“የታሪክ ማወራረድ ውስጥ መግባቱ አይጠቅመንም።”

0
502

‹ኢምፖወር አፍሪካ› መንግስታዊ ያልሆነ በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የምርምር፣ ሥልጠናና ማማከር አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው። “እኛና ብሔራዊ መግባባት” በሚል ርዕስ ኅዳር 10፣2011 በዋቢ ሸበሌ ሆቴል አዘጋጅቶ በነበረው ሕዝባዊ ውይይት ላይ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበርና የመድረክ ከፍተኛ ኃላፊ መረራ ጉዲና (ዶ/ር) የመነሻ ጽሁፍ አቅርበዋል፡፡  ሕዝባዊ ውይይቱን የተከታተለው ታምራት አስታጥቄ በብሔራዊ መግባባት ዙሪያ፣ ስለኦፌኮ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ፣ ከማንነት ጋር ተያይዘው ስለሚነሱ ጥያቄችና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች አነጋግሯቿል፡፡

መረራ ጉዲና (ዶ/ር)
የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበር

አዲስ ማለዳ፡ ብሔራዊ መግባባት ምን ማለት ነው?
መረራ ጉዲና፡ ብሄራዊ መግባባት የሚባለው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ማኅበረሰቦች ከማኅበረሰቦቸ ጋር፣ በተለይ የፖለቲካ ኃይሎች መስማማት አቅቷቸው አገሪቱ ሠላምና መረጋጋት ስታጣ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋታል። በተለይ አስተዳደሩም ሆነ ምጣኔ ሀብቱ ሁሉን አቀፍ ባልሆነበት ጊዜ፣ ሁሉም ‹‹ይሄ መንግስት አይወክለኝም›፣ ይሄ ፓርቲ አይወክለኝም›› ዓይነት ፍጭትና ግጭት ውስጥ ሲገባ ብሔራዊ መግባባት አገሪቷና ሕዝቦቿን አቅጣጫ ለማስያዝ፣ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የተሻለ ስምምነት እንዲፈጠር ለማድረግ በአገሪቱ ዕጣ ፈንታ [እና] መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ በተለይ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ስምምነት እንዲደረስ የሚያደረገው ብሔራዊ መግባባት ነው።
የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑ መሠረታዊ የምንላቸው ጉዳዮች ምን ምን ናቸው?
ኢትዮጵያ ወዴት ትሂድ፣ አንድ አገረ አለን የለንም የሚለው ላይ መስማማት ያስፈልጋል። እየታገልን ያለነው የተለያዩ አገሮችን ለመፍጠር ነው ወይስ የተሸለ አንድ አገርን ለመገንባት ነው? የአገሪቱ አንድነት ላይ አቅጣጫ ማስያዝ የግድ ያስፈልጋል።
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት መገንባት ላይ መስማማት አለብን። የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይሁንታን ያገኘው ፓረቲ በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን የሚወጣበት፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሕዝብ ይሁንታን ያላገኘው የሚወርድበትና ትግሉን የሕዝብ ይሁንታ እስኪያገኝ የሚቀጥልበት ሥርዓት ማለት ነው።
