የራያ ሕዝብ ታሪክ፣ የመብት እና የአስተዳደር ጥያቄ (ክፍል ሁለት)

0
1091

በክፍል አንድ መጣጥፋቸው ብሩክ ሲሳይ ስለ ራያ ሕዝብ አሰፋፈር፣ ሌሎች ሕዝቦች ጋር ያደረገውን ውሕደት እና የወረሴህ ስርወ መንግሥት አመሠራረት አስነብበውን ነበር። በዚህ ክፍል የራያ ሕዝብ ከዐጤ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት እስከ ዐፄ ኃይለሥላሴ ድረስ ያለፈበትን የታሪክ ጉዞ የወያኔ አመፅ የሚባለውን የገበሬዎች እምቢታ ለማክሸፍ አስተዳደሩ በሁለት እስከተከፈለበት 1935 ድረስ ያለውን ታሪክ መልሰው ያስቃኙናል።

 

 

(ክፍል ሁለት)

በዳግማዊ ዐጤ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት፣ ራያ በኋላ ዐጤ ተክለ ጊዮርጊስ የተባሉት የእነ ዋግሹም ጎበዜ እንዲሁም የመጨረሻው የወረሴህ ራስ ቢትወደድ ዳግማዊ ዓሊ መደበቂያ እና የሽፍትነት ቦታቸው ነበር። ዐጤ ዮሐንስ በሙስሊሙ ላይ በተለይም በራያና አዘቦ ማኅበረሰብ ላይ ሲዘምቱ በአዋጅ በነጋሪት በማስነገር ነበር። ለወታደሮቻቸውም ‹ሒዱ የራያ እና የአዘቦ ሰዎችን ግደሉ፤ ከእነሱ መካከል አንዱን ገድሎ ጀብዱን ያላሳየ የእኔ ወታደር ሊሆን አይችልም› በማለት ዘምተው ከፍተኛ እልቂት አስከትለዋል[ባይሩ ተፍላ]። በዚህ ዘመቻ ከሞት የተረፉት እንደ ሼኽ ጀማሉዲን አንይ ወይም መሐመድ ሮብሶ የመሳሰሉት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መንዙመኛ ወደ አፋር፣ የጁ እና ወረባቦ ቆላማ ቦታዎች ተሰደው እስከ እልፈት ሕይወታቸው በስደት ኑሯቸውን ገፍተዋል።
በዚያው ዘመን በፈረስ ሥማቸው አባ መጀን እየተባሉ የሚጠሩ መቲ ሻኪር የሚባሉ የየጁ ባላባት ስለ ራያ ዞብል እና አካባቢዋ አጠቃላይ ሁኔታ ደብረ ታቦር ድረስ በመሔድ በግንባር ቀርበው ንጉሡን ለማስረዳት እና ለማሳመን በመቻላቸው ንጉሡም ከጦር መኮንኖቻቸው እና ከመኳንቶቻቸው ጋር ተመካክረው በመዝመት ከላስታ ምሥራቅ ክፍል ጀምሮ እስከ ዞብል እና አካባቢው ድረስ የነበረውን አስፈሪ ጥቅጥቅ የደን ጫካ በማስመንጠር እና መንገድ በመጥረግ ንጉሥ ተራራ በተባለው ቦታ የአስተዳደር ማዕከላቸውን እንደ መሠረቱ ታሪክ ያስረዳል።በመቀጠልም ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች የትግራይ ሰዎችን በማንሳት የራያ መሬት ላይ በገፍ አስፍሯል። ለጦር ሠራዊታቸውን እና ለመኳንቶቻቸውን ከራማ እስከ ጎሊና (ደቡባዊ የዞብል ወሰን) ድረስ ያለውን ግዛት አከፋፍለው በመደልደል የአካባቢውን አስተዳደር በቢትወደዳቸው በራስ ገብረኪዳን አማካኝነት አቋቋሙ። ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ በኢማም አሕመድ ዘመን የተቃጠሉትን ቤተክርስትያናት እና የተደበቁትን ታቦታት እንደገና በጎንደር አምሳል 44 አድባራት ሥም እንዲታነፁ አድርገዋል። በተለይ በአደባባይ ኢየሱስ እና በራማ መንበረ መንግሥት ገብርኤል ላይ የጎላ ድርሻ በማበርከት ወይም ቅድሚያ በመስጠት ሌሎችንም አድባራት በመኳንንቱ አማካኝነት እንዲታነፁ ማስደረጋቸውን ትውፊት ያስረዳል።
