ሐሙስ ነሐሴ 12 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በአርትስ ቲቪ የ”አበስኩ ገበርኩ” ፕሮግራም አዘጋጅ እንዳልካቸው ዘነበ “ሀሰተኛ መረጃ እንዲሁም የጥላቻ ንግግር በማህበራዊ ሚዲያ አሰራጭተሃል” የሚል ክስ ቀርቦበት በጋሞ ዞን በብርብር ከተማ በእስር ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
አርትስ ቲቪ ጉዳዩን ከያዙት ፖሊስ ባደረገው ማጣራት፤ እንዳልክ የከተማዋን ከንቲባ ሥም የሚያጠፋን ጽሁፍ “ላይክ” እና “ሼር” አድርገሃል በሚል ክስ እንደቀረበበት ገልጿል፡፡ ይህንን ክስ ግን እንዳልካቸው እና ቤተሰቦቹ እንደማይቀበሉትም በመግለጽ፤ ይልቁንስ ጉዳዩ የግል ቁርሾ መወጣጫ ነው ማለታቸውን አስታውቋል፡፡
በእንዳልክ ላይ በቀረበበት ክስ ወንድሞቹ ቴዎድሮስ ዘነበ እና ተከተል ዘነበ በአንድ መዝገብ እንደተከሰሱ የእንዳልካቸው እናት ተናግረዋል፡፡

እንዳልካቸው በፌስቡክ ሀሰተኛ መረጃ እንዲሁም ጥላቻ ንግግር በማሰራጨት በሚል ከተከሰሰ ወንድሞቹ ለምን አብረው ታሰሩ፤ ማዘዣስ ወጣባቸው በሚል አርትስ ቲቪ ለፖሊስ ጥያቄ ቢያቀርብም ፖሊስ ግን ጉዳዩን በዝርዝር መናገር እንደማይፈልግ ተናግሯል፡፡
የእንዳልካቸው እናት ስለዚህ ጉዳይ ሲናገሩ “የእንዳልክ ወንድሞች አብረው የታሰሩት በፌስ ቡክ ጽሁፍ “ላይክ” አድርጋችኋል በሚል” እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
አርትስ ቲቪ በጉዳዩ ላይ ባደረገው ማጣራት የብርብር ከተማ ፍ/ቤት በእንዳልክ እና ወንድሞቹ ላይ በቀረበው ክስ ምንም አይነት ዝርዝር ጉዳይ እንዳልደረሰው፣ ለፖሊስም በፍጥነት የክስ ዝርዝር እንዲያቀርብ እንዳዘዘ ለማወቅ ተችሏል፡፡

እንዳልክ እና ወንድሞቹ አሁን ያሉበት ሁኔታ ምን እንደሆነ ጥያቄ ለእናቱ የቀረበላቸው ሲሆን፤ የዋስ መብቱ ከዞን ተከብሮለት በዋስ እንዲወጣ የዞን ደብዳቤ እየተጠባበቁ እንደሆነ ገልጸው፤ ሌላ ተጨማሪ ነገር ከሌለ እንዳልክ በዋስ ሊወጣ እንደሚችል ተናግረዋል፡፡



