በበጀት ዓመቱ 400 ተሽከርካሪዎች ተገዝተዋል ተብሏል
በ2014 በጀት ዓመት በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች በሽያጭ እንዲወገዱ ውሳኔ ከተሰጠባቸው ካገለገሉ ተሽከርካሪዎችና ሌሎች ቁሳቁሶች የተገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 26.7 በመቶ መቀነሱን የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ገለጸ።
የ2014 በጀት ዓመት ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ቅናሽ ያሳየው በሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆኑን ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ በግልጽ ያሳያል።
በመጀመሪያ የተጠቀሰው መንስኤም ለሦስት ጊዜያት ያህል ለጨረታ የቀረቡ ንብረቶች ባለመጫረታቸው መሆኑ ተነስቷል። እንደ ገለጻው ከሆነ፤ በአገልግሎቱ በኩል ለማስወገድ ለ3ኛ ጊዜ ለጨረታ ከቀረቡት 137 ሎት ንብረቶች 123 ሎት በተጫራቾች ዋጋ ሳይቀርብባቸው ቀርቶ ሳይወገዱ ቀርተዋል።
በአደገኛ ቆሻሻ ዝርዝር ውስጥ በሚካተቱ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች መስፈርቱን የሚያሟላ ተጫራች አለመቅረቡ በኹለተኛ ደረጃ የተነሳ መንስኤ ነው። በመሆኑም 78 ሎት የአገልግሎት ጊዜያቸው ያበቃና በባህሪያቸው በአደገኛ ቆሻሻ ዝርዝር ውስጥ በሚካተቱ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ሽያጭ መስፈርቱን የሚያሟላ ተጫራች ባለመቅረቡና ንብረቶቹ ሳይወገዱ መቅረታቸው ተጨማሪ ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል።
ለገቢው መቀነስ ሦስተኛው ምክንያት በአገልግሎቱ በኩል የሚወገዱ ንብረቶች የዋጋ ግምት የገንዘብ ጣሪያ ከነበረበት ከብር 100 ሺሕ ወደ ብር 500 ሺሕ በላይ ከፍ በመደረጉ በመሥሪያ ቤቶች የሚቀርበው የንብረት ይወገድልን ጥያቄ በመቀነሱ መሆኑ ተብራርቷል።
በአጠቃላይ በዓመቱ ከተሽከርካሪዎችና ከተለያዩ ንብረቶች የግል ጨረታ የሽያጭ ክንውን 45 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ ይኸውም ባለፈው ዓመት ከተገኘ ገቢ ጋር ሲነጻጸር 26.7 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል ተብሏል።
በሌላ በኩል የመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን በ2014 በጀት ዓመት በርካታ ግዥዎችን የፈጸመ ሲሆን፤ በዚህም 400 ተሽከርካሪዎችን ለተቋማት መግዛቱን ጠቅሷል።
ከተቋሙ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው ከሆነ፤ በ2014 በጀት ዓመት ለመንግሥት ተቋማት 400 የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ተገዝተው ለተጠቃሚ ተቋማቱ ተከፋፍለዋል ነው የተባለው።
በመሆኑም ለገቢዎች ሚኒስቴር ተደራቢ (ደብል) ጋቢና ያላቸው 40 ፒክአፕ ተሽከርካሪዎች በውል ዋጋው ከ54 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ በሚሆን ብር ግዥ ተፈጽሞ ተሽከርካሪዎቹ ለተጠቃሚው መሥሪያ ቤት ገቢ መደረጋቸው ተጠቁሟል።
ከፒክአፕ ተሽከርካሪዎቹ በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ ተገዝተው ለተቋማት የተበረከቱት 360 የሚሆኑ ሞተር ሳይክሎች መሆናቸውን ከተቋሙ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
እንደ መረጃው ከሆነ፤ ከተገዙት 360 ሞተር ሳይክሎች መካከል 300 የሚሆኑት ለኢትዮጵያ ጤና መድን ኤጀንሲ እንዲሁም ቀሪ 60ዎቹ ለገቢዎች ሚኒስቴር በድምሩ 360 ሞተር ሳይክል የግዥ ሂደቱ ተጠናቆ አሸናፊ ለሆነው ተጫራች 57 ሚሊዮን 240 ሺሕ በላይ ብር አሸናፊነት ደብዳቤ ተሰጥቷል ነው የተባለው።
እንዲሁም ለቦረና ዩኒቨርስቲ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ዕቃዎች ግዥ የተማሪዎች መገልገያ ፈርኒቸር፤ የተፈጥሮ ሳይንስ (ለባዮሎጂ፤ ለኬምስትሪ እና ለፊዚክስ) የላቦራቶሪ መሣሪያዎች ግዥ እና ለማኅበራዊ ሳይንስ መጽሐፍት ግዥ በድምሩ ከ21 አቅራቢ ድርጅቶች ጋር 251 ሚሊዮን ብር በላይ የአሸናፊነት ደብዳቤ ተሰጥቷል። በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ በ5.2 ቢሊየን ብር ግዥ ተፈጽሟል ተብሏል።
ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014