ዐጤ ዮሐንስ ከአላ ውኃ እስከ ኤቦ ድረስ ባለው አገር ገዥ የነበሩትን ወረሴህ ደጅ አዝማች ዘገዬ ብሩን ከሹመታቸው አስነስተው በትግራዩ ራስ ገብረ መድህን ተክተዋል[ሞላ ትኩዬ]። ዐጤ ዮሐንስ መተማ ላይ ሲሞቱ፣ የራስ ገብረ መድህን የራያ ገዥነትም አብቅቷል። ከራስ ገብረ መድህን በፊትም ሆነ በኋላ የራያ፣ በከፊል የላስታ እና የየጁ ጌታ የነበሩት ደጅ አዝማች ዘገዬ ብሩ ነበሩ፤ ግዛታቸውም እስከ ኤቦ ወንዝ ነበር፤ ኤቦ ወንዝ መሆኒን አልፈን የምናገኘው ነው።። ደጅ አዝማች ዘገዬ በዘመነ መሳፍንት በወረሴሆች ዘመነ መንግሥት ወቅት የዚያኔዋን ኢትዮጵያን በራስ ቢትወደድ ማዕረግ በበላይነት ለ5 ዓመታት ያስተዳደረው የራስ ቢትወደድ ዓሊጋዝ ጓንጉል የልጅ ልጅ ናቸው። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በዐፄ ዮሐንስ ተነሳሽነት የራያ ዞብልን መቅናት እና ዝና በመስማት ከምሥራቅ ላስታ ከምሥራቃዊ ግዳን ከዲኖ፣ ከመቅደላ፣ ከአንጎት፣ ከጥቂት አንጎት፣ ከሲንቃ አምባ፣ ከገደባ፣ ከሸወይ ወዘተ በርካታ ሰዎች ከታቦቸው ጋር አብረው ሠፍረዋል። እነዚህ ሰዎች በራያ ዞብል የመሠረቷቸውን መንደሮች በመጡበት አካባቢ ነው የሰየሟቸው። መቅደላ፣ ታሎ ማርያም፣ ዲኖ፣ አንጎት፣ ጥቂት አንጎት፣ ሸኾይ፣ ተሁላ ወዘተ አሁን ድረስ በራያም ሆነ በምሥራቃዊ ላስታ ግዳን የሚገኙ ተመሳሳይ የቦታ ሥሞች ናቸው።
ይህ ምሥራቃዊ የግዳን ክፍል የዘወልድ እና የክፍሎ የትውልድ ሐረግ እና ቤተሰብ መነሻ ነው። የዘወልድ እና የክፍሎ ትውልድ አሁን ላለው ለራያ ማኅበረሰብ መስተጋብር እና ዘመን የተሻገረ አስደናቂ የማኅበረሰባዊ ግጭት አወጋገድ፣ የጋብቻ አፈፃፀም፣ የእርቅ እና የሠላም መፍትሔ ለሆነው “የዘወለድ የእርቅ፣ የሽምግልና እና የዳኝነት ስርዓት” መፈጠር ምክንያት ነው። በራያ የሚታወቀውን የዘወልድ እርቅ እና ዳኝነት ምክንያት በመሆኑ በራያ ምድር አሁን ድረስ የተጣላ የሚታረቀው፣ ደም የሚደርቀው፣ የጋብቻ ሁኔታ የሚወሰነው በዘወልድ ባሕላዊ የማኅበረሰቡ የማይታይ እሴት አማካኝነት ነው። ከኦሮሞ ሕዝብ መስፋፋት እና ሠፈራ ጋር በተያያዘ በከፍተኛ ደረጃ የኦሮሞው ማኅበረሰብ የሠፈረባቸው እንደ ቦረን፣ ጎዶ፣ ቀበና፣ ቀለንቲ፣ አርጆ፣ ጋላ ጎራ፣ ወረ ቡርቃ፣ ዲቃሎ፣ አረቋቲ፣ ቦኩ፣ ገረዳቦ፣ ወዘተ የሚባሉ የኦሮምኛ ቋንቋ ሥያሜወች ያላቸው ቦታዎች በራያ ዞብል ይገኛሉ።
ከዐፄዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ማብቃት በኋላ የራያ አካባቢ አስተዳደር መልኩን እየቀየረ የመጣ ሲሆን፤ ብዙውን ጊዜም በየጁ፣ በላስታ፣ በዋግ እና በራሱ በራያ ባላባቶች ሥር ከብዙ ተከፋፍሎ ሲተዳደር ኖሯል። በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት እስከ ዋጃ ሸምበቆ ውኃ ድረስ ያለው የራያ ክፍል በየጁው ራስ ወሌ ብጡል ሥር የነበረ ሲሆን ወደ ሰሜን ያለው ዋጃ፣ ወፍላ ዳዩና አላማጣ ደግሞ በዋግ ሹሞች ሲተዳደር ጨርጨር እና አዘቦ ደግሞ በራያው ተወላጅ ደጅ አዝማች ተድላ ዋህዱ አማካኝነት ይተዳደር ነበር። ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ሞተው አቤቶ ልጅ እያሱ ሥልጣን ሲይዙ ራስ ወሌ ብጡል በቁም እስር ሲቀመጡ የራያ ግዛት በሞላ የወሎ እና የትግራይ ንጉሥ ተብለው ለነገሡት በንጉሥ ሚካኤል ዓሊ ሥር ሆኗል። ላስታ፣ ራያ፣ የጁ እና ዋግ አራቱም አውራጃወች ከሁለት ተከፍለው በንጉሥ ሚካኤል ልጅ ራስ ገብረ ሕይወት እና በልጅ ልጃቸው ራስ ኃይለ ማርያም አማካኝነት ይተዳደሩ ነበር።