ከዚህ ውጪ ያሉ ጉዳዮችን የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ፖሊሲያቸው ቢያደርጉት ጥሩ ነው። ለምሳሌ የቋንቋ ጥያቄን፣ ምን ዓይነት ፌደራሊዝም እንከተል የሚለውን፣ የግለሰብ መብቶችንና የማኅበረሰቦች መብቶችን እና የመሬት ጥያቄን የመሳሰሉትን ማለቴ ነው። የኢትዮጵያ ችግር ኢሕአዴግ 27 ዓመታት የከፋፍለህ ግዛ ሴራ እንጂ ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም አላመጣም። የመድረክ አቋም ዴሞክራሲያዊ ፌደራሊዝም እስከተገነባ ድረስ የግለሰብ መብትና የቡድን መብቶች አንድ ላይ መስተናገድ ይችላሉ የሚል ነው።
በብሔራዊ ምግባባት እነዚህን ለብዙ ዘመናት ተከማችተው የመጡ ችግሮች ሁሉ በአንዴ እንፍታ ማለት አይቻልም። ችግሮች መፈታት ያለባቸው ደረጃ በደረጃ መሆን ይገባቸዋል። አለበለዚያ ችግሩ ተቃዋሚውን በመከፋፈልና አገሪቱን ሌላ ዙር ቀውስ ውስጥ ይከታታል።
እንዴት አብረን እንኑር፣ ምን ዓይነት የመንግስት ቅርጽ ይኑረን፣ ሁላችንንም በእኩልንት የሚያስተዳድር ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዴት እንፍጠር በሚሉት ዙሪያ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እየተነጋገሩና እየተደራደሩ መፍታት ላይ መድረስ ይሻላል።
የሁሉም ችግሮች ቁልፍ ያለው ፖለቲካችችን ማስተካከለሉ ላይ ነው። በነፃና ፍትሃዊ ምርጫ በተመረጠ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሥር ሁሉም የኢትዮጵየ ሕዝቦች ፍላጎተቻቸውን፣ ምኞታቸውን፣ ህልሞቻቸውን የሚገልፁበት የሚደራደሩበት ሁኔታ ሲፈጠር ወደ ብሔራዊ መግባበት እንሄዳለን።
የብሔራዊ መግባባት ተሳታፊዎች እነማን ናቸው?
ልሂቃኖች ወይም የተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎች፣ የኅብረተሰብ ክፍሎች እና አገር የሚመራውን ይጨምራል።
በቅርቡ መንግሥት ዕርቀ ሠላም ኮሚሽን ለማቋቋም በእንቅስቃሴ ላይ እንደሆነ እየተሰማ ነው፡፡ ከዚህ አንጸር የኮሚሽኑ መቋቋም ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ምን ሚና ሊጫወት ይችላል?
መንግሥት የሚያቋቁመው ኮሚሽን ቄሶችን፣ ሼኮችን፣ አባ ገዳዎችንና ምሁራንን የሚያስገባበት ይመስለኛል። በሃቅ እስከሆነ ድረስ እነዚህም ሰዎች ተነጋግረን፣ የመቻቻል ፖለቲካ ፈጥረን እንዴት እንኖራለን የሚለውን ብዙ መግፋት ይችላሉ የሚል ሐሳብ አለኝ። ዝም ብለው መንግሥት ያለውን ተቀበሉ የሚለውዓይነት ውስጥ ከገቡ ግን ብዙም አይፈይዱም። አሁን ባለንበት ሁኔታ የተሸለ ድርድር መካሄድ የሚቻል ይመስለኛል።
በየጊዜው የሚወሰዱት እርምጃዎች መንግሥት ለብቻው በራሱ መንገድ እየወሰደ ይገኛል። እዚህ ላይ ያለዎት አስተያየት ምንድን ነው?
እኛን በተመለከተ ከአራት ወር በፊት ለመንግሥት የድርድር ነጥቦች አስገብተናል። ካካተትናቸው ነጥቦች መካከል ምርጫ ቦርድና ነፃና ፍትሃዊ ምርጫን፣ የፀረ ሽብረተኝነት ሕጉን ፣ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ሕጉን፣ የመገናኛ ብዙኃን ሕጉን፣ የብሔራዊ አንድነት መንግሥትንና በዋናነት ደግሞ ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተ ይገኙበታል። መንግሥት በራሱ መንገድ እየሄደበት ነው። ለምን ሄደበት ብለን ያን ያክል ተቃውሞ አናሰማም።
ስለዚህ መንግሥት እየወሰዳቸው ባሉት እርምጃዎች ተስማማታችኋል ማለት ነው?
አፍችንን ሞልተን ተስማምተናል ማለቱ ቢያስቸግረንም አሁምን ቢሆን የዛን ጊዜ ያቀረብናቸው ነጥቦች እስካሁን ድረስ የነበሩውን ጣጣ በተወሰነ ደረጀ ይቀርፉ ነበር። ምሳሌ መጥቀስ ቢያስፈልገ መፈናቀልን በተመለከተ።
መድረክ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲቋቋም ለረጅም ጊዜ ሲወተውት እንደነበረ ይታወቃል፡፡ አሁንም ከዚሁ አቋማችሁ ጋር ናችሁ?
