በማጭበርበር ተሰማርተው የተገኙ 73 ሠራተኞች ተጠያቂ ተደርገዋል ተባለ

0
1124

የ32 ሠራተኞች ተጠያቂነት ገና በሂደት ላይ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ በማጭበርብር ተሰማርተው የተገኙ 73 ሠራተኞቹ ተጠያቂ ማድረጉን ለአዲስ ማለዳ ገለጸ።

ሠራተኞቹ ተጠያቂ የሆኑት የተለያዩ ሕግን የሚጥሱ ድርጊቶችን ሲያከናውኑ ተገኝተው መሆኑን ማወቅ የተቻለው ተቋሙ ለአዲስ ማለዳ በላከው የ2014 ዓመታዊ ሪፖርት ነው።

ከተቋሙ የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው፣ የአመራሮችንና ፈጻሚዎችን ተጠያቂ ለማድረግ በታቀደው መሠረት 105 ሠራተኞች ተለይተው 73 የሚሆኑት ሠራተኞች ተጠያቂ መሆናቸውን ነው።

ሰዎቹ ተጠያቂ የተደረጉት የተለያዩ ሥራዎችን አግባብነት በሌለው መልኩ ሲያከናውኑ መሆኑን ከተቋሙ የተላከው መረጃ የሚጠቅስ ሲሆን፤ ይኸውም እጅ ከፍንጅ ብር ሲቀባበሉ በመገኘታቸው፤ ሐሰተኛ ማስረጃ አስመስለው የሚሠሩና ማስረጃውን ማሠራት ለሚሹ አካላት ሠርተው በመስጠታቸው ነው ተብሏል።

እንዲሁም ተገልጋይን በማጉላላት ከዲሲፕሊን ወይም ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ተግባር በማከናወናቸውም ተጠያቂ ስለመሆናቸው በዓመታዊ ሪፖርቱ በግልጽ ተቀምጦ ይገኛል።

አመራሮችንና ፈጻሚዎችን በሚሠሩት ሥራ ትክክል መሆንና አለመሆንን ለመመዘን በታቀደው መሠረት እንዲለዩ ከተደረጉት 105 ሠራተኞች መካከል 73 ተጠያቂ የተደረጉ ሲሆን፤ 32 የሚሆኑት ግን ተጠያቂነታቸው ገና በሂደት ላይ ስለመሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል።

በመሆኑም፤ በሠራተኞች ላይ የሌብነት አስተሳሰብና ተግባር መኖሩ እንደተደረሰበትና እርምጃ እንደተወሰደ እንዲሁም በመወሰድ ሂደት ላይ ያሉም ስለመኖራቸውም ነው ማወቅ የተቻለው።

እጅ ከፍንጅ ብር ሲቀበሉ ተይዘዋል የተባሉት አካላት ስንት እንደሆኑና ምን ያህል ብር እንደተቀባበሉ ለማጣራት የተደረገው ሙከራ ግን፤  የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ መላክ መኮንን ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ማካተት አልተቻለም።

በሌላ በኩል፣ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ አቅዶ ያላከናወናቸው በርካታ ሥራዎች መኖራቸውም ተመላክቷል። ከእነዚህም መካከል የወሳኝ ኩነትን ሲስተም መቶ በመቶ ተረክቦ ለማስተዳደር፤ መቶ በመቶ ወረዳዎችን ወደ ማእከላዊ ዳታ ሴንተር ማገናኘት ቢታቀድም ሳይከናወን መቅረቱ ተመላክቷል።

እንዲሁም ምርጥ ተሞክሮዎችን የመለየት፤ የመቀመር እና የማስፋት፤ የሰው ኃይል 70 በመቶ ለማሟላት እንዲሁም ሲስተም የሌላቸው ወረዳዎች ሲስተም እንዲኖራቸው ማድረግ ከ86 ነጥብ 2 በመቶ ወደ መቶ በመቶ ከፍ ለማድርግ ታቅዶ ግን ሳይሳካ እንደቀረ ነው ማወቅ የተቻለው።

በአዲስ አበባ ከተማ ስር በሚገኙ 11 ክፍለ ከተሞች የዲጂታል መታወቂያ እንዲሰጥ መደረጉ የተጠቀሰ ሲሆን፤ 3 ሺሕ 860 የሚሆኑት የዲጂታል መታወቂያዎች ግን በ11 ወር ውስጥ ብቻ የጥራት ችግር እንደተገኘባቸው ተመላክቷል። በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ የታዩ በርካታ ችግሮች ስለመኖራቸውም ተቋሙ ጠቅሷል።

በተቋሙ  የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት እና የሪፖርትና ሌሎች መረጃዎች በጥራትና በወቅቱ መለዋወጥ ውስንነት መፈጠር፤ የሕዝብ አደረጃጀቶችን ወደ ተግባር አለማስገባት ከክፍተቶቹ መካከል ተጠቃሽ ናቸው ተብሏል።

እንዲሁም፤ የግብዓት ማነቆዎችን መፍታት አለመቻል፤ ቅንጅታዊ አሠራር በሚፈለገው ደረጃ አለመሠራቱ ተያያዥ ክፍተቶች ሆነው ተመዝግበዋል። አጠቃላይ ከአገራዊ የኩነቶች ምዝገባ ስትራቴጂ ዕቅድ እና ከዓለም ዐቀፍ የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦች አንጻር የወሳኝ ኩነት የምዝገባ አፈጻጸም መሆን ከነበረበት አንጻር ዝቅተኛ ስለመሆኑ መነገሩ አይዘነጋም።


ቅጽ 4 ቁጥር 197 ነሐሴ 7 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here