የሸዋ መኳንንት አዲስ አበባ ላይ መክሮ በሴራ ልጅ እያሱን በአዋጅ ከሻሩት በኋላ በተደረገው የሰገሌው ጦርነት ንጉሥ ሚካኤል ተሸንፈው ሲማረኩ ራስ ወሌ ብጡል የተቀሙትን የቀድሞ የየጁ እና የራያ እንዲሁም የላስታ ግዛታቸው ተመለሰላቸው። ከዚያም በመቀጠል የደቡቡ ሆርማት ወንዝ ግዛት በራስ ወሌ ብጡል፣ ቆቦ ከተማን ጨምሮ የመካከለኛው የራያ ክፍል በላስታው በልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ ሥር፣ የሰሜኑ የራያ ክፍል ዳዩ፣ አላማጣ እና ገበቴ ደግሞ በዋግሹም ከበደ ተፈሪ ሥር ደጅ አዝማች ታፈረ ተሰማ እንዲተዳደር ተደርጓል። የራያ እና አዘቦ ጨርጨር አካባቢ ደግሞ በጥላሁን ግዛው እና በልዕልት ሣራ ግዛው አባት በደጅ አዝማች ግዛው አበራ ሥር ይተዳደር ነበር።
ከዚያም በኋላ የራያ ወጣቶች እስከ ወረባቦ ድረስ በቆላው ክፍል በመሔድ ሲራራ ነጋዴዎችን እየዘረፉ ስላስቸገሩ፣ ራስ ጉግሣ ወሌም የራያን ሕዝብ እንዲቀጣ ቢታዘዝም መጀመሪያ እያቅማማ ዝም ካለ በኋላ በኋላ ግን ዘምቶ ምንም ሳያደርግ ወዳጅነት መስርቶ በመመለሱ የሰሜኑ ደጅ አዝማች አያሌው ብሩ አገር አቆራርጠው ላስታን መሸጋገሪያ አድርገው አቡሃይ ጋሪያ ላይ ሠፈር ካደረጉ በኋላ ራያ ወርደው የሸፈቱትን እምቢ ባይ ወጣቶች ደመሰሱ። ከዚያ በኋላ መላው ራያ በአንድ ላይ በአንድነት ፋሽስት እስኪገባ ድረስ በማዕከላዊ መንግሥት ዕዝ ሥር እንዲሆን ተደረገ። በፋሽስት የአገዛዝ ዘመን ከጉራወርቄ እና ከቃሊም ውጭ መላው የራያ ክፍል እንዲሁም የላስታ ክፍል የነበረው አንጎት እና ዋግን ጨምሮ ከትግራይ ላይ አንድ ላይ በራስ ሥዩም መንገሻ እየተዳደረ በኤርትራው የጣሊያን የቅኝ ግዛት ክፍል ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ ይተዳደር ነበር። በጣልያን የአምስት ዓመት የወረራ ዘመን ፋሽስት የራያ ሰዎች እና ሽምቅ ተዋጊዎች ጥቃት ስለበረታበት በቆቦ እና በአላማጣ ከተማወች በግምብ ምሽግ ቢሠሩም የራያ የደፈጣ ተዋጊዎችን ዘረፋ እና ጥቃት ሊከላከሉ ጨርሶ አልቻሉም ነበር።
የወያኔ አመፅ እየተባለ በሚታወቀው የራያ ገበሬዎች አመፅ ምክንያት በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ራያ በመላ በወታደራዊ ሕግ እና ደንብ በጀኔራል አበበ ዳምጠው አማካኝነት እንዲተዳደር ተደርጓል። የመጀመሪያው የወያኔ አመፅ መንስኤ በ1934 አምስት የመንግሥት ወታደሮች እና የእንግሊዝ መኮንኖች በቆቦ ከተማ ስለተገደሉ በአየር ተደብድባለች። የወያኔ አመፅ ምክንያት ገዥው መደብ ሠላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በሚል ምክንያት ሕዝቡ ትጥቅ እንዲፈታ መታወጁ፣ መሬት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መሆኑ፣ መሬት ከገበሬዎች እየተነጠቀ ለገዥው መደብ አገልጋዮች ይሰጥ ስለነበር የመሬት ባለቤት ካልሆን ግብር አንከፍልም እንዲሁም ማዕከላዊ መንግሥት በሚሾማቸው ተሾሚወች አንገዛም የሚል ነበር።የራያ ገበሬዎች በዐፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ላይ ያካሒዱት የነበረው አመፅ ለማብረድና ለማስቆም ሲባል በ1935 ራያ ከሁለት ተከፍሎ እንዲተዳደር ታወጀ።
(ይቀጥላል)

ብሩክ ሲሣይ በአማካሪነት፣ ተመራማሪነት እና በኋላፊነት በማገልገል የሚገኙና በግላቸው የታሪክ ጥናትና ምርምር ሥራዎች ተነስተው የተለያዩ ታሪካዊ ጦማሮችን ያዘጋጃሉ። በኢሜይል አድራሻቸው brooh77@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here