የብሔራዊ አንድነት መንግሥት በምንለው አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ከሥልጣን ይውረድ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቦታውን ይዘው፣ መንግሥትም ራሱን እያያሻሻለ ሥልጣን ላይ ይቆያል፤ ነገር ግን የዚህ መንግሥት መሠረት እንዲሰፋ እንፈልጋለን። ይህም በዋናነት ከቅልበሳ ነፃ ያወጣል ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ የኔ መንግሥት ነው እንዲሁም ሁሉም ኃይሎች የኛ ነው ብለው የሚሳተፉበት መንግሥት ዓይነት እንዲፈጠር ያስችላል።
ሰሞኑን መንግሥት የቀድሞ የሜቴክና የብሔራዊ ደኅንነት የሥራ ኃላፊዎችን በተደራጀ ሌብነትና ሰብዓዊ መብት ጥሰት ጠርጠሮ የእስር እርምጃን ከመወሰዱ ጋር በተያያዘ ምን ይላሉ?
በኔ አስተያየት መንገድ ይዟል፤ ሥጋቴ አሁንም ቢሆን ትናንሽ አሳዎች ላይ ብቻ እንዳይቀር ነው። ሥርዓቱን እንደ ሥርዓት የፈጠሩ፣ ያንቀሰሳቀሱ፣ መዋቅር የዘረጉ ብዙ ሰዎች አሉ። ተጠያቂነት ካለ እንዚህን ትናንሽ አሳዎች ብቻ ለቅመህ የምትወጣው ነገር አይደለም ውሎ አድሮ ምን እንደሚሆን አላውቅም። አሁን ያለው መንገዱ ጥሩ ነው ከማለት ውጪ የተሳካ ነው፣ የኢትዮጵያውያንን ችግር ይቀርፋል የሚለው ላይ ግን ያስጨነቀናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የሽግግር መንግሥት እንደማያስፈልግ ‹‹እኔ አሻግራችኋለሁ›› በማለት ግልጽ አድርገዋል
ዐቢይ አይችልም ወይም አይገባውም ሳይሆን የኢትዮጵያን ችግር ላለፉት 50 ዓመታት ያየን የፖለቲካ ኃይሎች በተቻለ መጠን አገሪቱን አቅጣጫ ለመስያዝ፣ ሕዝቡንም ለመምከር፣ የፖለቲካ ልሂቃን የሚባሉትንም ወደ ስምምነት ለማምጣት የተሻለ ይሆን ነበር ለማለት ነው።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር የፖለቲካ ልሒቃኑ ነው ሲባል በብዛት ይሰማል፡፡ እዚህ ላይ እርሶ ምን ይላሉ?
የፖለቲካ ልሂቃን የችግሩ ብቻ ሳይሆን የመፍትሔውም አካል ናቸው። የችግር አካል መሆናቸውን እየቀነሱ የመፍትሔው አካል የሆኑበትን እያሰፉ ቢሄዱ ጥሩ ነው። የማኅበረሰቡን ጥያቄ የሚያነሱት እነሱ ናቸው፣ ሕዝብን አደራጅተው የመምራት ዕድል የሚገጥማቸው እነሱ ናቸው።
ልሂቃኑ የራሳቸውን ህልሞች ይዘው ነው የሚጓዙት፤ እነዚህ ህልሞች ደግሞ የሚጋጩ ናቸው። ስለዚህ የሚጋጩ ህልሞችን ይዞ መፍትሔ ለማምጣት በጣም ያስቸግራል። በተለያየ ደረጃና በቀጥታም በተዘዋዋሪም እጃቸው አለበት። ተደራጅተው ጥያቄ የሚየስገተጋቡ፣ ለአደባባይ የሚያቀርቡ እነሱው ናቸው። ስለዚህ ችግር የመፍጠር አካልም ናቸው።
ሌላው የኢትየጵያ ትልቁ ተግዳሮት ተደርጎ በበርካቶች በተደጋጋሚ ሲነገር የሚሰማው የዘውግ ብሔርተኝነት ነው፡፡ ይስማማሉ?
