ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ይፈጃል ተብሎ የሚገመተው የታላቁ ቤተ-መንግስት የመኪና ማቆሚያ ግንባታ ጥቅምት4/2012 የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል።በ10ሽሕ ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፍ እና 1 ሽሕ መኪኖችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችለው ይህ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ቦታ፤ አራት ቤዝመንቶች ያሉት ሲሆን ግንባታው በአንድ ዓመት ከስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።(አዲስ ማለዳ)

………………………………………………………

7- የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የማመንጨት አቅሙ ሊቀንስ ነው ተብሎ እየተነገረ ያለው መረጃ ትክክል አለመሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ። የግድቡ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ እንደገለፁት ግድቡ በ16 ተርባይኖች በዓመት በአማካይ 15 ሺህ 670 ጊጋዋት በሰዓት ኃይል የማመንጨት ዕቅድ ተይዞ ነበር ግንባታው የተጀመረው፡፡ በዚህም 16 የነበሩ ተርባይኖች ወደ 13 በማድረግ በዓመት የሚጠበቀውን 15 ሺህ 670 ጊጋ ዋት ሰዓት የማመንጨት አቅም ሳይለወጥ ቀድሞ በተያዘው ዕቅድ መሰረት ኃይል ማመንጨት እንደሚቻል ሳይንሳዊ መደምደሚያ ላይ ተደርሶ እየተሠራ መሆኑንም ኢንጅነር ክፍሌ ገልፀዋል። (ኢቢሲ)

………………………………………………………

8- በጦርነት ተጎጂ የሆኑ ህፃናትን መታደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በሚመክረው ዉይይት ባለፉት 20 አመታት በጦርነት ምክንያት 5 ሚሊየን ህፃናት በሞቱባት አፍሪካ የህፃናት መብት እንዲከበርና ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ ተጠይቋል። በዉይይት መድረኩ ከኢትዮጵያ፣ ማሊ፣ደቡብሱዳን፣ናይጄሪያና ኮንጎ የተገኙ ህፃናት ተሳትፈዋል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የሴቭ ዘ ችልድረን ዳይሬክተር ያ ቬል አገራት የህፃናትን መብት ለመጠበቅ የገቧቸዉን አለምአቀፍ ስምምነቶች ሊያከብሩ ይገባል ብለዋል።(ዋልታ)

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here