እኔ እንደሚመስለኝ አንደኛው ብሔራዊ መግባባት የሚያስፈልገው ጉዳይ ይሄ ነው። በአብሮ መኖር ላይ፣ በመቻቻል ላይ፣ አብሮ መሥራት መሆን አለበት፡፡ [ምክንያቱም] ብሔረሰቦች የማይተማመኑባት ኢትዮጵያ ተፈጠራለች። ይሄንን እንዴት መቀልበስ እንችላለን በሚል በሀቅ መሥራት ያስፈልጋል። ችግሩ ግን ልሂቃን የሚባለው በፈለገው መንገድ የሚጋጩ ህልሞችን ይዞ መኳተኑ ሊጎዳን ይችላል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ሀቀኛ የማንነት ጥያቄ አለ ብለው ያምናሉ? ካለስ መገለጫው ምንድን ነው?
ሁለት የተለያዩ የማነነት ጥያቄዎች አሉ። አንዱ የበላይነት በመሻት ሲገፋ የነበረ አሁንም ሲገፋ ይታያል። ሌላው ደግሞ ትላንትም ዛሬም ተጨቁኛለሁ ብሎ የሚገፋ አለ። ለሁሉም ተከባብሮ መኖር ይሻላል። የታሪከ ማወራረድ ውስጥ መግባቱ ለሁላችንም ምንም አይጠቅመንም። የዛሬና የነገ ኑሯችንን ለማሻሻል የመቻቻል ፖለቲካ እንዴት እንፍጠር ብሎ ወደ ሀቀኛ ድርድር መግባት ያስፈልገናል።
የማንነት ጥያቄ በተደጋጋሚ መነሳቱ ለአገር ደኅነት ሥጋት ፈጥሯል የሚለው ሐሳብ ላይ ምን ይላሉ?
ሥጋቶቹን የምትቀንሰው የሥጋቶቹን ምንጮች በሥነ ሥርዓት ስታውቅ ነው። ለእኔ ዋነኛው የሥጋት ምንጭ ‹‹እኔ የበላይነት ከሌለኝ ኢትዮጵያ ትጥፋ›› የሚለው ሲሆን ትላንትም አላዋጣም፤ ዛሬም አላዋጣም፤ ነገም አያዋጣም።በዚሁ ተቃራኒም በሌላ በኩል ደግሞ ተጨቁኜ ስለነበር በሚል ካልተገነጠልኩ የሚል አለ። ይህ እንግዲህ ጨቋኞቹን እንኳን በቅጡ ሳይረዱ ማለት ነው። ለማንኛውም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ተከባብረው፣ ተቻችለው፣ ተነጋግረው፣ ተደራድረው አብሮ መኖር ይችላሉ። ልሒቃኑም ዕውቀትና ችሎታ ካላቸው እዚህ ላይ መሥራት አለባቸው። እንዴት አብረን እንኑር፣ እንዴት የመቻቻል ፖለቲካ እንፍጠር የሚለው ነው ዋና ቁምነገር መሆን የሚገበው።
የማንነት ጥያቄ በራሱ መቆም ይችላል ወይስ ሌሎች መገለጫዎች አሉት?
የማንነት ጥያቄ ብዙ ጣጣዎች አሉት በውስጡም ብዙ ነገሮች አሉበት። ከታሪክ፣ ከምጣኔ ሀብት፣ ከእኩል ተጠቃሚነት እጦት፣ ከባህልና ሌሎች ጉዳዮች ጋር ይያያዛል።
ይህ የማንነት ጥያቄ ታዲያ ማቆሚያው የት ላይ ነው?
የማንነት ጥያቄ መቆሚያው ብሔራዊ መግባባት ነው። እናት ኢትዮጵያ የማሰባሰብ፣ የተሻለች የመሆን ዕድል ከተፈጠረ ‹‹ኢትዮጵያ ካልተበታተነች›› የሚለው እየቀዘቀዘ ይሔዳል። ዋናው ነገር በተቻለ መጠን፣ ዕኩል ተጠቃሚነቱ ካለ፣ ሌላው የመከፋትና የመገፋት ስሜት ካልተሰማው አብሮ የመኖሩ ጉዳይ ችግር አይኖረውም። ይሄ የማንነት ጥያቄ መንስኤ ነው። በግልጽ ቋንቋ ለማስቀመጥ የኢትዮያዊነት የምስክር ወረቀት ሰጪና ከልካይ እኔ ነኝ ብለው ራሳቸውን የሾሙት ሰዎች ወይም ደግሞ ኢትዮጵያ በምንም መንገድ መዋቀር አለባት የሚለውን የግድ እኔ መወሰን አለብኝ የሚሉት፤በሌላ በኩል ሲጨቁኑ፣ ሲገፉ፣ ሲዘርፉ፣ ሲያዘርፉ የነበሩት የኢትዮጵያ መንግሥትና መሪዎችመሆናቸው እየታወቀ ‹‹የግድ እኔ ካልተገነጠልኩ ኢትዮጵያ ሠላም ማግኘት የለባትም›› ብሎ የሚገፋ ኃይል አለ። እነዚህ ሁለቱ ያስቸግራሉ፤ ከሁለቱም መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ወሳኙ ጉዳይ ኃይሎቹን እንዴት ሚዛን ማስጠበቅ እንችላለን የሚለው ነው።
በተደጋጋሚ ከሚነሱት የማንነት ጥያቄዎች አንጻር ክልሎች የራሳቸውን አጀንዳ ለማስፈጸም እየተጠቀሙበት ነው የሚባለው ጉዳይ እንዴት ያዩታል? ለአብነትም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በትግራይና አማራ ክልሎች መካከል የተፈጠረው እሰጣ ገባ ይጠቀሳል፡፡
በነገራችን ላይ በራያ ጉዳይ ላይ ኦሮሞም ቀስ ብሎ መግባቱ አይቀርም። ወደ ጥያቄህ ስሄድ የማነነት ጥያቄ ራሱን ችሎም ሆነ የክልሎችን አጀንዳ በማስፈፀም ሊውል ይችላል።
ችግሩ ግን ኢሕአዴግ እንደፓርቲ 27 ዓመት የቆየበት መንገድ አለ። ያንን እንደገና የመለወጥ ሙከራ ያለ ይመስላል። ቢያንስ የማስተካከል ሙከራዎች አሉ። ማስተካከሉ ላይ ግን ምናልባት እጎዳለሁ የሚል ቡድን ይኖራል። ድሮም የበላይነት የነበረው እንዴት የበላይነት አጣለሁ ብሎ የሚገፋ ኃይል ይኖራል። ድሮ ተገዢ የነበረው ደግሞ እስከመቼ የበታች ሆኜን እኖራለሁ ብሏል። ስለዚህ ሁለቱም ወደ ውጥረት ይመልሱናል።
ከማንነት ጋር ለሚነሱ ጥያቄዎች በሕገ መንግስቱ መፍትሄ ማግኘት ይችላሉ ብለው ያመናሉ?
አሁን ባለው መንገድ ለጊዜው ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ሕዝብን ማረጋጋት ነው። የግድ መሻሻል ካስፈለገም ቀስ ብሎ ሕገ መንግስቱንም ማሻሻል ይችላል።
ኦፌኮ ምን ያህል የኦሮሚያ ወረዳዎች ላይ በሥራ ላይ ያሉ ቢሮዎች አሉት? ምን ያክልስ አባላት አላችሁ?
በየጊዜው ምዝገባ ስለሚካሄድ አሁን ያሉትን አባባት ቁጥር ይሄ ነው ብዬ መናገር አልችልም። ጽ/ቤትን በተመለከተ በአብዛኛው ኦሮሚያ አካባቢዎች 120 ቢሮዎች ከፍተን እየተንቀሳቀስን ነው። አሁን ያለውን ለውጥ የተሸለ ከሚጠቀሙበት የፖለቲካ ኃይሎች አንዱ ኦፌኮ ነው። ሰፋፊ ስብሰባዎችን አድርገናል፤ ቢሮዎቻችንንም እያደራጀን ነው።
ኦሮሚያ ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር ያላችሁ የተናጠልም ሆነ የጋራ ግንኙኙት ምን ይመስላል?
አንድ እርምጃ የተራመድነው ከነዳውድ ኢብሳ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ነው። ከእሱም ጋር ቢሆን አቅጣጫ ማስቀመጥ ነው እንጂ በስፋት አልተደራደርንም። ዋናው አቅጣጫ ያስቀመጥነብት ጉዳይ ቄሮ የሚባለው የኦሮሞ ወጣት ትልቅ ኃይል ስለሆነ እንዳይከፋፈል ማድረግ ላይ ነው። ይህ ኃይል ድርጅቶቻችን ወዴት ይወሰዱናል የሚል ሥጋት አለው።
ከኦሮሞ ዴሞክራሲሲዊ ፓርቲ ጋር የተለየ ድርድር አያስፈልገንም።
የኦሮሞ ድርጅቶች መብዛትስ አያሳስባችሁም?
እኔ ባገኘዋቸው አጋጠሚዎች ለባለሥልጠናቱ እየነገረኳቸው ነው ብዙዎቹ መንግሥት የሚቀልባቸው ናቸው።
ምን ማለትዎት ነው መንግሥት የሚቀልባቸው ናቸው ሲሉ?
ገንዘብ የሚሰፈርላቸው፣ ደሞዝ ተሰጥቷቸው፣ ቢሮ ተከፍቶላቸው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። መንግሥት ለመቃወም ሳይሆን ተቃዋሚን ለመቃወም የተፈጠሩ ናቸው። ይህንን መንግሥት ያውቃል። ላገኘናቸውም የመንግሥት ባለሥልጣናት በግልጽ ቋንቋ ነግረናቸዋል።
ሌሎች ጠንካራና ነፃ የሚባሉት የኦሮሞ ድርጅቶችን በተመለከተ በራሳቸውም በሕዝቡም ግፊት ወደአንድነቱ እንዲመጡ እየጠየቃቸው ነው። ስለዚህ ምርጫ ሲመጣ ቢበዛ ሦስት ፓርቲዎች ብቻ የሚኖሩ ይመስለኛል። የተወሰኑት ከኦነግ ጋር፣ የተወሰኑት ከኛ ጋርና የተቀሩት ደግሞ ከኦዴፓ ጋር ትስስር የሚፈጥሩበት ሁኔተ ይፈጠራል የሚል እምነት አለኝ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በምዕራብ ኦሮሚያ እተፈጠረ ላለው የፀጥታ ችግር ኦፌኮ ምን እየሠራ ነው?
እኛ በተለያየ መንገድና ባነኘናቸው አጋጣሚዎች ሕዝቡን እያስተማርን ነው። ይሄ ችግር በዋናነት እዛ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ኃይች መካከል ነው። በግልጽ ቋንቋ የኦዴፓ እና የኦነግ ጉዳይ ነው። ይህንን ለማስተካከልና አንዳንድ ነገር በማድረግ ባለን መስመርና ባገኘናቸው አጋጣሚዎች ሁለቱንም ድርጅቶች እየመከርን ነበር። በሕዝባዊ ውይይቶችም በሚዲያም እንጠየቃለን ችግኖቹን መፍታት ወሳኝ ነው ብለን እናምናለን።
ከኛ ይልቅ የአገረ ሽማግሌዎች፣ የሃይማነት አባቶች፣ ምሁራን ቢሞክሩት ይሻላል የሚል እምነት አለን። የመፍትሔው አቅጣጫ ግልጽ ነው።
በመጨረሻ ማስተላለፍ ሚፈልጉት መልዕክት ካለ
ምሁራንና ጋዜጠኞች በተቻለ መጠን በተለይ የማንነት ጥያቄዎች ላይ ሕዝቡ እየተረጋጋ ወደ መደራደሩ፣ ወደ መተማመኑ ቢሄድ ይሻላል። ዋናው ጉዳይ የመተማመኑ ፖለቲካ ጉዳይ ነው። ሕዝቡ ውሎ አድሮ እየተነጋገረ፣ እየተደራደረ፣ የተመካከረ ተከባብሮ አብሮ የሚኖርበት ፖለቲካዊ ሥርዓት ወደ መፈጠሩ ማስተኮሩ ይሻላል። በተለየይ የመገናኛ ብዙኃን ጥንቃቄ ቢያደርጉ ጥሩ ነው።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here